ሁለት ወጣቶች በጸጥታ አስከባሪዎች ተገደሉ
(በኃይሌ ሙሉ | The Reporter)
አንድ የ16 ዓመት ታዳጊ ወጣት በሰሜን ጐንደር ዞን የጸጥታ ኃላፊ ጠባቂ መገደሉ ተገለጸ፡፡ በተመሳሳይም አንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል አንድ ወጣት በጥይት ተኩሶ ከገደለ በኋላ መሰወሩ ታውቋል፡፡
የሟች ቤተሰቦች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ነዋሪነቱ በጐንደር ከተማ የነበረው አወት ወልደ ገብርኤል የተባለው የ16 ዓመት ታዳጊ ወጣት፣ ነሐሴ 14 ቀን 2002 ዓ.ም. ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ የአንድ የከተማው ባለሥልጣን ልዩ ጠባቂ በሆነ ግለሰብ በሽጉጥ ተገድሏል፡፡
የሟች ወንድም አቶ ዓለም ወልደገብርአል የዓይን እማኞችን በመጥቀስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሟች ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ከዋለበት ቦታ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ሳለ፣ የሟች ጓደኛ ወደኋላ በመቅረቱ ‹‹ለምን ወደኋላ ትቀራለህ መሽቷል›› በማለት በኃይለ ቃል ሲናገሩት ተጠርጣሪው ‹‹እኔን ነው በኃይለ ቃል የምታናግሩኝ?›› የሚል ጥያቄ እንዳቀረበላቸው፣ ልጆቹም በቁጣ የተናገሩት ጓደኛቸውን እንጂ እርሱን አለመሆኑን ሲነግሩት፣ ተጠርጣሪው ሽጉጥ በመተኮስ የታዳጊ ወጣት አወትን ደረት መትቶታል፡፡ ባልጠበቀው ሁኔታ አደጋ የደረሰበት አወትም ወዲያውኑ ሕይወቱ አልፏል፡፡
ታዳጊ ወጣት አወት ሲገድል የተመለከቱ ሰዎች ገዳዩን ለመያዝ ሙከራ ሲያደርጉ፣ ተጠርጣሪው ሊይዙት ወደ ሞከሩት ሰዎች መሣሪያውን በማዞር አስፈራርቶ ለጊዜው ማምለጡን የጠቆሙት አቶ ዓለም፣ ተጠርጣሪው በዚያው ቀን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ተናግረዋል፡፡
የሟች ወንድም እንደሚሉት ከሆነ ተጠርጣሪው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ቢውልም የገደለበት መሣሪያ እስካሁን አለመያዙ በፍርድ ሒደቱ ላይ ተጽዕኖ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ‹‹የመሣሪያው አለመያዝ በሕግ ሒደቱ ላይ እንከን ይፈጥርብናል የሚል ፍርኃት አሳድሮብናል፤›› ሲሉ አቶ ዓለም ተናግረዋል፡፡
የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የነበረው የታዳጊ ወጣት አወት ድንገተኛ ሞት በቤተሰብ ላይ የፈጠረው ሀዘን መሪር መሆኑን የገለጹት አቶ ዓለም፣ ‹‹አንድ የጸጥታ አስከባሪ ከሚባል ሰው ሊፈጽም የማይችል የሽፍታ ድርጊት ነው፤›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም ምንም በማያውቅ አንድ ታዳጊ ወጣት ላይ እንደዚህ ዓይነት ግድያ መፈጸሙ፣ የሰው ልጅ ከቤቱ በሰላም ወጥቶ በሰላም ስለመግባቱ እርግጠኛ እንዳይሆን የሚያደርግ ክስተት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የጐንደር ከተማ የወንጀል ምርመራ መኮንን ምክትል ኢንስፔክተር ማረልኝ ሞላልኝ በበኩላቸው፣ ተጠርጣሪው ግድያውን ከፈጸመ በኋላ እጁን ለፖሊስ የሰጠ መሆኑን፣ ፖሊስም የሰው ምስክሮችንና ሌሎች ማስረጃዎችን አጠናቅሮ ለዓቃቤ ሕግ ማቅረቡን ጠቁመው፣ ከዚህ በኋላ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንደሚታይ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ምክትል ኢንስፔክተሩ ገለጻ፣ የሟች ሁለት ጓደኞች እስር ቤት ውስጥ ገብተው የልጁን ገዳይ ለይተው እንዲያወጡ የተደረገ ሲሆን፣ ሁለቱም ያለምንም ችግር ተጠርጣሪውን ከብዙ እስረኞች መካከል ለይተው መጠቆም ችለዋል፡፡
በተመሳሳይም ባለፈው ሳምንት ዓርብ ከጓደኞቹ ጋር ሲዝናና የነበረ አንድ ወጣት በአዲስ አበባ የፖሊስ አባል በጥይት ተገድሏል፡፡
በተለምዶ 22 ማዞሪያ በሚባለው አካባቢ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ከስድስት ጓደኞቹ ጋር ሲዝናና የነበረው አለማየሁ ለማ የተባለው ወጣት በፖሊስ የተገደለው፣ የድራፍት ብርጭቆ መሰበርን ተከትሎ በመጣ ጭቅጭቅ ምክንያት መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡
የሟች ጓደኛ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ሟችና ሌሎች ጓደኞቹ ለተሰበረ የድራፍት ብርጭቆ አንከፍልም ትከፍላላችሁ በሚል አለመግባባት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ለተሰበረው የድራፍት ብርጭቆ 25 ብር ከፍለው ከሆቴሉ ወጥተዋል፡፡
እርሱን ጨምሮ ሌሎች ስድስት ጓደኞቹ ከሆቴሉ እንደወጡ የሆቴሉ የጥበቃ ሠራተኛ በአካባቢው ለነበሩ ሁለት ፖሊሶች የሆነ ነገር ሄዶ እንደነገራቸው፣ ፖሊሶችም ማንንም ሳያናግሩ በአምስት ጓደኞቻቸው ላይ ድብደባ መጀመራቸውን የገለጸው ይኼው የዓይን እማኝ፣ ሟች ጓደኛውና እሱ፣ ‹‹ጓደኞቻችንን ለምን ትደበድባላችሁ? ሕጋዊ ናችሁ ብለን ነው እንጂ እናንተ ሁለት እኛ ሰባት ነን፤›› ብለው ሲናገሩ፣ አንደኛው ፖሊስ በጥይት ተኩሶ ጓደኛውን እንደገደለው ተናግሯል፡፡ እንደ ዓይን እማኙ ገለጻ፣ ፖሊሱ ጓደኛውን ከገደለው በኋላ መሣሪያውን ይዞ ሸሽቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመረጃ ክፍል ሠራተኛ በበኩላቸው፣ ለተሰበረ የድራፍት ብርጭቆ ዋጋ ክፈሉ በሚል በተነሳ ጭቅጭቅ በሆቴሉ ብጥብጥ በተከሰተበት ወቅት፣ በቦታው የተገኙት ሁለት ፖሊሶች ሟችና የሟችን ጓደኞች እንዲከፍሉ በኃይለ ቃል ሲናገሩ፣ ሟች የአንዱን ፖሊስ አንገት ማነቁን፣ የጓደኛውን አንገት መታነቅ የተመለከተው ፖሊስም አናቂውን በጥይት ጭንቅላቱን መትቶ የገደለው መሆኑን የእለቱ መረጃ እንደሚጠቁም ተናግረዋል፡፡
የገዳዩ ባልደረባ ልጁ ከተገደለ በኋላ ወዲያውኑ ለፖሊስ እጁን የሰጠ መሆኑን የጠቆሙት እኚሁ የመረጃ ክፍል ሠራተኛ፣ ገዳዩ ግን ግድያውን ከፈጸመ በኋላ ማምለጡን ገልጸዋል፡፡