ከዳኮታ የጥናት ማእከል የቀረበዉ የሁሉን-አቀፍ ትብብር መፍትሄነት ከእስከመቼ የዝግጅት ክፍል

ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻፫ ዓመተ ምህረት በዳኮታ የጥናት ማዕከል የቀረበውን የሁሉን-አቀፍ ትብብር መፍትሄነት ተመለከትነው። የዳኮታ የጥናት ማዕከልን ለቀረቦታቸውና ለበሳል ትንታኔያቸው እናመሰግናቸዋለን። በኛ በኩል ደግሞ ይኼን ጨዋነት የተሞላበት የበሰለ የፖለቲካ ዉይይት የኛን ሀሳብ በማቅረብ እንቀላቀለዋለን። እዚህ ላይ ማሳሰብ የምንፈልገው፤ የመወያያ ርዕሱ፤ የትብብሩን መንገድ በሚመለከት የቀረበው ሀሳብ እንጅ፤ አቅራቢዎቹ ግለሰብ ሆኑ ስብስቦች አለመሆናቸውን ነው። ማንም ያቅርበው ማን፤ ውይይቱ በቀረበው ሀሳብ ላይ ነው። በዚህ መግባባት ተመርኩዘን፤ የኛን አመለካከት እናቀርባለን።

እስካሁን በተመለከትነው፤ ሁሉን አቀፍ ትብብር አይሠራም ወይንም አያስፈልግም የሚል በፅሑፍ አላየንም በንግግርም አላዳመጥንም። ስለዚህ ባልተባለ ሀሳብ መወያየቱ፤ አግባብነት የለውም። ውይይቱ ሁሉን አቀፍ ስንል፤ መተቃቀፊያው ምንድን ነው? ነው። በዚህ መተቃቀፊያ ስምምነት ከተገኘ፤ መተቃቀፉን እንሽቀዳደምበታለን።

ለኛ መተቃቀፊያው ኢትዮጵያዊነት ነው። ይኼን የምንለው፤ የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መንግሥት ባሁኑ ሰዓት የያዘው ዘመቻና የትግሉ ማዕከላዊ መሰባሰቢያችን ኢትዮጵያዊነታችን ነው ብለን ስለምናምን ነው። ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያዊነት ማለት በሀገራችን ካለው የፖለቲካ ሀቅ አኳያ የሚኖረን ግንዛቤ ነው። ለሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መንግሥት፤ ኢትዮጵያዊ ማለት፤ የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መንግሥትን የሚደግፍና የመንግሥቱን ተቃዋሚዎች የሚሠድብ ማለት ነው። ለኛ ኢትዮጵያዊ ማለት፤

፩ኛ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዓላዊነት መከበር፤
፪ኛ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት መጠበቅ፤
፫ኛ በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት መስፈን፤
፬ኛ ለያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዴሞክራሲያዊ መብት በሕግና በተግባር መረጋገጥ፤
፭ኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ሥር መስደድ፤
፮ኛ የፖለቲካ ምኅዳሩ ኢትዮጵያዊነትን አናግተው፤ ሊከፋፍሉ ከሚችሉ ዘውግንና ሀይማኖትን መነሻ ካደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች ነፃ መሆን፤ እና
፯ኛ የዚህ ሁሉ ጠንቅ የሆነው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መንግሥት ተወግዶ፤ በቦታው በኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድና ውሳኔ የተመሠረ መንግሥት መቋቋም፤ መታገል ማለት ነው።

እንግዲህ በኢትዮጵያዊያን መካከል የሚኖረውን መተቃቀፍ ከዚህ አንፃር ነው እኛ የምናየው። እነዚህ ሰባት ነጥቦች፤ መሠረታዊና አነስተኛ መሠባሰቢያ ነጥቦች ናቸው እንላለን። መሠባሰቢያ ነጥቦችን ሳናበጅ በባዶ መሰባሰብ የለም። የዳኮታ የጥናት ማዕከል፤
˝ እኛ የምንለው አገራችን ባለፈው ሃያ ዓመታት በወያኔ ስር ከተለወጠችበት ሁኔታ አንጻር፤ በወያኔ የተጨቆኑና ፀረ-ወያኔ የሆኑ ብሔረሰባዊና ሀገራዊ ድርጅቶችን ያካተተ ትብብር በመመስረት የመለስ መንግስት የሚፈጽመውን ጥፋት መመለሻ የሌለው ደረጃ ከመድረሱ በፊት ማስቆም ይቻላል ነው። ̋
ይላል።

ይህን አባባል ለመቀበል ይቸግረናል። ወያኔ እያራመደ ያለው፤ የ ˝ብሔረሰቦችን ጭቆና ̋ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን እንደ አንድ መንግሥት፣ ሀገርና፤ ሕዝብ ውሎ ማደር በተቻለው መንገድ ማጥፋትና፤ በቦታዉ፤ ወያኔ በተበተበው ሤራ የተበታተነ ትንንሽ መንግሥታት ማቋቋም ነው። በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት መንግሥት እየተራመደ ያለው፤ ረሀብን በመላ ኢትዮጵያ፤ ከትግራይ እስከ ሶማሊያ ማስፋፋት ነው። በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት መንግሥት እየተራመደ ያለው፤ የሀገራችንን ለም መሬትና ደንበር ለዉጭ አሳልፎ መስጠቱ ነው። በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት መንግሥት እየተራመደ ያለው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ለመውጣት አንዱ ባንዱ የሚጠቃጠቅባት መሆኗ ነው። በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት መንግሥት እየተራመደ ያለው፤ የኢትዮጵያ በማንኛውም የሀገሮች የሥልጣኔ መለኪያ ወለል ላይ መወዘፏ ነው።

ታዲያ ይኼን ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የሚታገሉት የፖለቲካ ሀቅ ሆኖ፤ እንዴት ነው ˝ ፀረ-ወያኔ የሆኑ ብሔረሰባዊና ሀገራዊ ድርጅቶች ̋ በአንድነት ይሠለፉ የምንለው? ኦነግ የሚለው፤ ˝ ኦሮሞዎች በሙሉ የኔ ደጋፊዎች ናቸዉ፤ ከፈለጋችሁ ዶክተር ጌታቸው በጋሻውን ጠይቁ። ማንም በኦሮሚያ ምድር ሌላ ተወካይ ሊያስብም ሊታሰብም አይገባውም ” ነው። ኦብነግ የሚለው፤ ˝ የኦጋዴን ነዋሪዎች በሙሉ የኔ ደጋፊዎች ናቸዉ። ማንም በኦጋዴን ምድር ሌላ ተወካይ ሊያስብም ሊታሰብም አይገባውም ” ነው። በዚህ ሂሳብ ግንቦት ሰባት በነዚህ ክልሎች ደጋፊ አባላት የሉትም ማለት ነው። ይህ ትክክል ካልሆነ ደግሞ፤ ችግር አለ ማለት ነው። እና፤

“በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለውም ጥፋቱን በቶሎ ከማስቆምም በተጨማሪ የዚህ ዓይነት ትብብርና ትግል በትክክልኛ መንገድ ከተመራ በሸግግር ወቅት ሊኖሩ የሚችሉ ችግሮችን ማስቀረት ይችላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀገራችን በአሁኑ ሰዓት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የተረጋጉ ሀገራት ረድፍ ውስጥ ለመግባት በታሪኳ ምክንያት ያለባትን የእኩልነት፤ የዲሞክራሲና የፍትህ ጉድለቶች ማስተካከል አለባት።”

በማለት ያቀረቡት ምኞት እንጂ ቀን የማየት ዕድል የሌለዉ ግንዛቤ ነው ማለት ነው።
ለዚህ ሁሉ ሁሉን አቀፍ ትብብር መነሻቸው፤

“ግትር የፖለቲካ ክርክር ከሚፈልግ ሰው በስተቀር በውጭም ያሉት እንደ ኦነግ ዓይነት ድርጅቶች ቀድመው የአቢሲኒያ ቅኝ ግዛት፤ ነጻ ኦሮሚያ ወይም ሞት ከሚለው አቋማቸው ብዙ ርቀው የብሄረሰቦች ጥያቄ በዲሞክራሲ፤ በእኩልነትና በፍትህ ላይ በተመሰረት ሥርዓት ለመፍታት እንደሚቻል በየቦታው በቱባ ቱባ መሪዎቸቸው እየተናገሩ ነው።”

የሚለው ቀረባ ነው።

በሌላ በኩል ያለው ሀቅ ደግሞ፤ በመርኀ ግብራቸውና በየድረ ገፆቻቸው የሚታየው፤ መሠረታዊ እምነታቸውና ግባቸዉ ነው። ለኛ መተማመን የሚጀምረው ከዚህ ነው። መጀመሪያ፤ የሚናገሩት፣ የሚፅፉትና የሚሰብኩት አንድ መሆኑ! ከዚያ ቀጥሎ የምንስማማባቸውን በጋራ ማንጠብ ነው። የወያኔን በዘውግ ተደራጅቶ ሀገሪቱን መከፋፈል የሚቃወም ስብስብ፤ መከፋፈልን መሠረት ካደረገ ማንኛውም ድርጅት ጋር መሠለፉ፤ ቀለል አድርገን ብናስቀምጠዉ፤ አላዋቂነት ነው።

የዳኮታ የጥናት ማዕከል ባንድ በኩል፤
” በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ግልጽ የሆነ በዘር ላይ የተመሰረተ የርስ በርስ መተላለቅ እንኳን ደርሶ የእኩልነታችን መፍትሔ መገንጠል ነው ተብሎ አልቀረበም። ”
“የተጀመረው የሁሉን-አቀፍ ትብብር ውይይት ጉዞ የት ስምምነት ላይ እንድሚደርስ ለጊዜና ለትብብሩ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እንተወዋለን። እንደ እኛ እምነት ግን ይውይዩ መዳራሸ የሚቀጥሉት ሁለት ሃሳቦች ቢሆኑ ሁላችንንም አቸናፊ ያደርገናል የሚል ጽኑ ዕምነት አለን። አንደኛው የትብብሩ መዳረሻ ዲሞክራሲያዊ ስርአት በአገራችን መመስረት መሆን አለበት። ይህም ማለት አንድ ሰው አንድ ድምጽ በሚለው በምርጫ ሂደት ለመዳኘት ሁሉም ፍቃደኛ መሆን አለበት። ሁለተኛው የትብብሩ መዳረሻ ደግሞ የኢትዮጵያ ሉዕላዊነት መሆን አለበት። ከዛ መለስ የሆኑ ጥያቄዎች በሙሉ ጠረጴዛ ላይ ቀርበው ልንነጋርበት እንችላለን። አሉ የሚባሉ ጥያቄዎችና ችግሮች በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩ ናቸው። ኢትዮጵያን አንድ ሉአላዊ አገር መሆኗን ጥያቄ ውስጥ ሳናስገባ ምፍትሄ ልንሰራ በደንብ እንችላለን የሚለው ቅድመ ሁኔታ ሚዛናዊና ሊያቀራርብ የሚችል አቋም ሆኖ አግኝተንዋል። በርግጥ በመጀመርያ ይህ ሁለተኛ ሃሳብ በቅድመ ሁኔታ መቀመጡ ላያቀራርብ ይችላል ብለን አስፈርቶን ነበር።” (መሠመሩ በኛ)
ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ፤

“ለመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ተቃዋሚዎች አንድ አይነት ስምምነት ላይ ለመድረስና አብሮ የሚያሰራ ስምምነት ለማድረግ በርግጥ ዋና ችግር የሆነው መገንጠል የሚለው አላማ ነው ወይ ብለን ስንጠይቅ የእኛ መልስ አይመስለንም ነው።”
ይላሉ።

ቆይ! አሁን ባለን ሳይንሳዊ ግንዛቤ፤ በአንድ ጊዜ ሁለት ቦታ በአካል መገኘት አይቻልም። አንድም ለመገንጠል ደጋፊ ሆኖ ከደጋፊዎች ጋር አብሮ መቆም ነው፤ አለያም መገንጠል ከስሌት አይገባም ብሎ አቋም መውሰድ ነው። በፖለቲካው ምኅዳር የተሠለፉትን በዘውግ የተደራጁ ነፃ አውጪ ድርጅቶችን አስመልክቶ በጭፍኑ መዝጋት አይቻልም። ዋና የሆነውን የኢትዮጵያዊነት ፯ ነጥቦችን አንግቦ መጠጋትና የሚሉትን ማድመጥ ያስፈልጋል። እናም ለብሶታቸው መንስዔ የሆነውን የፖለቲካ ሀቅ ተቀብሎ፤ መፍትሄ የሚሆነው፤ ለጥሩ ነገ መታገል እንጅ ለጥሩ ትናንት መታገል እንዳልሆነ ማሳመን ነው። ተጨቁነናል ሲሉ ትክክል ናቸው። በታሪክ የሠፈረ በደል አለ ሲሉ ትክክል ናቸው። በአንፃሩ ደግሞ፤ ጭቆናቸው የግል እንዳልሆነና ሀገራዊ አንድነታችን ያየለ መሆኑንና ትግሉን ከኢትዮጵያዊነት አንፃር መያያዝ እንዳለብን ማስገንዘቡ የኛ ኃላፊነት ነው። ይህ የሚሆነው ግን ትግሉ፤ የኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያዊነታቸው ለኢትዮጵያዊነታውቸው መሆኑን በማስቀደም ነው።

እንግዲህ ለዚህ ሁሉ መሠረት የሚሆነው፤ የኢትዮጵያዊነትን አንድነት አስቀድመው፤ የፖለቲካ መድረካቸው በዘውግ ወይንም በሀይማኖት ያልመሠረቱ ድርጅቶች ሲሰባሰቡ ነው። ይኼን አቀራረባችንን የዳኮታ የጥናት ማዕከል አልወደደልንም። በለዘብታ ከመጎንተል በቀር፤ አጠንክረው አላጣጣሉትም። እንዲህ ይላሉ፤

“ይህ ምክንያት በዚህም ሆነ በዛ መንገድ መፍትሄ ልንፈልግለት የሚገባ ችግር መኖሩን በማመን ነው የሚነሳው። መፍትሄው ላይ ለመነጋገርና ለመስራት ግን አሁን ጊዜው አይደለም ነው አንደምታው። ተጽኖ ማሳደር እንድንችል መጀመርያ እኛ መጠንከር አለብን ነው። ጥንካሬ ደግሞ እንደሚታወቀው አንጻራዊ ነው። ስለዚህ ይህ አስተሳሰብ የሀገር-አቀፍ ድርጅቶች በብሄረሰብ የተደራጁ ድርጅቶች ላይ የጥንካሬ የበላይነት እስክናገኝ እንጠብቅ ነው። ይህ አይነት አካሄድ የሚሰራበት ሁኔታ ይኖራል። አሁን የትግሬ ዘረኞች የሀገሪቱን የጦር፤ የጸጥታ፤ የፕሮፖጋንዳና የኢኮኖሚ አውታር በተቆጣጠሩብትና ሆን ብለው በሕዝቡ ውስጥ የከፈፍለህ ግዛ ፖሊሲ በሚያራምዱበት ሰዓት አንዱ ዓይነት ተቃዋሚ በሌላው ዓይነት ተቃዋሚ ላይ እዚህ ግባ የሚባል የጥንካሬ የበላይነት ሊኖረው አይችልም። የሚፈለገው ጥንካሬ የሚመጣው በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ በሀገር-አቀፍ ድርጅቶች ፕሮግራም ዙሪያ ያለው ድጋፍ ስፋት ነው። ይህ ደግም አሁንም ቢሆን ለ20 ዓመታት ወያኔን እንቅልፍ የነሳው ኃይል ነው።”
መቼ ነው ” የትግሬ ዘረኞች የሀገሪቱን የጦር፤ የጸጥታ፤ የፕሮፖጋንዳና የኢኮኖሚ አውታር ” ያተቆጣጠሩብትና ” ሆን ብለው በሕዝቡ ውስጥ የከፈፍለህ ግዛ ፖሊሲ” ያላራመዱበት ሰዓት? የሀገር አቀፍ ድርጅቶች የዓላማ አንድነት ስላላቸው፤ በአንድነት ይሠለፉ የሚለው፤ ከየትም ወገን ተቃውሞ ሊነሣበት የሚገባ ሀሳብ አይደለም። ይኼን ማራመድ የሚኮነንበት ጉዳይ ለኛ አልታየንም።

ትብብርን ለመመስረት የሚያግድ ጊዜ ሆነ የጊዜ ገደብ የለም። የዓላማ መቀራረብና ፈቃደኝነቱ ብቻ ነው የሚያግደው። ቅደም ተከተል ማስተካከልን እንደ እምቢታ መውሰድ፤ ቅነንነት የጎደለዉ ፖለቲካ ነው። አዎ የሀገር አቀፉ አጀንዳ አቸናፊ ሆኖ እንዲወጣ እንፈልጋለን። አዎ ዘውግን የተመረኮዘ ፖለቲካ ከፖለቲካው ምኅዳር እንዲወገድ እንፈልጋለን።

” . . . በአማራጩ “የአንድነት ኃይሎች” በሚል መጠሪያ የሚደረገውን የትብብር ሥራ ላይ የድጋፍ ሥራ መሥራት ይመረጣል። ይህንን የአንድነት ኃይሎችን የህብረት ሃሳብ ማብራራት የተሻለና የበለጠ ጠቃሚ ስሚሪት ይመስለናል። ለምሳሌ ለእኛ ይህ የአንድነት ኃይሎች ብላችሁ የሰየማችሁት ትብብር ከአሁን በፊት ተፈጥሮ እስከ አሁንም ካለው የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ኃይሎች ሕብረት እንዴት እንደሚለይ ግልጽ አይደለም። ልዩነት ከሌለ ደግሞ አዲሱ ትብብር ምን ምን ቢሰራ ነው ከቀድሞው ህብረት የተሻለ ውጤት የሚያመጣው?”

በማለት በንቀት አሥፍሮልናል። በመጀመሪያ አንድነትን “የአንድነት ኃይሎች” ብሎ በጥቅስ ማስቀመጡ አላስደሰተንም። ሁለተኛ ይህ “የአንድነት ኃይሎች ብላችሁ የሰየማችሁት ትብብር” ብሎ ማሾፍ ንቀትን ልብስ ማድረግ ነው። መቼም የኤኤፍዲን መመሥረትና የትም አለመድረስ ማገናዘቡ በተገባ ነበር፤ ትምህርት ለመውሰድ።

[email protected]