የፖለቲካ ተንታኞች የወያኔን የአምስት አመት እቅድ ማጣጣላቸውን ቀጥለዋል
ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ለመጪው አምስት አመታት ያወጣው እቅድ በኢኮኖሚስቶች እና በፖለቲካ ተንታኞች ሲወገዝ ሰንብቷል።
ባላፈው ሳምንት ለዝግጅት ክፍላችን መልክት የላኩ አንድ የፖለቲካ ተንታኝም፣ አገዛዙ በዚህ እቅዱ ውስጥ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን አስመልክቶ ያሰፈረውን ቁጥር አጣጥለውታል። አዲስ አበባ የሚገኘው የሬውተርስ የዜና አገልግሎት ሪፖርተር ከማእድን እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አለማየሁ ተገኑ ጋር ሐሙስ ቃለ መጠይቅ አድርጎ፤ ሚኒስትሩ የወያኔ አገዛዝ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ምርት ከ2000 ሜጋ ዋት ወደ 10000 ሺህ ሜጋ ዋት እንደሚጨምር መናገሩን ዘግቧል።
ይህንን አስታከው አስተያየታቸውን የሰጡን የፖለቲካ ተንታኝ፥ የወያኔ አገዛዝ የዛሬ አምስት አመት ባወጣው እቅድ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ከ15% ወደ 50% ከፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ እንደነበር አስታውሰዋል። ከሁለት ወራት በፊት በአገዛዙ ቁጥጥር ስር የሚገኘው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል በድረ-ገጹ ላይ ባወጣው ዘገባ ግን ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት የሚያገኙት ኢትዮጵያውያን 14 በመቶ ብቻ መሆናቸውን መግለጹን ጠቅሰዋል። የፖለቲካ ተንታኙ፥ ወያኔ እራሱ የሚያወጣቸውን ቁጥሮች ላነጻጸረ፤ አገዛዙ የሃሰት ተስፋን ለመስጠት ሲል ብቻ ሊፈጽም የማይችለውን ቃል እንደሚገባ ግልጽ ነው ብለዋል።
መለስ ዜናዊ ከአምስት አመታት በፊት በሶስት አመታት ጊዜ ውስጥ የአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ሽፋን መቶ በመቶ እንደሚሆን መናገሩ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ፥ ከአምስት አመታት በኋላ ግን ያ ቁጥር 0.4 በመቶ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህም በተጨማሪ፥ ዘረኛው አምባገነን የዛሬ ሃያ አመት ገደማ የኢትዮጵያ ህዝብ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ እንደሚጀምር ከመናገር አንስቶ፤ በቅርብ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ የዔሌክትሪክ ሃይል ስለሚትረፈረፍ ከዚህ በኋላ ሻማ የሚበራው ለልደት ብቻ ነው ማለቱ የሚዘነጋ አይደለም።