የደሴ ፖሊሶች የግፍ ድርጊት – ፍኖተ ነጻነት
አቶ ብስራት አቢ የአንድነት ፓርቲ የደብበ ወሎ ዞን ሰብሳቢ
ዛሬ ነሃሴ 30 በምኖርባት ደሴ ከተማ በተለምዶ ባምቧ ውሃ የተባለው አካባቢ በአንድ መዝናኛ በረንዳ ላይ ከጓደኞቼ ጋር ተቀምጠን እየተጫወትን ነው፡፡ ሰዓቱ 9፡30 ይሆናል፤ ጎዳናው ላይ አንድ የገጠር አለባበስ የለበሰ ሰው ከፖሊሶች ጋር ለፀብ ሲገባበዝ ተመለከትኩት፡፡ ሰውየው ጠጥቷል እናም ፖሊሰቹን ለመተናኮስም ቃጥቶታል፡፡ ፖሊሶቹ የወሰዱት እርምጃ ግን ፍፁም ህግን አስከብራለሁ ከሚል አካል የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ ከፖሊስነትም ባለፈ ማዕረግ የደረደሩት ፖሊሶች ሰውየውን በያዘው ቀርከሃ እየተቀባበሉ ቀጥቅጠውት እግርና እግሩን ይዘው መሬት ለመሬት እየጎተቱ በአቅራቢያቸው ወዳለው 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ይዘውት ገቡ፡፡ በግምት ከ1 ሰዓት ቆይታ በኋላ ሰውየው በውሀ ርሶ አንድ እግሩ ለመርገጥ እየተቸገረ ወጣ፡፡ በጣቢያው ውስጥ ምን እንደደረሰበት ለመገመት አልተቸገርኩም፡፡ ግፍ የደረሰበት ሰው ሰክሮ ከፖሊሶች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ መግባቱ ትክክል አይደለም፤ ሆኖም የሰውየው ስህተት/ጥፋት በምንም አይነት መልኩ ፖሊሶቹ ለፈፀሙት የግፍ ድርጊት ማስተባበያ መሆን የለበትም፡፡
ይህን ግፍ የፈፀሙት ፖሊሶች የደሴ ፖሊሶች ሙሉ ለሙሉ ወከሉም አልወከሉም የሰውን ልጅ እንደከብት መሬት ለመሬት እየጎተቱ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲያስገቡ “አረ በህግ” የሚል አንድ ፖሊስ እንኳ መጥፋቱ የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያን ባልደረቦች እንደተቋምም ለመውቀስ እገደዳለሁ፡፡ የሰው ልጅ ሰብአዊ ክብሩ ተዋርዶ ግፍ ሲፈፀምበት እንደመመልከት ምን ልብ የሚሰብር ነገር ይኖራል?
በትግላችን ሰብአዊ መብት የተከበረባት ኢትዮጵያን በቅርቡ እውን እናደርጋለን!!
– See more at: http://www.fnotenetsanet.com/?p=5595#sthash.NC76bcCe.dpuf
