ረጅም ዕድሜ ለማንዴላ! ረጅም ዕድሜ ለሰው ልጆች መብትና ነፃነት ለሚታገሉ ሁሉ!!! በፍቅር ለይኩን -ከደቡብ አፍሪካ
የ93 ዓመቱ አዛውንትና የነፃነት ታጋይ የኔልሰን ማንዴላ የልደት በዓል ሰኞ ሐምሌ 18 2011 እ.ኤ.አ በዚህ በደቡብ አፍሪካ በታላቅ ስሜት ነው የተከበረው፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ በርካታ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ የዜና አውታሮች እና ዓለም አቀፍ የመገኛኛ ብዙሃን ለእኚህ ታላቅ አባት የእንኳን አደረሰዎ መልእክትና የመልካም ልደት ምኞት መግለጫ ተጨናንቆ ነበር የዋለው፡፡
መሰረቱን በዚህ በደቡብ አፍሪካ ያደረገው DSTVም በዕለቱ የማንዴላንና የትግል አጋሮቻቸውን የነፃነት ተጋድሎ የሚያዘከሩ ሁለት ጥናታዊ ፊልሞች አቅርቦ ነበር፡፡ በሀገሪቱ ከሚታተሙና በርካታ አንባቢ ካላቸው ጋዜጦች መካከል ታይምስ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በመላው ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ታዳጊ ህፃናት ለኔልሰን ማንዴላ ሰኞ እለት በትምህርት ቤታቸው 93ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው እንኳን አደረስዎ የዘመሩት መዝሙር ከህጻናቱ ፎቶግራፍ ጋር አውጥቶት ነበር፡፡ የመዝሙሩ መልእክት የህፃናቱን ከልብ የሆን ፍቅራቸውን የሚያነጸባርቅና በእጅጉ ልብን የሚነካ ነው፡፡
በዛ የሰው ልጅ በቆዳው ቀለም በሚፈረጅበትና የአፓርታይድ ዘረኛ መንግስት መብታችን ይከበር ብለው በወጡ የስዌቶ ጨቅላ ህፃናት ተማሪዎች በነጭ ፖሊሶች ጥይት ደማቸው የውሻ ደም በሆነበት ሀገራቸው፣ ዛሬ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ያለምንም የዘር ልዩነት ለነፃነትና ለዚህ እኩልነት ያበቋቸውን ኔልሰን ማንዴላን መልካም ልደት በሚል ጥኡም ዜማ እንዲህ ዘመሩላቸው፡-
Madiba, Halala
Happy birthday to you!
Happy birthday to you!
Happy birthday dear Tata!
We love you Tata
We love you Tata
Nelson Mandela. Ha hona
Ya tshwanang le wena (there is no like you)
Yeep yeep!
Hooray!
በኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽን አስተባባሪነት በዚህ በደቡብ አፍሪካ ማንዴላ ልደት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ነበር የዋለው፣ በኢንግላንድ፣ በአቡዳቢና በሌሎች ሀገሮችም ጭምር የልደት ቀናቸው የተከበረው በበጎ ፈቃደኝነት ወላጅ አልባ ህፃናትን በመጎብኘት፣ የህክምና እርዳታ በመስጠት፣ አረጋውያንን በመጎብኘትና በመሳሰሉት በጎ ተግባራት ነው፡፡ በኢስተርን ኬፕ የትውልድ ቀዬቸው በሆነችው በቁኑ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የቀድሞ ባለቤታቸውና የትግል አጋራቸው ዊኒ ማንዴላ እነዲሁም የANC ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በድምቀት ነበር የማዲባ 93ኛ የልደት በዓል የተከበረው፡፡
በኒዮርክ የሚገኘው የመንግስታቱ ድርጅትም በጽ/ቤቱ በእለቱ የማንዴላን ፖለቲካዊ ሰብእናና የነፃነት ትግል የሚዘክር አውደ ርዕይ አዝጋጅቶ ነበር፡፡ ጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫም፡- “The exhibition is a special dedication to Mr. Mandela in part as a commemoration of his ninety-third birthday on July 18 and most importantly, for his selfless devotion of his life “to the service of humanity – as a human rights lawyer, a prisoner of conscience, and an international peacemaker.”
ከተለያዩ የዓለማችን መሪዎችና ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የእንኳን አደረስዎ መልእክት ተቀብለዋል፡፡ በእለቱ ደቡብ አፍሪካን ሲጎበኙ የነበሩት የብሪትሹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ባሰተላለፉት የእንኳን አደረስዎ መልእክታቸው፡-
“President Mandela is an inspiration to the world, and as we celebrate his birthday and look back at just how far South Africa has come, so I believe we can look forward with confidence to an even better future for South Africa and her people,”
የዩናይትድ ስቴትሱ ባራክ ኦባማም በራሳቸውና በአሜሪካ ህዝብ ስም ባስተላለፉት የመልካም ልደት ምኞት መግለጫቸው፡-
“Mandela is a beacon for the global community and for all who work for democracy, justice and reconciliation. His legacy exemplifies wisdom, strength and grace, and on the anniversary of his birth we salute the example of his life”
ማንዴላ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ እኩልነትና ነፃነት የታገሉ የፍቅርና የይቅርታ ሰው መሆናቸውን በዚህ በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ ፍሪ ስቴት ዩኒቨርስቲ ሬክተር የሆኑ ፕሮፌሰር ጃነሰን በጆሐንስበርግ ለሚታተመው ታይምስ ለተባለው ጋዜጣ በላኩት ጹሑፍ፡-
“…affectionately known to all South African by his clan name, Madiba, and Tata (isi Xhosa for Father), Mandela represents many things: the importance of standing by your own beliefs, dignity, equality, humility, strength, determination, selflessness and above all, forgiveness…”
የተባበሩት መንግስታት በ2009 በዓለም አቀፍ ደረጃ የማንዴላ ቀን እንዲከበር ወስኗል፣ በዚህም ቀን መሪዎች ለዜጎቻቸው እኩልነትና ነፃነት የማንዴላን የሰላም፣ የአንድነትና ይቅር ባይነትን መርህ በመከተል ዓለማችን የሰው ልጆች ፍትህ በማጣት የሚሰቃዩባት፣ በአምባገነኖች የአገዛዝ ቀንበር ፍዳቸውን የሚቆጥሩበት የሰቆቃ ዘመን ሚያበቃበት እንዲሆን ነበር የእኚህ የሰው ልጆች መብት ታጋይ፣ የሰላምና የፍቅር-የይቅርታ ተምሳሌት የሆኑት የኔልሰን ማንዴላ ቀን እንዲከበር የወሰነው::
አሰገራሚው እውነታ ግን በጣት ከሚቆጠሩ የአፍሪካ መሪዎች በስተቀር ሀገራችንን ጨምሮ የእኚህን የነፃነት ታጋይ ከማሞካሸት በስተቀረ ህዝባቸው የነፃነት አየር ይተነፍስ ዘንድ ፍትህና ዲሞክራሲ ይሰፍን ዘንድ ፍቃደኞች አለመሆናቸውንና እነዲሁም ላለፉት የትውልዱ የታሪክ ስህተቶች ለአንድነትና ለሰላም ሲባል ስህተቶችን በይቅርታ ለመዝጋት የሚችል የመንፈስ ልእልና ላይ ገና ያልደረሱ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ታዝበናል፡፡
ለ27 ዓመታት በዘረኛው የአፓርታይድ መንግስት ቀዝቃዛውን የአትላንቲክ ውቅያኖስ ተጎራብቶ በተገነባው በሮቢን ደሴት ላይ በግዞት የታሰሩት ማንዴላ ከእስር በተፈቱ ማግስት ያደረጉት ነገር ቢኖር ህዝባቸውን ለበርካታ ዓመታት ለሞት፣ ለውርደትና ለሰቆቃ ከዳረገው የአፓርታይድ ዘረና መንግስት መስራችና አቀንቃኝ ወደነበሩት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ሟች ፕሬዝዳንት ሚስት ዘንድ በመሄድ በቀድሞ የአፓርታይድ ዘመን አሁን በሕይወት የሌሉት ባለቤታቸው በሳቸውና በህዝባቸው ላይ ስላደረሱባቸው ታሪክ ለማይረሳው ግፍ ከልብ የሆነ ይቅርታ ማድረጋቸውን በአካል በሟች ፕሬዝዳነቱ ቤት ተገኝተው በሕይወት ለነበሩት ለባለቤታቸው፣ ለህዝባቸውና ለዓለም በማወጅ ለሀገራቸው አዲስ ታሪክ ምእራፍን ከፈቱ፡፡ ዛሬይቱ ደቡብ አፍሪካ ሰላምና ብልጽግና ማንዴላና የሳቸውን መርህ የተከተሉ በሳል የፖለቲካ አመራሮች የወሰዱት ለሰው ልጆች መብት መከበርና ፍትህ መስፈን በጽናት መቆም ነው፡፡
ዛሬ በሀገራችን ትውልድ እርስ በርሱ የሚወቃቀስበት፣ ዘርና ጎሳ ለይተን እርስ በራሳችን ለበቀል የምንፈላለግ ወደ መሆን ዘግናኝ የታሪክ ምዕራፍ የተሻገርነው በከፊል በሀገራችን ታሪክ ለዘመናት የነበሩ ነገሥታትና መንግስታት ልዩነቶቻቸውን ይፈቱ የነበሩት ደም በማፍሰስ ብቻ ስለነበር ነው፡፡ በደልን በይቅርታ ሽሮ ለሀገርና ለህዝብ ሰላምና አንድነት ሲሉ ይቅር መባባል በእኛ ታሪክ ውስጥ ውርደት ከውርደትም በላይ የሞት ሞት ነው፣ በፍቅር መሸነፍ በእኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ ፈጽሞ የለም፣ ሰለዚህም የመበላላትና የመጠፋፋት ታሪካችን ዛሬም ቀጥሏል፡፡ ገና ያላወራረድነው የደም ካሳ በብዙዎቻችን ልቡ ውስጥ እያቃጨለ ነው፡፡
ማዲባ በፍቅር በመሸነፋቸው ሀገራቸውን ካነዣበበባት የእርስ በርስ እልቂት ለመታደግ ችለዋል፣ ምንም እንኳ የዘረኝነቱ አበሳ አሁንም ድረስ ፈጽሞ ያልጠፋ ቢሆንም፣ ጥቁሩ ድቡብ አፍሪካዊም ከነጮቹ አነፃር ሲታይ በኢኮኖሚ ቀውስ፣ በድህነት የሚቆራፈድ፣ በስራ እጦት የሚስቃይና ችግሮቹ ሙሉበሙሉ የተቀረፉ ባይሆንም የትናትነዋ ድቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ የዘረኝነትና የመለያየት ግንብ ፈርሶ ያለምንም የቆዳ ቀለም ልዩነት ሰዎች ሁሉ በነፃነት እና በእኩልነት መኖር ይችሉ ዘንድ ማንዴላ ለዲሞክራሲያዊ ሥረዓት፣ ለፍትህና ለነፃነት የከፈሉት መስዋዕትነት ማንዴላን በብዙዎች ልብ እንዲታሰቡና ከልብ በመነጨ ፍቅር ባወጁት የይቅርታ መንፈስም የደቡብ አፍሪካውያንና የዓለምን ህዝብ ወዳጅነትና ፍቅር ማግኘት ችለዋል፣ ከቂም በቀል ምን ትርፍ አለ- እርስ በርስ ከመጠፋፋትና ከመበላላት በስተቀር፡፡
በዚህ የማንዴላ የ93 ዓመት የልደት በዓል በተከበረበት ቀን ከኔልሰን ማንዴላ ጸረ አፓርታይድና ከመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት መራር ተጋድሎ ጋር የጠበቀ ታሪካዊ ትስስር ያላት ሀገራችን ኢትዮጵያን ዛሬ ያለችበትን ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ ሳስብ መቼ ይሆን በሀገራችን ለህዝብ መብት መከበር የሚሟገት፣ ለፍትህና ለነፃነት የሚቆም እንደ ማንዴላ የይቅርታና የፍቅር ልብ ያለው በሳል የፖለቲካ መሪን የምንታደለው በማለት ራሴን ጠየቅሁት፡፡ ይሄ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንገብጋቢ የወቅቱ ጥያቄ እንደሆነ እገመታለሁ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ጥናት ኮንፈረስ በተካሄደበት የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በዋናው ግቢ የኔልሰን ማንዴላ መንገድ መሰየሙን አሰታወሳለሁ ይሄ ይበል የሚያሰኝ ነው፣ ግና በዛ አንጋፋ የትምህርት ተቋም እንኳ፤ የማንዴላ መርህ የሆኑት ነፃነት፣ ፍትህ፣ መብትና እኩልነት ገና በሰማይ ላይ የተንጠለጠሉ የተሰፋ ዳቦዎች ናቸው፡፡ የሚበዙት ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን በኢህአዴግ የዘረኝነት ፖለቲካ ስር የሚማቅቁ፣ ተማሪዎቻቸውም እርስ በርሳቸው በብሔርና በዘር ተከፋፍለው በጎሪጥ የሚተያዩበት የጥላቻና የመለያየት ነጋሪት የሚጎሰምባቸው ተቋማት ወደመሆን ከተሸጋገሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ገና ከጠዋቱ በህዝቦች የፍትህና የዲሞክራሲ ጥያቄ የተነሳ የብዙ ወጣት ምሁራን ደም እንደ ውኃ የጎረፈበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለሰው ልጆች መብት መከበር፣ ለፍትህና ለሰላም መራር ትግል ባደረጉት በኔልሰን ማንዴላ ስም መንገድ ከመሰየም ባሻገር ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥረዓት ለሰው ልጆች ነፃነትና መብት የሚቆሙ ቆራጦች የሚወጡበት ይሆን ዘንድ ያሰፈልገዋል፡፡ ሀገራችን ወደተሻለ እድገትና ብልጽግና እንድትመጣ፣ ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ግንባር ቀደሙን ሚና መጫወት ያለባቸው የሀገራችን የትምህርት ተቋማት ከዘረኝነትና ከጎሳ ድንበር አልፈው የሚያስቡ የለውጥ ሐዋርያት የሆኑ ወጣት ሙሁራን ይወጡበት ዘንድ ነፃነት ሊታወጅላቸው ስፈልጋቸዋል፡፡
ረጅም እድሜ ለሰው ልጆች መብት መከበር፣ ለፍትህና እኩልነት ለሚታገሉ ሁሉ!
እግዝአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!