ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የንግዱ ማህበረሰብ ማዋከቡን ቀጥሏል፣ መርካቶ ውስጥ ከ450 በላይ ንግድ ቤቶች ታሸጉ

በአዲስ አበባ ከተማ ወረዳ አንድና ስምንት ውስጥ ከ450 በላይ የንግድ ቤቶች ያለንግድ ፈቃድ ሰርታችሁዋል በሚል ምክንያት መታሸጋቸውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዝን ኢሳት የውስጥ ምንጮቹን በመጥቀስ የዘገበ ሲሆን ዘረኛውና ጨካኙ የወያኔ አገዛዝ የወሰደው ርምጃ ነጋዴዎቹን እጂግ ማበሳጨቱን ተያይዞ የደረሰው ዜና አመልክቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ባሁኑ ሰአት በንግዱ ማህብረሰብ ከፍተኛ የሆነ ግብር በመጣልና እንዲሁም ለአባይ ግድብ ግንባታ ከፍተኛ ገንዘብ ካላዋጣችሁ በማለት ለከፍተኛ ምሬት እየዳረጋቸው መሆኑ ታውቋል:: ኢሳት ዘጋቢውን ዋቢ በማድረግ እንደገለጸው ቀድሞ 300 ብር ይከፍል የነበረ ነጋዴ በአሁኑ ሰአት ከ7 እስከ 8 ሺ ብር ክፈል እንደሚባል ታውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግብሩን የሚጥሉት የአገዛዙ ባለስልጣናት በዘር ሃረግ፣ በዘመድ አዝማድ፣ በድርጅት አባልነትና በመሳሰሉት የሚሰሩና ከፍተኛ የሆነ አድሎ እየፈጸሙ በመሆናቸው በህዝቡ ላይ በደልን ይፈጽማሉ በማለት ነጋዴዎች እንደሚናገሩ ኢሳት በዘገባው ላይ አክሎ ገልጿል።

የነጋዴው ማህበረሰብ ባሁኑ ሰአት እየተጣለበት ያለው ከአቅም በላይ የሆነ የግብር ጥያቄ እሮሮ በአዲስ አባባ ከተማ ብቻ ሳይሆን በመላ ሃገሪቱ በሚገኙት ሌሎችም ክልሎች እንደሆነ ታውቋል። በአማራ ክልል የሚገኙ ነጋዴዎች የክልሉ ባለስልጣናት ተገቢ ያልሆነ ግብር እየጣሉ ድርጅቶቻቸው እንዲዘጉ እንደሚያደርጉዋቸው በተደጋጋሚ ለኢሳት መግለጻቸውንም ዘገባው አመልክቷል።

እንደ ኢሳት ዘገባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጠላ የሚሸጡ አነስተኛ ነጋዴዎች ሳይቀሩ የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ በመጠየቃቸው ከፍተኛ የሆነ ትርምስ እንደተፈጠረ ነዋሪዎች እየተናገሩ መሆኑ ታውቋል::

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን በአዲስ አበባና ሌሎች ትላልቅ የክልል ከተሞች ተዘዋውሮ የተመለሰው ሪፖርተራችን ገልጾአል። እንደ ሪፖርተራችን ዘገባ የእህል ዋጋ ከአለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር እስከ 50 በመቶ ጭማሪ ከማሳየቱ ጋር ተያይዞ የህዝብ የመግዛት አቅም እጅግ እየወረደ መምጣቱና የወያኔ አባልና አጋር ድርጅቶች አባላት ሳይቀሩ በኑሮ ውድነቱ እየተማረሩ መምጣታቸው ታውቋል። የምግብ እህሎች የዋጋ ጭማሪ በተለይም በደሃው የህብረተሰብ ክፍል ላይ እጂግ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩንና ኑሮም ሰቆቃ እየሆነባቸው መምጣቱን ተያይዞ የደረሰን ዘገባ አመልክቶአል።

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በምርጫ 97 በህዝብ መተፋቱን ከተረዳ ቦኋላ በተለይም በዝረራ በተሸነፈበት የአዲስ አባባ እና አንዳንድ ትላልቅ የአገሪቱ ከተሞች ህዝብ ላይ የብቀላ እርመጃ በመውሰድ ሆን ብሎ ምሬትንና ጉስቁልናና እያስፋፋ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቶአል። በወቅቱ ለቅንጅት ድጋፋቸውን ሰጥተው የነበሩ የንግዱ ህብረተሰብ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግልጽ የሆነ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ ሲታወቅ ከገቢያቸው በላይ ግብር እንዲቆለልባቸውና የያዙትን የንግድ ድርጅት ማንቀሳቀስ ተስኖአቸው ከውድድር እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑ ብዙዎችን የመረረ ሃዘን ላይ ጥሎአል።