ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በማይደግፉት ዜጎች ላይ የሚያካሄደውን ዘርፈ ብዙ ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሏል

በሰሜን ኢትዮጵያ ከተሞች የሚኖሩና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ወይም ደጋፊዎች የሆኑ፤ እንዲሁም ወያኔን ለመቀላቀል ፈቃደኞች ያልሆኑ ዜጎች ዘርፈ ብዙ ጥቃት እየተካሄደባቸው እንዳለ የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአካባቢው ባደረሰን መረጃ ገልጿል።

በወልቃይት ጠገዴ፣ በዳንሻ፣ በሳንጃ፣ በጎንደር፣ በባህርዳር እና በመቀሌ የሚኖሩት ዜጎች በሰበብ አስባቡ ንብረታቸውን ከመወረስ አንስቶ በተፈበረከ ክስ ለእስር እስከመዳረግ፤ እንዲሁም ታፍነው የደረሱበት እስከማይታወቅበት ድረስ እየተጠቁ መሆኑን ዘጋቢያችን ያደረሰን መረጃ አሳይቷል።

በተለይም የመንግስት ሰራተኞች የሆኑት የጥቃቱ ሰለባዎች፤ ከበርካታ አመታት በፊት ህገ-ደንብ ጠብቀው የፈጸሙት የእቃ ግዢ ወይም የተቀበሉት የውሎ አበል በትክልል እንዳልተፈጸመ እየተነገራቸው እስር እየተፈረደባቸው ይገኛል።

በአርማጭሆ፣ በዳንሻ፣ በሳንጃና በጎንደር አካባቢ ደግሞ በስርአቱ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በአገዛዙ የጸጥታ አባላት እየታፈኑ ተወስደው የደረሱበት አለመታወቁ ቤተሰብ እና ዘመዶቻቸውን ማስጨነቁን ሪፖርተራችን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል። የተቀሩት የጥቃቱ ሰለባዎች ደግሞ ግብር አልከፈላችሁም በሚል ከጥቃቅን የንድግ ቁሳቁሶች አንስቶ እስከ ከፍተኛ ማምረቻ ድርጅቶች ድረስ እየተወረሰባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።