ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በአባይ ግድብ ግንባታ ሽፋን ዜጎችን መዝረፉን ቀጥሉአል፣ የግል ትመህርት ተቋማት በግዴታ የተጣለባቸውን ገንዘብ መክፈል አንችልም እያሉ ነው

የዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በውዴታ ግዴታ ገንዘብ እንዲለግሱ ከጠየቀ ወዲህ ፣ ተቋማቱም የተጣለባቸውን እዳ የከፈሉ ቢሆንም ዘራፊው የወያኔ አገዛዝ የከፈላቺሁት መጠኑ አነስተኛ ነው በሚል በድጋሚ እንዲያዋጡ ማዘዙን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ ገለጸ።

እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት የግል ተቋማቱ 30 ሚሊዮን ብር ማዋጣት እንዳለባቸው ዘራፍፊው አገዛዝ የግዴታ ትእዛዝ መስተላለፉ የታወቀ ሲሆን፣ ተቋማቱ ግን ይህን ያክል ገንዘብ ለመክፈል እንደማይችሉ ግልጽ በማድረጋቸው ውዝግብ የተፈጠረ ሲሆን ይህን የተነሳውን ውዝግብ በድርድር ለመፍታት በሚል ሽፋን በተደረገው ማስፈራራትና ዛቻ ተቁአማቱ ቀደም ብሎ በግድ እንዲከፍሉ የተጠየቁት የ30 ሚሊዮን ብር ወደ 20 ሚሊዮን ብር ዝቅ ሊል እንደቻለ ታውቁአል።

በዚህም ምክንያት በወንበዴው አገዛዝ የገንዘብ ክፍያ የግዴታ ጫና የተጣለባቸው የግል ትምህርት ተቋማት ይህን ገንዘብ ለማሙዋላት እየተተራመሱ እንደሚገኙ ተያይዞ የደረሰን ዘገባ አመልክቱአል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ተብሎ የሚዋጣው መዋጮ በህበረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታና ተቃውሞ እያስከተለ በመምጣቱ አገዛዙን እጅግ ስላሰጋው ያለውዴታ በግዴታ የወር ደመወዛቸውን እንዲለቁ ለተደረጉት መንግሥት ሠራተኞች የተወሰደባቸው ገንዘብ ወደ ቦንድ ግዢነት እንዲለወጣላቸው ማስታወቁን ዘግቦአል። የሚሊኒየም ግንባታ ተብዬው ቦርድ ሃላፊ ከሆነው በረከት ስምዖን ቢሮ የተሰጠውን ማስታወቂያ ዋቢ በማድረግ ዜናውን የዘገበው ኢሳት ፤ የዘረኛው አገዛዝ ላለፉት 3 ወራት የመንግስት ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን እንዲሰጡ ሲያስገድድ መቆየቱን አውስቶ ፣ ዜጎችን ያለውዴታቸው ማስገደዱ ከቀጠለ የህዝቡ ምሬት እየጨመረ አደጋውም የዚያን ያክል ከፍ ሊል ይችላል በሚል ስጋት መዋጮ የሚለውን ሀሳብ ለመሰረዝ እንደተገደደ ከአስተያየት ሰጪዎች መረጃ ማሰባሰቡን አክሎ ገልጹአል።

ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተፈጠረበትን ጫናና ውጥረት ያረግብልኛል በሚል በአዲስ ነጠላ ዜማነት የለቀቀው የአባይ ግድብ ዜማ የአንድ ሰሞን እስክስታ ብቻ ሆኑ መቅረቱና ኢትዮጵያዊያን የወያኔን ማዘናገያ በመገንዘባቸው ለግድብ ስራው ምንም አይነት ገንዘብ መክፈል እንደማይፈልጉ እየገለጹ መሆናቸውን ቀደም ብለን መዘገባችን አይዘነጋም።