የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ከተቃዋሚዎች ይወግናል በማለት የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ለአሜሪካ መንግሥት በማስረጃነት ያቀረበው ባለ 42 ገጽ አቤቱታ አፈትልኮ ለህዝብ ይፋ ሆነ
የህዝባችንን መረጃ የማግኘት መብት በማፈን የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም እየተወራጨ ያለው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ፤በቅርቡ ኢትዮጵያን ጎብኝቶ ለተመለሰው የአሜሪካ ድምጽ የአሰተዳደር ቦርድ ያቀረበው ባለ 42 ገጽ አቤቱታ ለህዝብ ይፋ መሆኑን የግንቦት 7 ዜና ዘጋቢ ገለጸ።
በወጣቱ የዲሞክራሲ አክቲቪስትና ጋዜጤኛ አበበ ገላው አማካይነት አዲስ ቮይስ በተባለው ድህረገጽ ላይ የወጣው ይህ 42 ገጽ የወያኔ አቤቱታ ፤ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የአማሪኛው ዝግጅት ክፍል እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከጃንዋሪ 13 አስከ ሜይ አሥራ አንድ 2011 ፤ወይም እንደ ኢትዮጵያዊን አቆጣጠር ከጥር እስከ ግንቦት 2003 ዓም ከተላለፉት ዝግጅቶች ውስጥ “ወያኔ ተቃዋሚዎቼ ናቸው” ካላቸው 31 ሰዎች ጋር የተደረጉ ቃለመጠይቆች ወይም አስተያየቶች ትራንስክሪፕት እንደሆነ ለማወቅ ተችሎአል።
ከአማሪኛ ወደ እንግሊዘኘ ተተርጉሞ ለአሜሪካ መንግሥት በቀረበው በዚህ 42 ገጽ ማስረጃ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች በአብዛኛው፤ በቱኒዚያና በግብጽ የተካሄዱ ህዝባዊ አብዮቶችን የቀሰቀሱ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በሙሉ በአገራችን ውስጥ መኖራቸውን የሚያመላክትና የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በቶሎ ማሻሻያ እርምጃዎችን ካልወሰደ በቀር በራሱ ላይ አደጋ እየጋበዘ መሆኑን ከማስጠንቀቅ ያለፈ መልዕክት እንደሌለው ታውቆአል።
በልማታዊ መንግሥትነት ሽፋን ሥም ዕድገትና መልካም አስተዳደር እያሰፈንኩ ነው በማለት ለ20 አመታት ሲደሰኩር የነበረው የመለስ በረከት አገዛዝ ፤ የህዝባችን የኑሮ ደረጃ ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ፤ ህዝባዊ ብሶቱ እየተጠናከረ በመምጣቱ ስለ ቱንዚያና የግብጽ አብዮት ማውራት አበው “በዶሮ ፊት ስለፈንግል በሽታ አይወራም” የሚሉት አይነት እየሆነበት መምጣቱን ይህ ለአሜሪካ መንግሥት ያስገባው አቤቱታ ይመሰክራል ብሎአል ዘጋቢያችን ።
የፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደርን በመወከል ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ የተመለሰው የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአስተዳደር ቦርድ ልዑካን ቡድን፤ ዘረኛው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የቪኦኤን ስርጭት ከማስተጓጎል የሚታቀብበትን መንገድ ለመሻትና በመስኩ ትብብር ለማስፋት አልሞ እንደነበር መገለጹ የሚታወስ ሲሆን ፤ በረከት ስምዖን ለልዑካኑ ቡድን ያቀረበውን “ተቃዋሚዎቻችንን ማስተናገድ አቁሙ” ጥያቄ ለህዝብ ይፋ ያደረጉ ባለሥልጣን ለትንሽ ጊዜ ከሥራ ገበታቸው ታግደው እንደነበረ መዘገቡ ይታወሳል። ሆኖም ኢትዮጵያዊያን ባሰሙት ተቃውሞና ባደረጉት ግፊት ሰውዬው ወደሥራ ገበታቸው የተመለሱ ቢሆንም የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል እራሱን በራሱ ሳንሱር እንዲያደርግ እየተፈጠረበት ያለውን የውስጥ ጫና ለመቃወም በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተጠናከረ ዘመቻ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሎአል። በዚህ የተቃውሞ ዘመቻ ኢትዮጵያዊያኑ ለአሜሪካ መንግሥት የህግ አውጭና ህግ አስፈጻሚ አካላት በሙሉ አቤቱታ ከማሳማት ጀምሮ አስፈአጊ ሆኖ ከተገኘ ጉዳዩን በህግ ፊት እስከማቅረብ የሚዘልቅ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸው ታውቆአል። ለህዝባቸውና ለአገራቸው ነጻነት የሚቆረቆሩ ኢትዮጵያዊያን ቪ ኦ ኤ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ያቀርብ የነበረውን በ እውነት ላይ የተመሰረተ ገለልተኛ መረጃ ለህዝባችን ማሰራጨቱን እንዲቀጥል ግፊት ለማድረግ የመጀመሪያቸው በሚሆን ይፋ እርምጃ የፊታችን ጁላይ 25 በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጽቤት ፊት ለፊት ታላቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጅተዋል።
ወያኔ ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ህዝባችን በከፍተኛ የረሃብ አለንጋ ውስጥ ሆኖ ህጻናትና አረጋዊያን እንደቅጠል መርገፍ በጀመሩበት በዚህን ሰዓት ሳይቀር ከውጪ ወደ አገር ቤት የሚተላለፈፉቱን የሬዲዮና የቴለቪዥን ስርጭቶችን በየዕለቱ በብዙ መቶ ሺ ዶላር የሚገመት ገንዘብ ወጪ በማድረግ መጥለፉን ቀጥሎበታል።
አንባቢዎቻችን በሰሜን አሜሪካ በዋሽንግተን ዲስና አካባቢዎ የሚትገኙ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጁላይ 25 ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጽ.ቤት ፊት ለፊት በተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በመገኘት ድርጊቱን እንዲታወግዙ የዝግጅት ክፍላችን የበኩሉን አገራዊ ጥሪ ያቀርብላችኋል።