የወያኔ የአባልነት ደብተርን በመቅደድ ነፃነትን ማወጅ፤ ዛሬ!!!

በዚህ ሳምንት ከወደ ሰሜን ሸዋ ባጭሩ እንዲህ የሚል መልካም ዜና ተሰምቷል።

በሰሜን ሸዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ የኢህአዴግን ስብሰባ አንሳተፍም ያሉ የኢህአዴግ አባላት የነበሩ መምህራን የ8 ቀናት ደመወዛቸው መቀጣታቸውና ከሐምሌ ወር ደመወዛቸው ተቀናሽ እንደሚሆን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሳቸው። መምህራኑ ለደብዳቤው በቃል የሰጡት ምላሽ

“ለወደፊቱም በኢህአዴግ ስብሰባ አንካፈልም፤ ራሳችንን ከአባልነት አግልለናል” የሚል ሆነ:: በዚህ ምላሽ የተበሳጩት የኢህአዴግ ባለሥልጣናት በስብሰባ የማይሳተፉና ከድርጅቱ የሚወጡ ከሆኑ ከሥራ እንደሚባረሩ ማስጠንቀቂያ ሰጧቸው። መምህራኑ ግን “የሚመጣውን ለመቀበል ተዘጋጅተናል”

አሉ።

ይህ ታላቅ ብሥራት ነው!!!

“ወይን-ለመኖር” የሚል ስላቃዊ ስያሜ የተሰጠው ለጥቅም ሲባል የወያኔ አባል መሆን፤ በገዛ ራስ ፈቃድ ባርነት መቀበል በመሆኑ ህሊና ያለው ዜጋ ሁሉ ሊዋጋው የሚገባ መሆኑን ከዚህ በፊትም ያነሳነው ጉዳይ ነው። “ወይን-ለመኖር” የኢትዮጵያን ህዝብ ያዋረደ፤ ለትውልድ የሚተርፍ የማኅበራዊ ስነልቦና ኪሳራ የሚያደርስ፤ ደካማውን ወያኔን ጠንካራ በማስመሰል የህዝባችንን የትግል ሃሞት የሚያፈስ እኩይ ተግባር ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ በወያኔ አባልነቱ የሚያገኘው ጥቅም “ራሱን ለባርነት የሸጠበት ዋጋ ነው” ከማለት ሌላ ምን ትርጉም ይሰጠዋል?

የሰሜን ሸዋ መምህራን “በወይን-ለመኖር” ላይ የመጀመሪያን ህዝባዊ ጡጫ በማሳረፋችሁ “እንኳን ደስ ያላችሁ!!!” እንላችኋለን። ኮርተንባችኋል!!!

እንደሚታወቀው “በወይን-ለኑሮ” ዘይቤ ራሱን እያታለለ ወያኔን የተቀላቀለ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከሚከተሉት ቢያንስ በአንዱ መንገድ መተባበሩ አይቀርም።

1. በስለላ መተባበር

የወያኔ ድርጅቶች የስለላ ተቋማት ናቸው። የወያኔ አባላት እርስ በእርሳቸው፣ ጎረቤቶቻቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸውን እንዲሰልሉ ይደረጋል። የወያኔ አባል መሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዚህ አጸያፊ ተግባር መሳተፍ ማለት ነው።

2. በዝርፊያ መተባበር

ለትናንሽ ጥቅሞች ተብሎ የወያኔ አባል በተሆነ ቁጥር ወያኔ የዝርፊያውን አድማስ ያሰፋል። በትንሹ እንኳን የጥቅም ተካፋይ የሆነ ሰው ትልቁን ዘረፋ የመቃወም የሞራል ብቃት አይኖረውም ። በዚህ የተበረታታው የወያኔ ዘረፋ እየሰፋ መጥቶ እነሆ የእርሻ መሬቶችን ለባእዳን ቱጃሮች እስከ መሸጥ ደርሷል።

3. በዝምታ መተባበር

የወያኔ ድርጅቶች በራሳቸው አባላትም በህዝብም ልብ ውስጥ ፍርሃትን የሚረጩ መርዞች ናቸው። በፍርሃት ሳቢያ በርካታ ዜጎቻችን ያዩትን እንዳላዩ፤ የሰሙትን እንዳልሰሙ ማለፍን ለምደዋል። በዚህም ምክንያት አድርባይነትና እኖርባይነት በአስደንጋጭ ፍጥነት እየተስፋፉ ናቸው። ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ስነልቦና በተላበሱ ዜጎች ልትገነባ አትችልም።

ከዚህ አዋራጅ ስነ-ልቦና የምንወጣበትን መንገድ የሰሜን ሸዋ መምህራን አሳይተውናል። መምህራኑ “ለጥቅም ወይም በፍርሃት ምክንያት የወያኔ አባል በመሆን ባርነትን አንቀበልም” ብለዋል። የወያኔን የአባልነት ደብተር በመወርወር ነፃነታቸውን ተቀዳጅተዋል። ይህ ነው እያንዳንዱ ህሊና ያለው የወያኔ አባል ሊያደርገው የሚገባ ተግባር።

ዛሬ ይህንን ታላቅ እርምጃ ደፍረው የወሰዱ ጥቂቶች ናቸው፤ ነገ ግን በየአደባባዩ የሚታይ ትዕይንት ይሆናል። በሊቢያ የጋዳፊን “አረንጓዴ መጽሃፍ” መቅደድ፣ መረጋገጥና ማቃጠል የምሬት መግለጫ እንደሆነ ሁሉ እኛም ዘንድ የወያኔ ኢህአዴግ የአባልነት ደብተሮች፣ ፎርሞችና ወረቀቶች በአደባባይ የሚቃጠሉበት ጊዜ እሩቅ አይደለም። ቀድመው ያደረጉት ግን ጀግኖች ናቸው።

እናም ልቦና ያላችሁ የወያኔ አባላት ዛሬ የአባልነት ደብተሮቻችሁን ቅደዱ!!! ይህንን በማድረግ ከህሊናችሁ መታረቅ እና ራሳችሁን ከባርነት ማላቀቅ ትችላላችሁ። ይህንን ተግባር ዛሬ ስትፈጽሙት ጀግኖች ናችሁ፤ ነገ ግን ተራ ነገር ይሆናል። ከጥቂት ጊዚያት በኋላ በይፋ መቀደዱ የማይቀርን ወረቀት በመቅደድ ለራሳችሁ ታሪክ ስሩ።

በዚህ አጋጣሚም “የወያኔ የአባልነት ፎርም አንሞላም” በማለት ከክልሉ የወያኔ ሹማምንት ጋር ተፋጠው ላሉት የትግራይ መምህራን ያለንን አክብሮት እንገልፃለን።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለእንዲህ ዓይነቱ ለመብትና ለነጻነት ለሚወሰዱ እርምጃዎች ትልቅ ዋጋ የሚሰጥ መሆኑን፤ ይህንንም ለሚያደርጉ ወገኖች ከፍተኛ ክብር እንዳለው እና እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን በቅርበት የሚከታተል መሆኑን ያሳውቃል።

በወያኔ አባልነት ስም የዜጎች ባርነት ይብቃ!

በቃ!!! ጋዬ!!! ይአከል!!! አሎኒ!!! ዲታህ!!! ወጣንደም!!! በስ!!! ጊዴስ!!!