ኑሮ በካንጋሮ ምድር(፪)

በአበሾቹ መንደር ፉት ስክሬይ በአንዱ የሐበሻ ሆቴል ቁጭ ብዬ አንድ ወገን ወደ እኔ መጣ፡፡ መጥቶም አልቀረ ወንበር ሳበና ቁጭ አለ፡፡
‹‹ዐውቅሃለሁ መሰል››
‹‹ይሆናል፣ የሰው መተዋወቂያው ብዙ ነው›› አልኩት፡፡
‹‹ዳንኤል ነህ አይደል›› አለኝ፡፡ አረጋገጥኩለት፡፡ እኔ በቀን አራት ጊዜ የሚፈራረቀው የሜልበርን አየር አልገባኝ ብሏል እርሱ ጃቦኒ ነው ያደረገው፡፡ ራሱን አስተዋወቀኝ፡፡ መጽሐፎቼን ማንበቡን ነገረኝ፡፡ መቼም በውጭ ሀገር ሰማሁ የሚል እንጂ አየሁ፣ እገሌ ነገረኝ የሚል እንጂ አነበብኩ የሚል ሰው ማግኘት ዋድላና ደላንታ ሄዶ ኦራል እንደማግኘት ብርቅ ነው፡፡ አመሰገንኩት፡፡
‹‹እንግሊዝኛ ብችል ኖሮ አንዳንዱን ጽሑፍ እተረጉመው ነበር›› አለኝ እየሳቀ፡፡
‹‹ታድያ ምን ችግር አለው፡፡ አውስትራልያ የእንግሊዝኛ ሀገር ናት፡፡ ተርጉመው›› አልኩት፡፡
‹‹እንደመጣሁ ቋንቋ ትምህርት ቤት ገብቼ ነበር፡፡ ለስደተኞች የሚሰጥ ኮርስ ስላለ ለመውሰድ፡፡ እንግሊዝኛና ብስክሌት በልጅነት ካልጀመሩት ጉድ ይሠራል››
ሳቅኩና ‹‹እንዴት?›› አልኩት››

‹‹ሞከርኩትና ቋንቋውን ትቼ ፈገግታውን ብቻ ተምሬው ወጣሁ›› አለኝ፡፡
‹‹የትኛውን ፈገግታ?››
‹‹አለች የእነርሱ ፈገግታ፤ እንደ ፍሬቻ ብልጭ ድርግም የሚያደርጓት፡፡ ቢገባህም ባይገባህም ከሳቅክ ፈረንጅ ደስ ይለዋል፡፡ ታድያ ሥራ ስገባ ቢገባኝም ባይገባኝም ሳቅ ስል ከአፍንጫ በታች ከአገጭ በላይ በሆነ ፈገግታ ያጅቡኝ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ሥራዬን ከሠራሁ የእነርሱ እንግሊዝኛ ቢገባኝ ባይገባኝ ብዬ ተውኩላቸው፡፡ አንድ ቀን ግን ጉድ ሆንኩ፡፡›› ጉጉቴ ከሳቅ ጋር ጨመረ፡፡
‹‹አንድ አብሮኝ የሚሠራ ልጅ አለ፡፡ በጉሮሮ እንግሊዝኛው ሲያወራኝ ስቄ ነበር የማሳልፈው፡፡ ‹እንግሊዝኛንና ስደትን ስቆ ማሳለፍ ነው› የሚል ጓደኛ ነበረኝ፡፡ ታድያ አንድ ቀን ሥራ እየሠራን የሆነ ነገር ያወራኛል፡፡ ልብ አልሰጠሁትም፡፡ ሲጨርስ ቀና ብዬ በፈገግታ ሳየው ተናደደ፡፡ በማውቃት እንግሊዝኛ ‹‹ምን ሆንክ›› አልኩት፡፡ ‹‹እንዴት እናቴ ትናንት ሞተች ስልህ ትስቃለህ›› አይለኝም፡፡ እኔ ራሴ ደነገጥኩ፡፡ ቀዥቃዣ ፈረንጅ፤ እናቱ ሞታ እስኪ ከፍራሽ አስነሥቶ ሠለስት እንኳን ሳይደርስ ምን ያመጣዋል፡፡ እኛ ድሮ የተማርነውን ሁሉ አጣመው አጣመው ድምጻቸው ሊያዝልኝ አልቻለም፡፡ አሁን ሲገባኝ ግን እነርሱ የጉሮሮ እኛ የከንፈር እንግሊዝኛ ነው የተማርነው፡፡››
‹‹ደግሞ እንግሊዝኛ የከንፈርና የጉሮሮ የሚባል አለው?››
‹‹ታድያስ፡፡ እስኪ ስማቸው፡፡ እኛ ‹ዋተር› ብለን ረገጥ አድርገን ስንጠራ እነርሱ ‹ዋር› ብለው በአየር ላይ ያልፉታል፡፡ እኛ ‹ገርል› እየተባልን ጫን ብለን ስንናገር እነርሱ ‹ገ – ል› ብለው በስሱ ያቆላምጧታል፡፡› አሁን ያለን አማራጭ በአማርኛ እያለቀስን በእንግሊዝኛ መሳቅ ነው፡፡›› እኔ ግን በአማርኛ ሳቅኩ፡፡
‹‹ለምን ትምህርት ቤት አልሄድክም(ውጭ ‹አልገባህም› አይባልም) እዚያ የግድ ከቋንቋው ተናጋሪዎች ጋር ስትቀላቀል ትለምደው ነበር››
‹‹ድመት ጅራቷ የተቆረጠበት ቦታ ተመልሳ አትሄድም› ሲባል ሰምተሃል፡፡ እኛም መቀመጫችንን (እርሱ ሌላ ነበር ያለው) የተገረፍንበት ስለሆነ ነው መሰል ወጣ ስትል እዚያ አይመራህም፡፡ እንጂ እዚህ ሀገርማ ብትማር ብዙ ይረዱሃል፡፡ አየህ ድሮ እንማር የነበረው ለእንጀራ ነበር፡፡ እዚህ መጥተን ሳንማር እንጀራ አገኘን፡፡ ታድያ ለምን እንማራለን? ደግሞ በየስደተኛው ካምፕ ፀጉራችንንና ልባችንን ጨርሰን መጥተን ነው መሰል እዚህ ሀገር ማስታወስ የሚባል ነገር የለም፡፡ ቶሎ ትረሳለህ፡፡ 
‹‹ምን ያህል ጊዜ ቆየህ አውስትራልያ››
‹‹በሃሳብ ዘጠኝ ዓመት፣ በአካል አሥራ ስድስት ዓመት›› አለመረዳቴን ለመግለጥ አንገቴን ሊወድቅ እንደተዘጋጀ ብርጭቆ አወዛወዝኩ፡፡

‹‹ሱዳን ነበርኩ፡፡ ሱዳን ዘጠኝ ዓመት ቆየሁ፡፡ እዚያ እያለሁ በተስፋ አውስትራልያ ነበርኩ፡፡ ነገ ትሄዳላችሁ፣ አልቋል፤ ተጠናቋል፤ ፎርም ሙሉ፤ ተዘጋጁ፤ አሻራ ስጡ፤ ፎቶ ተነሡ ስንባል ዘጠኟን ዓመት ጠጣናት፡፡ እኛስ ይሁን በልጅነታችን ወጥተን ነው፡፡ አረጋውያን አባቶች ነበሩ እዚያ፡፡ ስደትና እብደት ካረጁ በኋላ አያምርም፡፡ የአብርሃም ቤት አዛውንቶች ሲባል ሰምተሃል?››
‹‹አልሰማሁም›› አልኩት፡፡
ቀጠለ፡፡ ‹‹እነዚህ አዛውንቶች ከ1966 ዓም ጀምሮ በኢዲዩ፣ በከፋኝ፣ በምናምን እየተደራጁ ሲዋጉ የኖሩ ናቸው፡፡ በኋላ ግን ሁሉም ነገር አልሆን አላቸው፡፡ አረጁ፡፡ መጀመሪያ በተለያዩ ቦታዎች፤ በኋላ ደግሞ አብዱል ረከም በሚባል የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ከሃያ ዓመታት በላይ በሱዳን አሳለፉ፡፡ በመጨረሻም ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ወደ 350 የሚጠጉ አዛውንቶች አውስትራልያ መጡ፡፡ መንግሥት ጡረታ ይሰጣቸዋል፡፡ ቋንቋው ግን መከራ ያሳያቸዋል፡፡ ቤት የመጣ ፖስታ ለማንበብ፣ ከማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች ጋር ለመግባባት ችግር አለ፡፡ አውስትራልያ ብር እንጂ ቋንቋ አትረዳ፡፡
የዘመድ ሰላምታ ሲመጣ ደብዳቤ
አንብቡልኝ ብዬ ለሰው አስነብቤ – የሚል ዘፈን ትዝ ይልሃል (በዜማ ነው ያለልኝ) እዚህ ተወዳጅ ዜማ ነው፡፡››
‹‹እዚህ ሀገር ከሱዳን የመጡ ይበዛሉ ልበል፡፡››
‹‹ልክ ነህ፤ በተለይ በኢሕአፓና በኢዲዩ ጊዜ ወጥተው፤አሥርና ሃያ ዓመት ሱዳን ኖረው የመጡ ናቸው አብዛኞቹ፡፡ ያልተቀየጠ ንጹሕ የኢሕአፓ ዘር እዚህኮ ነው ያለው፡፡ ጓድ ሲባባሉ ትሰማቸዋለህ፡፡ 
‹‹ ለመሆኑ ግን ከወጣህ በኋላ ወደ ሀገር ተመልሰህ ታውቃለህ?››
‹‹አንድ ጊዜ ብቻ››
‹‹ምነው፤ ጥፊም ይደገማል ይባል የለ እንዴ››
‹‹ታክሲ ነጅ ከሆንክ መደጋገምህ አይቀርም››
ታክሲው አያደርሳቸው››
‹‹ትርፊክ እየጣስክ ትነዳ ትነዳና ነጥብ ትሰበስባለህ፤ ከዚያ ወደ ዘጠኝ አካባቢ ስትደርስ መንጃ ፍቃድህን ነጥቀው እንዳትነዳ ይሉሃል፡፡ እዚህ ሀገር እንዴት ትዘልቀዋለህ፡፡ ሀገር የናፈቀህ መስለህ ኢትዮጵያ ትሄድና አንድ ሦስት ወሯን ቅጣት እዚያ ታሳልፋታለህ፡፡ ‹ለዕረፍት የመጣ ፍቅር›› በሚለው ፋንታ ‹ለዕረፍት የመጣ ሾፌር›› የሚል ፊልም ሠርተህ ትመለሳለህ፡፡››
ቢሆንም አገር አይደል››
‹‹ወዳጄ ሀገር ቤት ደርሶ የመጣና ቤቱ የተቃጠለበት አንድ ነው››
‹‹እንዴት››
‹‹ሙልጭህን ነዋ የምትቀረው፡፡ እዚያ ዝንጥ እያለ የምታየው ዳያስጶራ ሁሉ ከሀገሩ ሲመለስ ስልክ አያነሣ፣ ከሰው አይገናኝ፣ ኢሜይል አይከፍት፤ ይመንናል፡፡ ከሆስፒታል መውጣት በለው፡፡ በተለይ ኢምፖርት ሊያደርጉ የሚሄዱትማ››
‹‹ምንድን ነው ኢምፖርት የሚያደርጉት››
(ይቀጥላል)
ካሮላይን ስፕሪንግስ፣ ሜልበርን፣ አውስትራልያ