ህወሃት በትግራይ ህዝብና በመላው አገራችን ላይ የፈጸመውን ክህደት ለህዝብ ንባብ ያበቁ የቀድሞ ታጋይ እና አመራር አባል አቶ አስገደ ገብረስላሴ ትግራይ ውስጥ የቁም እስረኛ ሆኑ
ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ቀደም ሲል የጫካ ትግል ያካሂድ በነበረበት ወቅት አብረውት የነበሩትንና የድርጅቱን ጸረ አገርና ጸረ ህዝብ አቋም በሚገባ ከተረዱ ቦኋላ ለቀው በመውጣት ከተቃውሞው ጎራ የተሰለፉትን የቀድሞ ታጋዮች ማሳደዱን በመቀጠል አቶ አስገደ ገብረስላሴ በተከታታይ ለንባብ ባበቁአቸው መጻህፍት ምክንያት የቁም እስረኛ እንዳደረጋቸው ከስፍራው የደረሰን ዘገባ አመለከተ:: እንደ መረጃ ምንጮቻችን ዘገባ አቶ አስገደ ለዚህ የቁም እስር የበቁት ቀደም ብሎ ገሀዲ ቁጥር 1 ቁጥር 2 እና ቁጥር 3 በሚባሉት መጽሀፋቶቻቸው ሲሆን አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ክሱ የቀረበባቸው አሜሪካ አገር በሚኖር ብስራት አማረ በሚባል የህወሀት የደህንንት አባል መሆኑንም ተያይዞ የደረሰን ዜና አመልክቱአል።
እንደዜና ምንጮቻችን ሪፖርት አቶ አስገደ በመጽሀፋቸው የዚህን የደህንነት አባል ታሪክና የሰራቸውን እኩይ ስራዎች በገሀዲ ቁጥር ሶስት ዘርዝረው ያቀረቡ ሲሆን መጽሀፉ ህወሀትንና ህወሀትን ሲመሩ የነበሩ ሰዎችን ታሪክ የሚያቀርብ፣ ይዘቱም በህወሀት ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ መደናገጥ የፈጠረ ነው ተብሉአል።
የዜና ምንጮቻችን አክለውም የህወሀት ባለስልጣናት በቅርቡ “የ ገሀዲን ጎርፍን በምን እናግደው” በሚል አጀንዳ ተሰብስበው እንደነበርና አስገደን እንክሰሰው ወይንስ አንክሰሰው በሚል ጭቅጭቅ ላይ ሰንብተው እንደነበርና “ጸሀፊውን በህወሀት ደረጃ እንክሰስ፣ ህወሀት ክሱን ይመስርት” የሚል ሀሳብ የቀረበ ቢሆንም “እንደዚያ ማድረጉ ለመጽሀፉና ለጸሀፊው ትልቅ እውቅና የሚሰጥ ነው” በማለት የተቃወሙም እንደነበሩ ተመልክቱአል።
እንደዘገባ ምንጮቻችን ሪፖርት የትግራይ ፖሊስ አቶ አስገደን ለአንድ ቀን ይዞ ካሰረ በሁዋላ በሶስት ሺ ብር ዋስትና የለቀቃቸው የታወቀ ሲሆን፣ ከመቀሌ ከተማ እንዳይወጡ በማዘዝም የቁም እስረኛ አድርጓቸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት አቶ አስገደን በስልክ በማነጋገር መጽሀፉ የህወሀት ሰዎችን በከፍተኛ ደረጃ ያስደነገጠና በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ በመሆኑ አሁን በቁም እስር ላይ እንደሚገኙና መቼ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ እንደማያውቁ መናገራቸውን ዘግቡአል።
የአረና ትግራይ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አስገደ በቅርቡ የኢፈርት ኩባንያዎች የጥቂት ግለሰቦች መበልጸጊያ እንጅ የትግራይ ህዝብ ንብረቶች አይደሉም በማለት መናገራቸው ይታወሳል።