ኢሕአዴግ በዜጐች ላይ ሽብር እየነዛ ነው ሲል መድረክ ወነጀለ (ሪፖርተር)

የኢሕአዴግ መንግሥት በዜጐች ላይ ሽብር በመንዛት ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አስታወቀ፡፡ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመፍጠርና ሥልጣን ላይ በመቆየት ሐሳብ ላይ ግራ የተጋባ መሆኑን ዶ/ር መራራ ጉዲና ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

“በዜጐች ላይ ሽብር በመንዛት ሽብርተኝነትን ማስወገድ አይቻልም” በሚል ርዕስ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ መድረክ እንደገለጸው፣ ኢሕአዴግ “ሽብርን በመንዛት” ፍረጃ በመጠቀምና ዜጐችን “የዚህና የዚያ ሕገወጥ ድርጅት አባልና ደጋፊዎች ናችሁ፣ ወዘተ” በማለት የዜግነት መብትና ክብርን የሚገረስሱና የሚያዋርዱ ዕርምጃዎችን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሲወስድ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥታዊ ሥርዓት የዘመናዊ መንግሥታዊ ሥርዓት ተሞክሮ ሚዛንን የማያሟላ መሆኑን የገለጸው መድረክ፣ በገዥው ፓርቲ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እምነት ማጣቱን አውቆ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ሕጐችን የራሱ አባላት ስብስብ በሆነው ፓርላማ የአንድ ቀን ውሎው እያሳወጀ፣ ሕዝቡን እንደ ምርኮ ይዞ በማስፈራራት መግዛቱን አማራጭ ብሎ የያዘ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከእነዚህ ነውጠኛ ሕጐች መካከልም ገሚሶቹ ለጥቃት ኢላማ የተደረገን አንድ ወገን ታሳቢ ያደረጉና “ተለክተው የሚሰፉ” ዓይነቶች እንደሚገኙባቸው መግለጫው ይጠቅሳል፡፡

“የዚህና የዚያ ድርጅት አባላት ወይም ደጋፊዎች በማለት በቂ ማስረጃ ሳይያዝ እያሰሩ ማሰቃየትና ከቤት ኑሯቸው በማፈናቀል ቤተሰቦቻቸውን ለኑሮ ቀውስ መዳረግ በዜግነት ክብር ላይ የተቃጣ ዕርምጃ ከመሆን አያመልጥም” ያለው ድርጅቱ፣ በአሁኑ ጊዜ በሕገወጥ እስራት እየማቀቁ ያሉት የመድረክ አባል የሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ንቅናቄ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ብርሃኑ እምሩና የዚሁ ድርጅት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት የአቶ መለስ ጫላ ጉዳይ በእጅጉ እንደሚያሳስበው አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ነዋሪ የሆነውና በእስር ቤት በደረሰበት ግርፋትና እንግልት የአዕምሮ ሕመመተኛ የሆነው የአቶ ግዛቸው አብዲሳ፣ በደቡብ ጐንደር የወረታ ከተማ ነዋሪና የአንድነት ፓርቲ አባል በሆነው አቶ ሙላቱ አበባው ላይ የደረሰው ድብደባና በበርካታ የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ አባላት ላይ እየደረሰ ያለው በአካል ላይ ጉዳት የሚያደርስ እጅግ ዘግናኝና አሰቃቂ ድብደባ ጉዳይም በእጅጉ እንደሚያሳስበው መድረክ አክሎ ገልጿል፡፡

ኢንተርኔትን በመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች የሚደረጉ ይፋ ግንኙነቶችን ያደረጉ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሳይቀር በሽብር ፈጣሪነት በመፈረጅ ወንጅሎ ማንገላታት በደርግ ዘመነ መንግሥት “የዚህን ወይም የዚያን በራሪ ወረቀት አንብባችኋል” እየተባለ የአገሪቱን ምስኪን ዜጐች ፍዳቸውን ያዩበትን ወቅት የሚያስታውስ መሆኑን በመግለጫው ላይ የጠቆመው መድረክ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ለዜጐች ከተሰጡት መብቶች ጋር የሚጣረሱ ሕጐችን ዘወትር እየጐነጐነ ሕዝብን በፍርኃት ሸብቦ መግዛት በዘላቂነት እንደማይችል ተገንዝቦ፣ በፀረ ሽብርተኝነት ስም በየእስር ቤቱ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ውጭ ያሰራቸውን ዜጐች በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቋል፡፡

የመድረክ አመራር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ለሪፖርተር እንደገለጹት ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመፍጠርና ሥልጣን ላይ በመቆየት መካከል ግራ በመጋባቱ አገሪቱን መምራት አቅቶታል፡፡

ኢሕአዴግ ለሰላሳና ለአርባ ዓመታት የመምራት ሕልም ያለው በመሆኑ አገሪቱን ፍፁማዊ ወደሆነ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ እያመራች መሆኑን የገለጹት ዶ/ር መረራ፣ አገሪቱ በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ሥርዓት በመውደቋ ምክንያትም ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ሕይወት አልባ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

“አፈናው እየተስፋፋ ነው፤ በፍርድ ቤቶች የሚታዩ ነገሮች ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ እየተፈጠረች ነው ለማለት አያስደፍርም፤” ያሉት ዶ/ር መራራ፣ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ላይ ተግባራዊ የተደረገው የፀረ ሽብር ሕግም በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱትንና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ዜጐችን ለማፈን ጥቅም ላይ መዋሉን ይገልጻሉ፡፡