ፔትሮናስ የተባለው የማእድን አውጪ ኩባንያ በኦጋዴን ሲያካሄድ የቆየው አሰሳ እጣ ፈንታ አነጋጋሪ ሆኗል

የዛሬ ሁለት ወራት ገደማ ለወያኔ አገዛዝ ቅርበት ያለው ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ፔትሮናስ የተባለው የነዳጅ ቁፋሮ ቡድን በኦጋዴን የሚያካሄደውን ስራ ከጸጥታ ጉዳይ የተነሳ አቁሞ እየወጣ እንደሆነ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ የማእድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለስልጣን ጉዳዩን ተራ ወሬ ብሎ አጣጥሎታል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሃላፊ አለማየሁ ተገኑ ሐሙስ እለት ለሬውተርስ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ፔትሮናስ ስራውን እንዳቆመ አምኖ፤ ያን ያደረገው ግን ከዚህ በፊት ያካሄደውን ስራ ውጤት ለመመርመር ነው ብሏል።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ወይም ኦብነግ) በአካባቢው በተደጋጋሚ ጥቃት በማድረሱ እና የሂላላ የጋስ አሰሳ መስክን በመቆጣጠሩ ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተነሳ ፔትሮናስ አካባቢውን ለቆ የመውጣቱ ወሬ በተለያዩ ሚድያዎች መነገር ከጀመረ ሁለት ወራት አልፈውታል። ይሁን እንጂ ፔትሮናስ እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ቃሉን አልሰጠም፤ ሪፖርተር ጋዜጣ እና ብሉምበርግ የዜና አገልግሎት ከኩባንያው መልስ ለማግኘት ያደረጓቸው ሙከራዎችም አልተሳኩም።

ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየት የሰጡ የፖለቲካ ተንታኝ፥ የኩባንያው ዝምታ ጉዳዩን የበለጠ አጠራጣሪ አድርጎታል ብለዋል። ጨምረውም፥ የአገዛዙ ባለስልጣናት በአንድ በኩል ኩባንያው እስካሁን እያደረገ የነበረውን አሰሳ ለመመርመር ስራ ማቆሙን እየነገሩን፤ በሌላ ጎን ደግሞ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ ጋስ ወደ ውጭ አገር መላክ እንደሚጀምር በርግጠኛነት መናገራቸው እርስ በርሱ እንደሚጣረስ አስረድተዋል። ይህም አጠቃላይ ሁኔታውን በጥርጣሬ እንደሞላው አስተያየታቸውን ገልጸዋል።