አትሌት ኃይሌ የለንደን ኦሊምፒክ ማራቶንን ካሸነፈ ሽልማቱን ለገዳም እንደሚሰጥ ቃል ገባ
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ገዳሙን የጎበኘው ኃይሌ በገዳሙና በገዳሙ ቅርሶች እጅግ ተደምሟል፡፡ በተለይ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በገዳሙ የተቀበሩ አስከሬኖች ሳይበሰብሱና ሳይፈርሱ መቀመጣቸው አስገርሞታል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ያልተጎበኙ ቦታዎች አሉ፡፡ በዚህ ገዳም ለብዙ ዓመታት ሳይፈርሱ የተቀመጡ አስከሬኖች ይገኛሉ፡፡ ይህ ከሳይንቲስቶች ምላሽ ያልተገኘለት ነው፡፡ እኔ እጅግ ደንቆኛል፤ በማለት በገዳሙ መደነቁን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
የአቡነ መልከ ጸዴቅ ገዳም በዞኑ ሚዳ ወረሞ ወረዳ ውስጥ ስራቲ ቀበሌ ይገኛል፡፡ የቦታው አቀማመጥ እጅግ ተራራማና በግዙፍ ቋጥኞች የተከበበ ሲሆን፣ ገዳሙም የሚገኘው በተራራማ ቋጥኝ ሥር በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ነው፡፡
ሪፖርተርም ማየት እንደቻለው በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ አስከሬኖች አልፈረሱም፡፡ አፈር አልበላቸውም፡፡ ኃይሌም ሁኔታው አስደንቆት ለንደን ማራቶን ላይ ካሸነፈ ለገዳሙ ወርቁን እንደሚያበረክት ቃል ገብቷል፡፡
የዚህ ጥንታዊ ገዳም ቤተክርስቲያን በአሁኑ ወቅት ሕንፃው ከእርጅና ብዛት ፈርሶ በአዲስ መልክ እየተገነባ ነው፡፡ ይሁንና የተሠራበት የኮንስትራክሽን ግብዓት ጥንታዊነቱን የሚያንፀባርቅ ሳይሆን የአሁኑን ዘመን ጥበብ የተላበሰ ነው፡፡
ባለሙያዎች፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በጉዳዩ ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለበትና በተቻለ መጠን የጥንቱን ይዘት ባልለቀቀ መልኩ መሠራት እንደሚኖርበት ይጠቁማሉ፡፡
በውድነህ ዘነበ