ከነገሌ ቦረና እስከ ባር ዱባይ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮን በሚፃረረው ኑፋቄው የሚታወቀው ዲ/ን ኀይሉ ምስጋናው ከዐውደ ምሕረት አገልግሎት ታገደ!

  • የርምጃውን ጅምር የወሰደው አ/አ መካነ ሰማዕት ቅ/ቂርቆስ ደብር ሰበካ ጉባኤ ነው፡፡
  • የደብሩ የስብከተ ወንጌል ክፍል ጥብቅ ክትትል እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል፡፡
  • ለሰ/ጉባኤው የእግድ ውሳኔ ዝርዝር መረጃ የሰጠው የደብሩ ሰንበት ት/ቤት ነው፡፡
  • ሰንበት ት/ቤቱ ከአምስት ዓመት በፊት ከመናፍቃን ኅትመቶች ገልብጦ ባዘጋጀው በራሪ ወረቀት ምክንያት ከማንኛውም አገልግሎት አግዶ ክትትልና ማጣራት ሲያደርግበት ቆይቷል፡፡
  • ዲ/ን ኀይሉ በነገሌ ቦረና የሀ/ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊ ኾኖ በሚሠራበት ወቅት የፕሮቴስታንታዊውን ‹‹ቃለ ሕይወት›› መጽሔቶችና ካሴቶች ሲያሰራጭ ተደርሶበት ከሀ/ስብከቱ የተባረረ ነው፡፡
  • ከነገሌ ቦረና በኑፋቄ ተግባር ከተባረረ በኋላ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል መምሪያ በተዘዋዋሪ ሰባኪነት ለመቀጠር ሲጠይቅ መቆየቱ ተዘግቧል፡፡
  • የደብረ ፍሥሓ መካነ ሰማዕት ቅ/ቂርቆስ ሰበካ ጉባኤና ሰንበት ት/ቤት በዲ/ን ኀይሉ ምስጋናው ላይ የተላለፈውን እገዳ ከክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጀምሮ ለሚመለከታቸው የበላይ አካላት የማሳወቅ ሥራ እየሠመኾኑ ተገልጧል፡፡
  • በአሁኑ ወቅት ግለሰቡ በግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው ከተወገዙት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ከኾኑ 16 ግለሰቦች መካከል አንዱ በኾነው አሸናፊ መኰንን ቤት ክሕደቱን በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡
  • በዋናነት ኦርቶዶክሳዊውን የነገረ ድኅነት አስተምህሮ በሚፃረረው ኑፋቄው በሚታወቀው ኀይሉ ምስጋናው ላይ ለተወሰደው ርምጃ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር፣ የሰንበት ት/ቤቱ አመራርና የአጥቢያው ምእመናን ያደረጉት መቀናጀት ሕገ ወጥ ቡድኖችና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኞች ለአህጉረ ስብከት መዋቅራዊ አሠራርና ለሚመሯቸው ሊቃነ ጳጳሳት መመሪያ ባለመገዛት ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ በሚገኙባቸው በነገሌ ቦረናና በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች በባር ዱባይ ለሚገኙ ምእመናን ትልቅ አብነት ነው፡፡

ዲ/ን ኀይሉ ምስጋናው በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ደብረ ፍሥሓ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን የማታው የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ላይ ያስተላለፈው ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ው የኾነ ኑፋቄ ዋና ዋና ነጥቦችና የደብሩ ሰበካ ጉባኤ የእገዳ ውሳኔውን ያስታወቀበት ደብዳቤ

ቁጥር፡- ቂ/ሠ10/040/05

                                 ቀን፡- 03/12/05          

ለደብሩ ስብከተ ወንጌል ክፍል

አዲስ አበባ

 

ጉዳዩ፡- ዘወትር ሰኞ በማታው መርሐ ግብር ትምህርት እየሰጡ የሚገኙትን ዲ/ን ኀይሉ ምስጋናውን ይመለከታል

ከላይ በርእሱ ለመግለጽ እንደተሞከረው ዲ/ን ኀይሉ ምስጋናው ዘወትር ሰኞ በማታው የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ላይ ትምህርት በሚሰጡበት ጊዜ በተለይም ሐምሌ 1 ቀን 2005 ዓ.ም በሰጡት ትምህርት ላይ ፍጹም ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጭ የኾነ ትምህርት ሲያስተምሩ አምሽተዋል፡፡ ከሰጡት ትምህርት መካከልም፡-

  1. 1.  እግዚአብሔር እኛን የማያጠፋን ራሱን ማጥፋት ስለማይችልና ስለማይፈልግም ነው፡፡
    2.  ክርስቶስ ያለወንድ ዘር የተወለደው የውርስ ኃጢአት እንዳይነካው ነው፤ ያለአባት በመወለዱ ነው ጥንተ አብሶ የሌለበት፡፡
    3.  ታላቅ ወንድማችን ስለኾነ እንደሰውነቱ ከእኛ ጋር ጸሎትን ይልካል፡፡
    4.  ወንድማችን ስለኾነ ብቁም ስለኾነ ጸሎታችንን ያሳርጋል፡፡
    5.  መካከለኛው አንድ ነው ደግሞም መዋጮ አይፈልግም ሞትን ድል አድርጎ ስለተነሣ ለዘለዓለሙ አስታራቂ ነው ለዘለዓለም መካከለኛ ነው

በሚልና ሌሎችም ያልተገባ ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖትን የሚፃረር ትምህርት ሰጥተዋል በማለት የደብሩ ሰንበት ት/ቤት በሲዲ እና የትምህርቱን ኹኔታ የሚገልጽ 29 ገጽ ደብዳቤ ከ2 ገጽ መሸኛ ጋር ለደብሩ ጽ/ቤት በማያያዝ አቅርበዋል፡፡

ስለኾነም ግለሰቡ የደብሩ መደበኛ ሰባኪ ሠራተኛ ስላልኾኑ የቀረበባቸው ክሥ በሚመለከተው አካል ተጣርቶ ያስተምሩ የሚል መመሪያ እስኪመጣ ድረስ ከነሐሴ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በዐውደ ምሕረትም ኾነ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳያስተምሩ የተከለከሉ መኾናቸውን እየገለጽን የደብሩ ስብከተ ወንጌል ክፍልም ከወትሮው በተለየ ኹኔታ ትምህርተ ወንጌል በሚሰጥበት ጊዜ በአካል በመገኘት ጥብቅ ክትትል እንድታደርጉ እየገለጽን ከክትትል ማነስ ለሚፈጠረው ችግር ጽ/ቤቱ በስብከተ ወንጌል ክፍል ላይ ጥብቅ ርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መኾኑን እናስታውቃለን፡፡

ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር

የማይነበብ ፊርማና ማኅተም አለው

መልአከ ሰላም ዘላለም እሰይ

የመካነ ሰማዕት ቅ/ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ

ግልባጭ

ለደብሩ ሰንበት ት/ቤት

ለዲ/ን ኀይሉ ምስጋናው ባሉበት

አዲስ አበባ

Untitled-22