ችጋር በቃን!!! ረሃብ በቃን!!! መለስ በቃን!!!

በወገኖቻችን ላይ አስከፊ ችጋር መጥቷል። ምሥራቅና ደቡብ ኢትዮጵያን በአስከፊ ሁኔታ እያጠቃ ያለው ጥልቅ መሠረት ያለው ችጋር እንጂ የአንድ ወቅት ረሃብ አይደለም:: ከአሁኑ ሰው በረሃብ መሞት መጀመሩ ከሁለትና ሶስት ወራት በኋላ የሚመጣውን አደጋ ከባድነት መገመት ይሰቀጥጣል።

  • “ከ10% በላይ ተከታታይ እድገት አሳይተናል” የሚለው ዓይን ያወጣ ውሸት፣
  • “ድህነትን ተረት እናደርጋለን” የሚለው ጉረኛ መፈክር፣
  • የመለስ ዜናዊ ጀሌዎች በፎቅና ቪላዎች መንበሽበሽ፣
  • የለም መሬቶች ለቻይናና አረብ ቱጃሮች መታደል፣
  • የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራድዮ “የህዳሴ ብስራቶች”፣
  • ወዘተ …. ወዘተ

ለህዝባችን ቁርስ፣ ምሳና እራት አልሆኑም።

መለስ ዜናዊ እንደለመደው ችግሩን በተፈጥሮ እና በለጋሾች ፈጥኖ አለመድረስ ማላከኩን ተያይዞታል።

  • ለመሆኑ እየተደጋገመ ለሚመጣ ችጋርና ረሃብ ተፈጥሮ ብቻውን በቂ ምክንያት ሆኖ ያውቃልን?
  • ለምንድነው ፍትህና ነፃነት በሰፈነባቸው አገሮች ውስጥ ዝናብ ጠፍቶ የእርሻ ምርት በከፍተኛ መጠን በሚቀንስበት ጊዜ ሰው በረሃብ የማይሞተው?
  • አስከፊ የረሃብ ዜናዎች የሚሰማባቸው አገሮች በሙሉ ነፃነት የታፈነባቸው አገሮች መሆናቸውስ የአጋጣሚ ጉዳይ ነውን?
  • ለምንድነው አንድ ዓይነት ችግር እየተደጋገመብን መላ መፈለግ ያቃተን? “ችግር የመሳካት እናት ናት” የሚለው ብሄል ምነው እኛ ዘንድ አልሰራ አለ?

ችግር የመሳካት እናት የምትሆነው በነፃነት ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ሲኖር ነው። የኢትዮጵያ ገበሬና አርብቶ አደር ነፃነቱ ተገፎ እያለ እንደምን ችጋርን መቋቋሚያ መፍትሄ መፈለግ ይችላል?

ነፃነቱን የተገፈፈ ጭንቅላት ለችግሮች መፍትሄ የማፍለቅ አቅም የለውም። እንዲህ ዓይነቱ ጭንቅላት ችግሮችን ማሸነፍ ሳይሆን ተሸናፊነትን ተቀብሎ ከችግሮች ጋር ተስማምቶና ተወዳጅቶ መኖርን ይመርጣል። ለዚህም ነው የአስተዳደር በደልና ረሃብ ምክንያትና ውጤት ብቻ ሳይሆን እጅና ጓንትም ጭምር የሆኑት። ነፃነት ያለው ህዝብ ረሃብን እንደሚያሸነፍ ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ረሃብን የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ውጤት ብቻ አድርጎ ማቅረብ እውነትን መሸፈጥ የሚሆነው። ችጋርና ረሃብ የብልሹ አስተዳደር ውጤቶች ናቸው።

በአገራችን ውስጥ የተንሰራፋው ስር የሰደደ ችጋር፣ አገዛዝ በተቀየረ ቁጥር እየባሰበት የመጣው የብልሹ አስተዳደር ውጤት ነው። አገራችንን የችጋር ቀጠና ካደረጉ የ20 ዓመታት የመለስ ዜናዊ “የሽፍታ ኢኮኖሚ” ፓሊሲ ውጤቶች መካከል አንዳንዱን ለአብነት ያህል መዘርዘር ይቻላል።

  1. በየጊዜው በሚፈነዳዱ ግጭቶች ሳቢያ አርብቶ አደሩ ተረጋግቶ ስለረዥም ጊዜ ህይወቱ ማሰብና መዘጋጀት አልቻለም። ያለፉት ሃያ አመታት በሙሉ የአርብቶ አደሩ ምኞት ነብሱን ማዳን እና የእለት ጉርስን ማግኘት ብቻ እንዲሆን ተደርጓል። ለዘላቂ ልማት የታሰበ ነገር ባለመሆኑ እነሆ የአንድ የዝናብ ወቅት የዝናብ ካፊያ መጥፋትን እንኳን መቋቋሚያ አቅም አጥቷል።
  2. በመለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመን የደን ጭፍጨፋና የመሬት መሸርሸር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል። አገሪቷ በፍጥነት ወደ ምድረበዳነት እየተቀየረች ነው።
  3. ገበሬና መሬት ተለያይተዋል። አዳዲሶቹ ባለሃብቶች ለፈጣን ኪስ መሙላት እንጂ ለዘለቄታ የአፈር ልማት ፍላጎቱም፣ እውቀቱም የላቸውም። ለም መሬቶች በኢንቨስትመንት ስም በዘመኑ የወያኔ ጉልተኞች በመያዛቸውና እነሱ ደግሞ በተራቸው ለባዕዳን ቱዳሮች እየሸጡ በመሆኑ ባለሃገሩ ጭሰኝነት እንኳን አጥቶ ለቀን ሠራተኝነትና ልመና ተዳርጓል። በዚህም ምክንያት ገበሬው እንኳንስ ትልቁን የአየር መዛባት ትንሿንም የዋጋ ነውጥ መቋቋም እስከማይችልበት ደረጃ ተዳክሟል።
  4. በዘር በተመሰረተ ክልላዊ ድንበር ሳቢያ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ውስጥ ተዘዋውረው መሥራትና ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከረሃብ መታደግ አልቻሉም። ከአንድ ክልል ወደሌላው ከተሰደደ የአገራችን አርሶ አደር ይልቅ ከቻይና ለመጣ ገበሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የእርሻ መሬት ማግኘት ይቀለዋል። እንዲያውም ኢትዮጵያዊው ገበሬ በዱላና በጥይት ሲባረር፤ የቻይናው ገበሬ ብድርና ማበረታቻዎች ይሰጠዋል።
  5. ፋይዳ ያለው የስነ ህዝብ ፖሊሲ ባለመኖሩ የህዝብ ብዛት አሻቅቧል። የመለስ ዜናዊ የስታትስቲክስ ባለሥልጣን ቁጥራችንን በትክክል ሊነግረን ባይፈልግም እንኳን ረሃብ መብዛታችንን እየነገረን ነው።

በአንፃሩ

  1. የወያኔ ቁንጮዎች ራሳቸውን ባለቢሊዮኖች አድርገዋል። በተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሃግብር (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ጥናት መሠረት መለስና ሸሪኮቹ 8.3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከኢትዮጵያ አስወጥተዋል። ይህ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ወደ 150 ቢሊዮን ብር (ብር 150, 000, 000, 000) ይጠጋል። ይህ ገንዘብ 50, 000 የጤና ጣቢያዎችን ወይም 150, 000 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወይም 214, 285 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን መሠራት ያስችል ነበር። የመለስ ዜናዊ ባለሥልጣኖች በአገር ውስጥ ያካበቡት ሃብት ከላይ ከተጠቀሰው እጅግ በላይ ነው። የጥቂቶች ያለአገባብና ያለቅጥ መክበር እና የብዙሃኑን ህዝብ መደህየት፣ ችጋር ቋሚ ክስተት እንዲሆን አድርጓል።
  2. አገር በቀል እና ዓለም ዓቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የተራበውን ወገናችን ለማዳን በሚረባረቡት በአሁኑ ወቅት የመለስ ዜናዊ አገዛዝ 200 ታንኮችን ለመግዛት 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል። ይህንን ራሱ መለስ ዜናዊ በትዕቢት አረጋግጦልናል። አንድ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር ከ 1.7 ቢሊዮን ብር (ብር 1, 700,000,000.00) በላይ ነው። ለታንኮቹ መግዣ በወጣው ገንዘብ 2, 428 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን መገንባት ይቻል ነበር። መለስ ዜናዊ ግን የውሃ ጉድጓዶችን ከመገንባት ይልቅ ታንኮችን ገዝቶ መታቀፍን መርጧል።

እነዚህና የመሳሰሉት ጭብጦችን በማንሳት አገራችን ውስጥ የሰፈነው ችጋር የመለስ ዜናዊ ፓሊሲ ታክሎበት እንጂ ተፈጥሮ ብቻውን ያመጣው ችግር አለመሆኑን መረዳት ይቻላል።

ህዝባችን በነፃነት ማሰብ፣ መመራመር፣ መፈተሽ ቢችል ኖሮ ረሃብን ማጥፊያ ብልሃት ማግኘት ባላቃተውም ነበር። ወደፊትም ቢሆን ተፈጥሮ እኛ እንደፈለግናት አትሆንም፤ መተማመኛችን የሰው ልጅ ወሰን የለሽ የፈጠራ ችሎታና ችግሮችን የመፍታት አቅም ነው። ለዚህ ደግሞ ችግሮችን በልጦ መገኘት ያስፈልጋል። የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የኢትዮጵያን ህዝብ ሁሌ ከችግሮች በታች ሆኖ የእሱን ፈቃድ እንዲያሟላ ይፈልጋል፤ ለዚህም ነው ባርነትን ያወጀብን። መለስ ዜናዊን ከሥልጣን ሳናስወግድ ድህነትንና ረሃብ እናስወግዳለን ማለት ዘበት ነው::

በችጋር ለሚጠቃው ወገናችን መድረስ የምንችለው፤ የችጋሩ መሠረታዊ ምክንያት የሆነውን የመለስ ዜናዊን አገዛዝ አስወግደን ፍትህና ነፃነት የሰፈነባትን፤ ፈጠራ የተስፋፋባትን ኢትዮጵያን ስንገነባ ብቻ ነው። ጊዜ የለም …. ረሃብ ጊዜ አይሰጥም ። የወገኖቻቸንን ሕይወት ለመታደግ በአንድነት እንነሳ።

ችጋር አንገፈገፈን፣ ረሃብ በቃን!!! በቃ!!!!!

በቃ!!! ጋዬ!!! ይአከል!!! አሎኒ!!! ዲታህ!!! ወጣንደም!!! በስ!!! ጊዴስ!!!