በአቡነ ያዕቆብ የአፍሪቃ አህጉረ ስብከት አስተዳደር ላይ የሚቀርበው አቤቱታ እየተጠናከረ ነው
- በጥቅመኝነት ላይ የተመሠረተ የአገልጋዮች ምደባና ስምሪት፣ ለምእመናን ወቅታዊ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠት፣ በዕቅበተ እምነት ሊቀ ጳጳሱ ይታይባቸዋል የሚባለው ቸልተኝነት እና የጎጠኝነት ዝንባሌ በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡
* * *
- ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሥራች አባል ለኾነችበት ለመላው አፍሪቃ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ በምክትል ፕሬዝዳንትነት መመረጣቸው ለውጭ ግንኙነታችን መልካም ዜና ነው፡፡ ከጉባኤው ዓላማና ዋና ዋና ተግባራት መካከል÷ አብያተ ክርስቲያናት የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ማገዝ፣ በመካከላቸውም የባለሞያ ወይም የሰው ኃይል ተራድኦ እንዲኖር ማበረታታት፣ የጋራ ጥናትና ምርምር ማካሄድ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
- አህጉር አቀፍ ጉባኤው ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ አገልግሎቷን እንድታጠናክርና በተስፋ በምትጠበቅበት የጥቁሩ ዓለም ዕውቅናዋን እንድታስፋፋ ዕድል የሚሰጥ ከፍተኛ መድረክም ነው፡፡ ለውጭ ግንኙነት መሠረት የኾነውንና ወሳኝ ሚና የሚጫወተውን የውስጥ አስተዳደር ጥንካሬ የሚጠቅሱ ወገኖች÷ ብፁዕነታቸው መንበረ ሊቀ ጵጵስናቸው በሚገኝበት በጆሐንስበርግ መድኃኔዓለም የተወሰኑና በሌሎች አህጉር (ሱዳን፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ) የሚገኙ አብያተ ክርስቲያንን በቅርበት እንደማይከታተሉ በመጥቀስ ክፉኛ ይተቿቸዋል፡፡
- ሊቀ ጳጳሱ የአብያተ ክርስቲያኑን ተጨባጭ ኹኔታ ሳያገናዝቡ፣ የአብያተ ክርስቲያኑን አስተዳደርና ምእመናን ጥያቄ ችላ በማለት የሚያካሂዷቸው የአለቆች፣ ካህናትና ሰባክያነ ወንጌል ምደባና ስምሪት÷ ለክህነትና ስብከተ ወንጌል ሞያዊ ብቃት እንዲሁም ለቋንቋ ክህሎት ትኩረት የማይሰጥ በምትኩ የጥቅመኝነት ዝንባሌ የሚታይበት፣ የዝምድናና ጎጠኝነት ተጽዕኖ ያየለበት እንደኾነ ተመልክቷል፡፡
* * *
- በአገልጋዮች ምደባና ስምሪት በተፈጠረ ችግር ከመንበረ ሊቀ ጵጵስናው የተለየው የካርቱም ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን በራስ አገዝ አስተዳደር እየተመራ ነው፤ የአስተዳደር ሓላፊዎችን፣ ካህናትንና ሰባክያነ ወንጌል ስምሪትና ምደባን በራሱ እያካሄደ ነው፡፡
- ከአህጉረ ስብከቱ ጋራ ያለውን ግንኙነት ያቋረጠው የካርቱም ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ከመንበረ ፓትርያሪኩ ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት እያደረገ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ በተዘዋወሩት የቀድሞው አስተዳዳሪ ቦታ ይተኩ ዘንድ ሰበካ ጉባኤው ከካህናቱ ጋራ በአንድ ድምፅ በመወሰን ‹‹በሥነ ምግባራቸው፣ ዕውቀታቸው፣ የአገልግሎት ዘመናቸውና ብቃታቸው መርጫቸዋለኹ›› የሚላቸውን አባት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ አለመቀበላቸው ነው የአለመግባባቱ መንሥኤ፡፡
- እልቅናውን ከሚሹ ሌሎች ግለሰቦች እስከ ብር 47,000 እጅ መንሻ ቀርቦበታል ከተባለው ከዚህ ሹመት ጋራ ስማቸው ተያይዞ የሚነሣውና ለሊቀ ጳጳሱ ቅርበት ያላቸው ቀሲስ ግሩም ታዬ አንዱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንበረ ፓትርያሪክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር በአስጎብኚነት የሚሠሩት ቀሲስ ግሩም ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ ያስተሳሰራቸው የቀደመ ዕውቂያቸው ‹‹አጥማቂነታቸው›› መኾኑ ይነገራል፡፡
- በ‹‹አጥማቂነት›› ስም በሚፈጸሟቸው ነውረኛ ተግባራት ክሥና ወቀሳ የቀረበባቸው ቀሲስ ግሩም ከዚህ ቀደም በድጋፍ ሰጭነትና በሓላፊነት ሲሠሩባቸው በቆዩዋቸው ቦታዎች (መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ ፈረንሳይ ኤምባሲ፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት) በሥራ አጋጣሚ በእጃቸውን የገባውን ገንዘብና ንብረት ለግል ጥቅማቸው በማዋል እምነት ማጉደል ርምጃ ሲወሰድባቸው የቆዩ ናቸው፡፡
- ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጽ/ቤት ጋራ በቀጥታ እየተጻጻፈ የሚገኘው የካርቱም ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ያቀረበውን ማመልከቻ ማጤኑ የተነገረው በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ አለመግባባቱ በካህናቱና ምእመናኑ ጥያቄ መሠረት መፈታቱ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ወሳኝነት እንዳለው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጽፎታል በተባለው ደብዳቤ አሳስቧል፡፡
- በግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ርዳታ በሱዳን ካርቱም የተመሠረተው ቤተ ክርስቲያኑ ሁለንተናዊ አገልግሎቱን ለማጠናከር ት/ቤት ከፍቶ በሱዳን የሚወለዱ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት የሀገራቸውን ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ እንዲማሩ እየሠራ ይገኛል፡፡ የውጭ ግንኙነት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የቀድሞው ፓትርያሪክ ባደረጉት ጥረት ደብሩ የሱዳን መንግሥትን ድጋፍ አግኝቷል፤ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ከቤተ ክርስቲያናችን ጋራ በቅርበት እንዲሠራ አድርገዋል፡፡
* * *
- የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በቅድመ ክርስትና ዘመን አንሥቶ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የነበራትን የውጭ ግንኙነትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ታሪክ የሚከተለው የአፍሪቃ አህጉር እንቅስቃሴዋ ነው፡፡ መላዋ ኢትዮጵያ እንደ አንድ የቆብጥ ሀ/ስብከት ትቆጠር የነበረበት የ1600 ዓመት ሞግዚትነት ታሪክ የራስዋን መንበረ ፕትርክና በመቀዳጀት ካከተመ በኋላ ዓለም አቀፋዊ ልዕልናን ካገኘችባቸው 11 አህጉረ ስብከቷ አንዱ ነው – የአፍሪቃ አህጉረ ስብከት፡፡
- በግንቦት ፳፻፫ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ በአንድ መንበረ ሊቀ ጵጵስና እንዲመራ በተደረገው የአፍሪቃ አህጉረ ስብከት አስተዳደር ውስጥ፣ በ፲፰፻፺፪ ዓ.ም የተጀመረው በደቡብ አፍሪቃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት ላይ እንዳለ ተዘግቧል፡፡
- የሀገሪቱ መንግሥት ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሰጠው ክብር ለቤተ ክርስቲያናችን ሰፋፊ መሬቶች ተሰጥተዋል፡፡ በጆሐንስበርግ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን 200 ተማሪዎችን የሚያስተናግድ ት/ቤት፣ በፕሪቶርያ ኪዳነ ምሕረት ከ100 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚረዳ የቤተ ክርስቲያኗ የትምህርት ተቋማት ተገንብተዋል፡፡ በብሎምፎንቴን ለኢትዮጵያውያንና ለደቡብ አፍሪቃ ተወላጆች የሚኾን የቅዱስ ያሬድ የካህናት ማሠልጠኛ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴና የቅዱስ ያሬድ ገዳም በ20,100 ካሬ ሜትር ስፍራ ላይ የተመሠረተ ሲኾን ለግንባታው ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አድባራትና ገዳማት ከሁለት ሚልዮን ብር በላይ መለገሱ ተገልጧል፡፡
- ከአህጉረ ስብከቱ የአስተዳደር ችግሮች ጋራ ተያይዞ ስሙ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው በደቡብ አፍሪቃ የመንበረ ሊቀ ጵጵስናው ጸሐፊ በካቶሊካዊነት በስፋት ይታማል፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዐትንና ሥነ ምግባርን በማቃለል የሚታወቀው ጸሐፊው በሚፈጽመው አስተዳደራዊ ጫና [በደርባን ቅድስት ማርያም] የቤተ ክርስቲያን አንድነት ለአደጋ እየተጋለጠ መኾኑ ተነግሯል፡፡
- በፕሪቶርያ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግዥ መንሥኤ በተቀሰቀሰው ውዝግብ የደብሩ አስተዳዳሪ ከሓላፊነታቸው ለቀዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከሄዱ የሰነበቱት ሊቀ ጳጳሱ ለሦስት ወራት የዘለቀውን ይህንኑ ውዝግብ፣ ‹‹አስተዳዳሪውን ከምእመኑ በማስታረቅ እፈታዋለኹ›› ቢሉም ወደ ደብሩ በእልቅና ተመድበው ለመሄድ የጠየቁ አመልካቾች እስከ ብር 70,000 እጅ መንሻ መጠየቃቸውን በስሞታ መልክ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
* * *
- የቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊ ማንነት በሐዋርያዊ ተልእኮ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የውጭ ግንኘነቷ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን የምታስፈጽምበት አንድ መሣርያ ነው፡፡ በውጭ ግንኙነት ተልእኮዋ እንደ ጥንታዊነቷና ዓለም እንደሚጠብቃት ለመንቀሳቀስ ምእመናን በጎችን ሳይተኙ ነቅተው፣ ሳይሰንፉ ተግተው የሚጠብቁ፣ ባለርእይ የኾኑ፣ የውጩን ቋንቋ፣ ባህልና የኑሮ ዘይቤ በኦርቶዶክሳዊነት ሊዋጁ የሚችሉ አባቶችን፣ ካህናትንና ሰባክያነ ወንጌልን በመመደብ በብቃት ልታከናውን ይገባል፡፡
- በዚህ ረገድ የውጭ ግንኙነት መምሪያው በሰው ኃይል ተጠናክሮና በበቂ በጀት እንዲደገፍ፣ በአፍሪቃ፣ በአውሮጳ፣ በአሜሪካና በሌሎችም አህጉር አገናኝ ዴስክ እንዲቋቋም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን እንቅስቃሴ የሚዳስስ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋ የሚዘጋጅ ወርኃዊ መጽሔት እንዲጀመር ቅ/ሲኖዶስ በጥቅምት ፳፻፭ ዓ.ም ያስተላለፈውና አፈጻጸሙ በእጅጉ የዘገየው ውሳኔ በትውውቅ ከሚፈጸም ቅጥር በራቀ፣ ለሥራው ጥራት ከሚቆረቆርና ብቃት ላይ በተመሠረተ ጥንቃቄ ሊፈጸም ይገባል፡፡
- በዘመናችን ዝርወት ማለትም ዲዮስጶራነት የትውልዱ ባህል ቢኾንም ከቀዬአቸው፣ ከወገናቸውና ካደጉበት ባህል ርቀው በባዕዳን መካከል የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያን በማረጋጋት፣ ኢትዮጵያውያኑንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑን በመልካም ሰብእናና በመንፈሳዊ ሕይወት በማነፅ የኖረችበትን የመሰብሰቢያ፣ የመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ማእከልነት ማጠናከር ያስፈልጋታል፡፡
- ከዚህም ጋራ ለቤተ ክርስቲያናችን መስፋፋት፣ በአህጉረ ስብከት ደረጃ መደራጀት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ምእመናን ጥያቄና አቤቱታ ተገቢው ትኩረት አግኝቶ ወቅታዊ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል – ቤተ ክርስቲያናችን በስደትም፣ በመከራም፣ በእስራትም ጊዜ ከመንጋው የማትለይና ስለሕዝቧ በነገር ሁሉ የምትቀድም መኾኑን የምታረጋግጥበት አጋጣሚ ነውና፡፡