የኛ ሰው በካንጋሮ ምድር

7, 617, 930 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በምታካልለው ሰባተኛ አህጉር፣ በስፋቷ የዓለማችን ስድስተኛ ሀገር በሆነችው አውስትራልያ ውስጥ እገኛለሁ፡፡  አንድ አህጉር አንድ ሀገር ሲሆን አውስትራልያ በዓለማችን ብቸኛዋ ትመስለኛለች፡፡ የሚገርመው ግን ይህንን የሚያህል ሰፊ ሀገር ውስጥ የሚኖሩት ሃያ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ብቻ መሆናቸው ነው፡፡ ‹አይሆንም እንጂ ቢሆንማ› እንደሚባለው ቢቻል ኖሮ ከአውስትራልያ ይዤ ወደ ሀገሬ የምገባው የቤት መሥሪያ መሬት ነበር፡፡ እዚያ የወባ ክኒን የምታክል መሬት ለማግኘት የቀበሌ መታወቂያ፣ 10/90፣ 20/80፣ ባንክ ቤት፣ ወረፋ፣ ምዝገባ፣ ዕጣ፣ መከራ እያሳየን እዚህ መሬት የካንጋሮ መጨዋቻ ሆኖላችኋል፡፡ ‹አስወስጄ መጣሁ አስወስጄ› የሚለው ዘፈን ባህል ነውና እኛ የባሕር በራችንን አስወስደን ትንሷን ጅቡቲ ስንለማማጥ እንኖራለን፤ የዓለማችን ትልቋ ደሴት የምትባለው አውስትራልያ 34,218 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባሕር ጠረፍ ባለቤት ናት፡፡ አውስትራልያ የሚለው ስም ከላቲኑ ‹‹አውስትራሊስ› የመጣ መሆኑንና ትርጉሙም ‹ደቡባዊ› ማለት እንደሆነ ይነገራል፡፡

በስድስት ክልሎችና በሁለት ልዩ ግዛቶች የተመሠረተችው ይህች ፌዴራላዊት ሀገር ራሳቸውን ‹አውሴ› ብለው የሚጠሩት የዛሬ ዋነኛ ነዋሪዎቿ ከመምጣታቸው በፊት ‹አቦርጅን›[አዳሙ ተፈራ የሚባል አውስትራልያ የሚኖር ደራሲ – ‹ኑር ተገኝ› ብሎ ጠርቷቸዋል፡፡] የተባሉ ጥንታውያን ሕዝቦች ይኖሩባት የነበረች ሀገር ናት፡፡ እነዚህ ከእስያ መጥተው ከብዙ ሺ ዓመታት በፊት የኖሩት ባላገሮቹ ዛሬ በሰሜናዊ አውስትራልያ በሚገኘው ‹የሰሜን ግዛት› በሚባለው ልዩ ክልል ውስጥ በብዛት ይገኛሉ፡፡ እንግሊዞች ወደዚች ሀገር ሲመጡ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ቁጥር ነበራቸው የሚባሉት አቦርጅኖች በደረሰባቸው ግፍና መከራ የተነሣ ቁጥራቸው መንምኗል፡፡ ለመሬታቸው ሲባል ተሰድደው፣ ተገድለውና በበሽታ እንዲያልቁ ተደርገው ሀገራቸውን አጥተዋል፡፡ በ1787 ዓም የተነሣውና መጤዎቹ ሆን ብለው ወደ አቦርጅኖች እንዲደርስ አድርገውታል የሚባለው ፈንጣጣ ብቻ ‹ዳሩግ› ከሚባሉት የአቦርጅን ጎሳዎች መካከል ዘጠና በመቶውን ፈጅቷቸዋል፡፡ [የኡጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቪኒ ነጮች በአፍሪካ ላይ በመድኃኒት ጥቁሮችን እንዳይጨርሱ ያደረጋቸው ከብት አርቢ መሆናችን ነው፡፡ ብዙውን በሽታ ከብቶቹ ወስደውታል፡፡ ከከብት ጋር በመኖራችንም የመቋቋም ውሳጣዊ ዐቅም ገንብተናል ብለው ነበር፡፡] ልጆቻቸውን ለጉልበት ሥራ አስገድዶ በመውሰድ፣ እንዳይወልዱ የማምከኛ መድኃኒት በመስጠት፣ የመጠጥ ሱሰኞች ሆነው እንዲቀሩ በማድረግ አቦርጅኖች ከሀገር እንዲጠፉና ቁጥራቸው እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያት በሁለት መቶ ዓመታት ውስጥ እየጠፉ መጥተው በ1900 ዓም አካባቢ ቁጥራቸው ወደ 96 ሺ ወርዶ ነበር፡፡ አሁን ከጠቅላላው ሕዝብ 2 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ እሥር ቤት ስሄዱ ግን 25% እሥረኞች እነርሱ ሆነው ታገኛላችሁ፡፡ ልክ በአሜሪካ አፍሪካ አሜሪካውያን ከጠቅላላ ሕዝቡ 30 በመቶ ቢሆኑም እሥር ቤት ግን 60 ከመቶ እንደሆኑት ዓይነት ማለት ነው፡፡ 
አንዳንድ ጊዜ ለነጻነታችን ለተዋጉት አርበኞች ክብር የምትሰጡት ይህን መሰል የመከራ ታሪኮችን ስትሰሙ ነው፡፡ ‹በኋላ የመጣ ቀንድ በፊት የመጣን ጆሮ በለጠው› እንደተባለ በኋላ ሀገር የወሰዱት ዜጎች ክብሩንም፣ ነጻነቱንም፣ ኢኮኖሚውንም፣ ሥልጣኑንም ነጥቀውት ባላገሩን ሁለተኛ ዜጋ ሲያደርጉት ስታዩ ‹ነጻነት ሆይ ዋጋሽ ምን ያህል ነው?› ትላላችሁ፡፡ አንዳንድ ወገኖቼ ‹ጥቂት ቅኝ ብንገዛ ኖሮ እንሠለጥን ነበር፣ እናድግም ነበር› ብለው ይቆጫሉ፡፡ በእሳት የሚጫወት የአበራሽን ጠባሳ ያላየ ብቻ ነው፡፡ ባይሆን እኛ ‹ነጻነትን አላግባብ በመጠቀም ወንጀል›› ልንቀጣ የሚገባን ሕዝቦች ነን፡፡ ነጻነታችንን ለዕድገትና አንድነት፣ ለብልጽግናና ለመልካም አስተዳደር ከመጠቀም ይልቅ ለጦርነት ተጠቅመንበታል፡፡ የውጭ ወራሪዎችን ተከላክለን ራሳችን በራሳችን ስንዋረር ኖረናል፡፡ ነጻነትን ለጦርነት የመጠቀም ልማዱ አልለቀን ስላለም በአንጻራዊነት የመብት ነጻነት ተከብሮባቸዋል ወደሚባሉት ሀገሮች ስንገባ እንኳን ‹የዘሬን ያንዘርዝረኝ› ብለን ጦርነቱን ቀጥለነዋል፡፡ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭው ዓለም ያሉ የፓርቲና የኮሙኒቲ፣ የሚዲያና የኪነ ጥበብ፣ የቤተ እምነትና የማኅበራዊ ተቋማት አደረጃጀቶቻችን ሁሉ የጦርነት አደረጃጀቶች ናቸው፡፡ የህልውናችን መሠረቱ ጠላት ነው፡፡፡ ያለ ጠላት ህልው መሆን ስለማንችል ጠላት ካጣን ጠላት እንፈጥራለን፡፡
‹እንግዳ ሆነሽ ትመጭ ባለቤት ሆነሽ ትቆጭ› እንደሚባለው በኋላ ዘመን የመጡትና ባለቤትነቱን የወሰዱት እንግሊዞች እነዚህን ነባር ሕዝቦች እንዳይድኑ አድርገው ሰብረዋቸዋል፡፡ ዛሬ ምንም እንኳን ችግሩ የተቀረፈ፣ መንግሥትም ለተፈጸመው ግፍ ይቅርታ የጠየቀ፣ እነርሱን የሚደግፍ ሕግም ያወጣ ቢሆን አካላዊ፣ ባህላዊና ሞራላዊ ህልውናቸውን እንዲያጡ በመደረጉ የተነሣ ወደ ጥንቱ ክብራቸው ለመመለስ አልቻሉም፡፡ እንግሊዞቹ እነዚህን ሕዝቦች ከምቹ የመኖርያ ሥፍራዎች በማስለቀቅ ወደ በረሃማውና ለኑሮ አስቸጋሪ ወደሆነው አካባቢ ገፍተዋቸዋል፡፡ ለብዙ ዘመናት ትምህርትና ሥልጣኔ እንዳይቋደሱ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ይልቅ መጠጥና አደንዛዥ ዕጽ በአካባቢያቸው እንዲስፋፋ አድርገዋል፡፡ የቤተሰብን ማኅበራዊነት በመበተን ወላጆችና ልጆች እንዲለያዩ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደምረው ዛሬም የአውስትራልያ አቦርጅኖች በሀገራቸው ሙሉ በሙሉ የሚያዝዙ አልሆኑም፡፡
ከአውሮፓውያን መካከል አውስትራልያን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኛት ሆላንዳዊው አሳሽ ዊልያም ጃንስዘን ነው፡፡ ዊልያምስ በሰሜን አውስትራልያ የረገጠውን መሬት ‹አዲሲቷ ሆላንድ› ብሎ ሰየመና የሀገሩ ግዛት አደረጋት፡፡ እርሱን ተከትሎ ወዲያው የመጣ አውሮፓዊ ሠፋሪ ግን አልነበረም፡፡ ከእርሱ በኋላ ዊልያም ዳምፐር የተባለ እንግሊዛዊ በሰሜናዊ ምዕራብ አውስትራልያ በ1688 ደረሰ፡፡ እንግሊዞች ወደ አውስትራልያ እግራቸውን መስደድ የጀመሩት ከዚያ ጊዜ በኋላ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በ1770 ጄምስ ኩክ በተባለ መቶ አለቃ አማካይነት ወደ ምሥራቃዊው አውስትራልያ ክልል በመምጣት በእንግሊዙ ንጉሥ ጆርጅ ሦስተኛ ስም አካባቢውን ያዙና ‹ኒው ሳውዝ ዌልስ› ብለው ጠሩት፡፡
እንግሊዞች ወደ አውስትራልያ ፊታቸውን እንዲያቀኑ ያደረጓቸው ብዙ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ በአንድ በኩል የአሜሪካ ግዛታቸው ነጻ መውጣት የእርሻ ቦታቸውን ነጥቋቸዋል፡፡ ስለዚህም ሌላ ቦታ በማፈላለግ ላይ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወንጀለኞቻቸውን ያሥሩባት የነበረችው አሜሪካ ነጻ መውጣቷ ሌላ የወንጀለኞች ማሠሪያ እንዲያፈላልጉ አስገድዷቸው ነበር፡፡
እንግሊዞች ወታደሮቻቸውንና ወንጀለኞችን ይዘው በ1788 ዓም ወደ አውስትራልያ በመምጣት በሲድኒ በኩል አካባቢውን እያጸዱ መቆጣጠር ጀመሩ፡፡ በአሜሪካ የባሮችን ጉልበት ያጡት እንግሊዞች በአውስትራልያ የእሥረኞችን ጉልበት መጠቀም ጀመሩ፡፡ እየቆዩም ከተለያዩ ሀገሮች የመጡ ስደተኞች ተቀላቀሏቸው፡፡  
ዛሬ በአውስትራልያ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ220 በላይ ሀገር ሰዎች ይኖሩባታል፡፡ ምንም እንኳን ዋናው ኦፊሴልዊ ቋንቋዋ እንግሊዝኛ ቢሆን ከ224 ቋንቋዎች በላይም ይነገሩባታል፡፡ የፌዴራል ሥርዓት የምትከተለው አውስትራልያ የሀገሪቱ ርእሰ ብሔር የእንግሊዟ ንግሥት ናት፡፡ (በነገራችን ላይ ንግሥቲቱ ካናዳን ጨምሮ የ16 ሀገሮች ርእሰ ብሔር ናት) የ2006 ዓም የሀገሪቱ የቆጠራ ውጤት እንደሚገልጠው ከሕዝቡ ቁጥር ሩብ ያህሉ ከተለያየ ሥፍራ መጥቶ የሚኖር ነው፡፡ ጣልያኖች፣ ቻይናዎች፣ ቬትናሞች፣ ሕንዶችና ፊሊፒኖች ከስደተኞቹ መካከል ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ ከአፍሪካ አህጉር ብቻ ከ48 ሀገሮች የመጡ ስደተኛ ነዋሪዎች በአውስትራልያ ይገኛሉ፡፡
በ2006 ዓም የተደረገው የአውስትራልያ ሕዝብ ቆጠራ በሀገሪቱ 7516 ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይገልጣል፡፡ ነባር ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ግን ቁጥሩን የዚህ ሦስት እጥፍ አካባቢ ያደርጉታል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ለቆጠራው ቅጽ ትኩረት ባለመስጠታቸው እንደማይሞሉት፣ አንዳንዶቹም የቋንቋው ችግር ሳይረዱት እንዲቀሩ እንደሚያደርጋቸው፣ ሌሎቹም ከቆጠራው በኋላ በብዛት መምጣታቸውን እንደ ምክንያት በመውሰድ የኢትዮጵያዊውን ቁጥር እስከ ሃያ ሺ ያደርሱታል፡፡ የአውስትራልያ መንግሥት ቆጠራ እንደሚያሳየው 26 በመቶዎቹ የሀገሬ ልጆች በሹፍርናና ማሽኖችን በማንቀሳቀስ፣ 24.3 በመቶዎቹ በጉልበት ሥራ፣ 16.3 በመቶዎቹ በአገልግሎት ዘርፍ፣ 33.5 በመቶዎቹ ደግሞ በአስተዳደር፣ በጸሐፊነት፣ በቴክኒክ ሥራ፣ እንዲሁም በሌላ ሞያ ነክ ሥራ መሠማራታቸውን ያሳያል፡፡ በሀገሪቱ ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እዚህ እኔ ያለሁበት ቪክቶርያ ግዛት፣ ሜልበርን ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው፡፡
አዳሙ ተፈራ ‹ገመናችን በሰው ሀገር› ብለው በጻፉት መጽሐፍ ላይ እንደገለጡት ወደ አውስትራልያ ለመጀመሪያ ጊዜ የገቡት ኢትዮጵያዊ አቶ አዲስ ታምሩ ይባላሉ፡፡ እኒህ በ1965 ዓም ወደ አውስትራልያ የገቡት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባልደረባ ለትምህርት መጥተው ነው በዚሁ የቀሩት፡፡ ዛሬ ከሀገሩ ነባር ነዋሪ (አቦርጅን) ጋር ተጋብተው ይኖራሉ፡፡
እዚህ የሚኖሩ የሀገሬ ልጆች ብዙ አስገራሚ፣ ብዙ አስቂኝ፣ ብዙም አሳዛኝ ገጠመኝ አላቸው፡፡ እድሜና ጤና ከሰጠን አብረናቸው እናዝናለን፣ እንስቃለን፣ እንሳቀቃለንም፡፡
ሜልበርን፣ አውስትራልያ