በሽብር ተጠርጥረው የታሰሩት ጋዜጠኞች ምርመራ አልተጠናቀቀም

በታምሩ ጽጌ | ሪፖርተር

በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ኔትወርክ ለመዘርጋትና ለልዩ ልዩ የጥፋት ድርጊት የሚውል አደረጃጀት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸው የሁለት ጋዜጠኞችና ሌሎች የሰባት ተጠርጣሪዎች የምርመራ ሒደት አለመጠናቀቁን፣ የፌዴራል ፖሊስና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡ የአውራአምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ በፍትሕና አዲስ ፕሬስ ጋዜጦች፣ በፖለቲካ አምድ ላይ የምትጽፈውና ቋሚ ስራዋ መምህርነት መሆኗ የተገለጸው ወይዘሪት ርዕዮት ዓለሙ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘርይሁን ገብረ እግዚአብሔርና የፓርቲው አባል መሆኑ የተገለጸው አቶ ደጀኔ ተፈራን ጨምሮ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች፣ በሽብር ወንጀል ተሳትፎ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሁለቱ ተቋማት ተወካዮች ሰኔ 22 ቀን 2003 ዓ.ም. ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ይፋ ሳያደርጉ አራቱን ተጠርጣሪዎች ብቻ ይፋ ያደረጉበትን ምክንያት ተጠይቀው፣ አራቱን ግለሰቦች በሚመለከት ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተለያዩ ዘገባዎች ሲተላለፉ ስለነበር፣ እውነቱን ለማሳወቅ መሆኑንና ተጠርጥረው የተያዙበት ጉዳይም ጋዜጠኛና የፖለቲካ ፓርቲ አባል ከመሆናቸው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ለመግለጽ መሆኑን፣ በፌዴራል ፖሊስ የማዕከላዊ መረጃና የወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ገልጸዋል፡፡

እንደ ምክትል ኮሚሽነር ደመላሽ ገለጻ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከአገር ውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎችና ከሻዕቢያ ጋር በማበር በኤሌክትሪክ ማሰራጫዎችና በስልክ መስመሮች ላይ ጉዳት ለማድረስ፣ አገሪቱን ወደ ሽብርና ሁከት ቀጣና ለመቀየር ሲንቀሳቀሱ ፓሊስ ባደረገው ክትትል በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ኤልያስ ክፍሌ በሚባል ግለሰብ አማካይነት ከሻዕቢያ መንግሥት ጋር በመተባበር፣ በማቀድ፣ በማቃናጀት፣ በከፍተኛ ገንዘብ በመደገፍ ተጠርጣሪዎቹ ለወንጀሉ ተሳታፊ የሚሆኑ ሰዎችን በመመልመልና በማሠልጠን ለማሰማራት በዝግጅት ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆላቸው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ደመላሽ ገልጸው፣ ምርመራው እንደተጠናቀቀ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ የነበረውን የወንጀል ተሳትፎ ይፋ እንደሚያደርጉና በተገቢው ፍርድ ቤትም ክስ እንደሚመሠረትባቸው አስታውቀዋል፡፡ በቂ መረጃ ከተሰበሰበ በኋላ ከፍርድ ቤት የመመርመሪያና የመያዥያ ፈቃድ በመውሰድ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸውና ቤተሰብም እየጐበኛቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ በነፃነት ግዛት ውስጥ አቋራጭ መንገድ ተጠቅሞ ዜጐችን ለመፈረጅና ለማሰር የተደነገገ እንዳልሆነ፣ ማንም ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው ሊገምተው አንደሚችል የገለጹት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ናቸው፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት፣ ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በጋዜጠኝነት ወይም በምክትል አዘጋጅትነት ስለተሳተፉ ሳይሆን፣ በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል በመሆኑ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ላለፉት ዓመታት በጋዜጠኝነት ሲሠራ፣ መንግሥትን በመንቀፍና በመተቸት ሲጽፍ ቆይቷል፡፡ በጻፈው አስተያየትና ትችት የተነሳ ቢሆን ኖሮ ከዚህ በፊት በነበሩበት ሥራዎቹ ይጠየቅ ነበር ብለዋል፡፡

ጋዜጠኛው በቁጥጥር ሥር የዋለው በሽብርተኝነት ሥራ ውስጥ በመሳተፍ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ካሉ ተባባሪዎቹ ጋር በመመሳጠር፣ የመሠረት ልማት ተቋማትን ለማጥፋትና ለማውደም ቡድን ሲመለምል በተጨባጭ ፖሊስ ስለደረሰበት መሆኑን አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡