ባዶ አቁማዳ

ነፍሱን ይማረውና ሀገራችን ካፈራቻቸው የቅርብ ዘመን ገጣምያን አንዱ ደበበ ሰይፉ ‹ከአኩስም ጫፍ አቁማዳ›› የሚል ግጥም ነበረው ፡፡በዚህ የኢትዮጵያዊነት ፍቅርና መነሻውን በውብ ትረካ በገለጠበት ግጥሙ ላይ እንዲህ የሚሉ የመዝጊያ አካባቢ ስንኞች አሉት፡፡
‹‹እኔ ና ወንድሞቼ›› አለ በለዘብታ
ለራሱ እንዲያወራ የራሱን ስሞታ
‹‹እኔና ወንድሞቼ ሁላችን ሁላችን
ከባዶ አቁማዳ ነው የሚዛቅ ፍቅራችን
ይህ ነው አንድነታችን
ይህ ነው ባህላችን››
(ደበበ ሰይፉ፣ የብርሃን ፍቅር፣ 1992 ዓም፣ ገጽ 60)
አንዳንድ ጊዜ እኛነታችንን ዝም ብላችሁ ስታስተውሉት ይኼ ባዶ አቁማዳ ይታያችኋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከጥጋብ ይልቅ ረሃብ፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነት፣ ከደስታ ይልቅ መከራ፣ ከማግኘት ይልቅ ማጣት፣ ከነጻነት ይልቅ እሥር፣ ከሥልጣን ይልቅ ተራነት፣ ከመሾም ይልቅ መሻር፣ ከዕውቀት ይልቅ ማይምነት፣ ከምሁርነት ይልቅ ሌጣነት ሲያፋቅረን ታያላችሁ፡፡ እኛው አበሾቹ ‹ውሾች ምን ጊዜ ነው የሚናከሱ – ጅብ አባረው ሲመለሱ› ብለን እንተርታለን፡፡ ደስታና ጥጋብ፣ ማግኘትና ነጻነት ከሌሎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከመርሖቻችንና ከዓላማዎቻችን ጋር ሳይቀር ሲያጣላን እናየዋለን፡፡ በበረሓ ትግል ተግባብተውም ይሁን ተሸካክመው የኖሩ ታጋዮች ከተማ ሲገቡ ነው ከመርሖቻቸውም ከመርሕ ወገኖቻቸውም ጋር የተጣሉት፡፡ ተከባብረውም፣ ተሸካክመውም፣ ተጣጥመውም የኖሩት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ድልና ሥልጣን ወደ ደጃቸው መቅረብ ስትጀምርና በክብርና ዝና መጥለቅለቅ ሲጀምሩ ነበር ሽንፍላቸውን ገልብጠው ያሳዩን የጀመሩት፡፡ ከባዶ አቁማዳ ነበረ ፍቅራቸው፡፡

ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባዮች ናቸው፤ አብረው የሚበሉ፣ አብረው የሚጠጡ ናቸው፤ ማኅበራዊ ኑሮ የሚያውቁ ናቸው፤ ዘመድ ጠያቂ ናቸው፤ በክፉም በደጉም የሚጠያየቁ ናቸው፤ በዕድርና በዕቁብ የሚረዳዱ ናቸው፤ ጎረቤት ከጎረቤቱ ተለይቶ አይበላም፤ እየተባለ ይነገርልናል፤ ይዘከርልናል፡፡ እኛም በየቦታው በኩራት እንናገረዋለን፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ግን እነዚህን ነገሮች የምናገኛቸው ባዶ አቁማዳ ያለበት መንደር ነው፡፡ ‹‹ባለ ጸጎች› ከሚኖሩባቸው መንደሮች በአንዱ የሚኖር አንድ ጓደኛዬ ለልጁ ልደት ጠርቶኝ ሄጄ ነበር፡፡ የተሰበሰብነው ጓደኞቹ ብቻ ነን፡፡ ‹‹ጎረቤቶችህን አትጠራቸውም?›› ስለው ‹‹አንተዋወቅም›› አለኝ፡፡ እዚያ ቤት ከገባኮ ሁለተኛ ዓመቱ ሊሆን ነው፡፡ ‹‹አትገናኙም›› ስለው ‹‹መኪና ሳስገባ አንዳንድ ቀን እንተላለፋለን›› ብሎኝ ዕርፍ፡፡ ‹‹መስቀል አብራችሁ አታከብሩም›› መልሼ ጠየቅኩት፡፡ ‹‹እኔ እንዲያውም እናቴ ጋ ነው የምሄደው›› አለኝ፡፡ ደበበ ሰይፉ ‹ከባዶ አቁማዳ ነው የሚዛቅ ፍቅራችን›› ብሎ ነበር፡፡ ጠርሙስ ውስጥ ውኃ ሲገባ አየሩ እንደሚወጣው ሁሉ ፣ ባዶው አቁማዳ ውስጥ ሀብት ሲገባበት ፍቅሩ ይወጣል መሰል፡፡
ቡና ቢበዛ ከምሳ በኋላና በበዓል ጊዜ ከቤተሰባቸው ጋር ካልሆነ በቀር ከጎረቤት ጋር የሚጠጣ ቡና በአማርኛ ፊልም ብቻ የሚያዩ ወገኖቼ ሞልተዋል፡፡ እንኳን አሁን የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት መጥቶ ቀርቶ ድሮም ዕድር ገብቶባቸው የማያውቅ የሀብታም ሠፈሮች አሉ፡፡ ዕቁብማ ቃሉስ ይታወቃል ብላችሁ ነው? እንዲያውም ሀብቱና ዕውቀቱ ሲጨምር ከማኅበራዊነቱ ይልቅ ግላዊነቱ ሠልጠን ሳይል አይቀርም፡፡
ከኢትዮጵያ ወጣ ስትሉም ይህንን ነገር ታዩታላችሁ፡፡ ወገኖቻችን በነጻነት እጦት፣ በመብት ገፈፋና በሰቆቃ በሚኖሩባቸው የዐረብ ሀገራት እርስ በርስ ያለው መተሳሰብ፣ መከባበርና መፋቀር በገንዘብ ቢተመን የሀገራችን የዓመት በጀት የሚያስከነዳ ነው፡፡ ወደየ ቤተ እምነቶቹ ስትሄዱ ለመማር፣ ለማገልገል፣ ገንዘብ ለመስጠት፣ ለማልቀስና ራስን ለፈጣሪ ለማስገዛት እጅግ ብዙ የተከፈቱ ልቦችንና የተሰበሩ መንፈሶችን ታገኛላችሁ፡፡ አስደናቂና ፈዛችሁ የምትሰሟቸው የፍቅርና የመተሳሰብ ገድሎችን ትሰማላችሁ፡፡ ፍቅር ተጋግሮ ፍቅር ሲበላ ትደርሳላችሁ፡፡
ከዐረቡ ዓለም ሻል ያለ ነገር ግን ከሌላው የባሰ በሚሆነው የአፍሪካ አህጉር በስደት ላይ የምታገኟቸው ወገኖቻችንም መከራውንና ስደቱን፣ እንክርቱንና መገፋቱን ለመሸከምና ለማለፍ ሲሉ እንደ አፈርና ጭድ መረገጡ ሲያጣብቃቸው ታያላችሁ፡፡ በየስደተኞች ካምፕ የምታዩት ከአሮጌ አቁማዳ የሚዛቅ ፍቅር እዚያው ቅሩ የሚያሰኝ ነው፡፡ ከመከፋፈል ይልቅ መተባበር፣ ከመጣላት ይልቅ መፋቀር ቦታውን ተሻምተውት ታገኛላችሁ፡፡ ሁሉም ባለ ተስፋ ነው፤ ሁሉም መሄድን ይመኛል፤ ሁሉም ከዛሬ ይልቅ ለነገ ይተጋል፤ ሁሉም ተደጋግፎ መሻገር ይፈልጋል፡፡ እናም ሌላውን የመሸከም ዐቅሙ ታላቅ ነው፡፡
ወደ አውሮፓ ስትሻገሩ ፍቅሩና መተሳሰቡ፣ መሸካከሙና መከባበሩ፣ አንድነቱና ትብብሩ እየጠፋ እየጠፋ እየጠፋ ሲሄድ ታዩታላችሁ፡፡ በዘር፣ በፖለቲካ፣ በእምነት፣ በእምነት ዘውጎችና በቋንቋ የሚኖረው መለያየት ከስንጥቅ ወደ ንቃቃት ሲያድግ ይታያችኋል፡፡ አሮጌው አቁማዳ እየተቀደደ ይሄዳል፡፡ ተደማምጦ መነጋገር፣ ተግባብቶ መለያየት እየጠፋ ይሄዳል፡፡ የሚያግባባ ጉዳይ ይጠፋል፡፡ ሰው ልዩነት ብቻ ይኖረዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን አውሮፓ እንደ አሜሪካና አውስትራልያ ኑሮው ያን ያህል አይደላም፤ ነጻነቱም ያን ያህል አያወላዳም፤ የመኖሪያ ፈቃዱም ያን ያህል በቀላሉ አይገኝም፤ በካምፕ የሚኖር አለ፤ የመኖሪያ ፈቃድ ከዛሬ ነገ አገኛለሁ እያለ በተስፋ የሚኖር አለ፡፡ የመኖርያ ፈቃድ ቢያገኝም የተትረፈረፈ ገንዘብ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ስለዚህም እዚህ አሮጌዋ አቁማዳ ለበረከት ያህልም አትጠፋም፡፡ በአውሮፓ የከረረ ዘረኛነት፣ የከረረ የቤተ እምነቶች መለያየት፣ የከረረ ጎሰኛነት፣ የከረረ የፖለቲካ ጡዘት አናይም፡፡
አሜሪካና አውስትራልያ ስንሻገር ግን መልኩ ፈጽሞ ይቀየራል፡፡አሮጌዋ አቁማዳ ብጥስጥሷ ወጥቶ ከጥቅም ውጭ ትሆናለች፡፡ የሰው ሁሉ ሥዕለት አሜሪካ/አውስትራልያ ላይ ያቆማል፡፡ ስለዚህም ከእግዜር ጋር በችግሩ ጊዜ የነበረው ወዳጅነት ይቀዘቅዛል፡፡ ተስፋ ያበቃል፡፡ የተስፋይቱ ምድር ገብቷል፡፡ የሌላው ርዳታ አያስፈልገኝም ብሏል፡፡ ግለኛነት የነገሠበት ሀገር ደርሷል፡፡ ያን ጊዜ ኢትዮጵያዊነት የተደበቀ መልኩን ብልጭ ያደርጋል፡፡ አብሮ መብላት፣ አብሮ መኖር፣ መተሳሰብ፣ ሰው አፍቃሪ፣ ለወገኑ ሟች፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ማኅበራዊ ኑሮ የሚያውቅ የሚሉት ነገሮች ተረት ይሆናሉ፡፡ ጎሰኛነትና ጠባብነት፣ ጽንፈኛነትና አክራሪነት፣ ግለኛነትና ትዕቢት፣ እኔ ዐውቃለሁና የበላይነት ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡ ከፈረንጁ ጋር እየኖረ ከሐበሻው ጋር መኖር ይከብደዋል፡፡ በማያውቀው ሀገር እየኖረ ከሚያውቀው ሰው ጋር መስማማት ይሳነዋል፡፡ይበልጥ ሲሠለጥን ይበልጥ ይሠየጥናል፡፡ ይበልጥ ነጻነት ሲያገኝ ይበልጥ ይባልጋል፤ ይበልጥ ሲፈቀድለት ይበልጥ ይከለክላል፣ ይበልጥ ሲሰፋው ይበልጥ ይጠባል፡፡ በገንዘብ ሲበለጽግ በፍቅር ይበልጥ ይደኸያል፡፡ ለምን?
ፍቅራችን የሚመነጨው ከባዶው አቁማዳ ስለሆነ ይሆን? ታድያ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ሀብት ጸጋ ነው መርገም? በድኽነታቸው በሰላምና በፍቅር የኖሩ አፍሪካውያን ወዳጆቻችን፣ ነዳጅ፣ ወርቅና አልማዝ ተገኘ ሲባል ግን የጦርነት አውድማ ይሆናሉ፡፡ የእነርሱም እንደኛው ፍቅራቸው ከባዶው አቁማዳ የሚገኝ ነው እንዴ? ወይስ ድህነትን ለማስተዳደር ያለንን ልምድና ባህል ያህል ብልጽግናን ለማስተዳደር የሚሆን ልምድና ባህል የለንም? ቻይናዎች ‹‹ድህነት በበር ሲገባ ፍቅር በመስኮት ትወጣለች፣ተኩላ በበር ሲገባ ርግብ በመስኮት ትበራለች›› ይላሉ፡፡ የኛ ግን የግልንቢጥ ነው መሰል፡፡

ብሪዝበን፣ አውስትራልያ