በወላይታ የአንድነት አመራር ልጅ ታፍኖ ተወሰደ – ፍኖተ ነጻነት
በወላይታ የአንድነት አመራር ልጅ ታፍኖ ተወሰደ
አቶ ማሞ ዳሞ በወላይታ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር አባል ናቸው፡፡ለህዝባዊ ስብሰባው ስኬት በማሰብም ሙሉ ጊዜያቸውን በመሰዋት ጠንካራ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ማሞ ከዚህ ቀደም በህገ ወጥ መንገድ ሲታሰሩና ሲፈቱ ሁሉንም በጸጋ በመቀበል በሰላማዊ ትግል ሃሳባቸውን ከመግለጽ መንግስት መብቴን ሊያከብር ይገባዋል በሚሉት ሁሉ ያለምንም ፍርሃት ድምጻቸውን በማሰማት በወላይታ ነዋሪዎች ዘንድ አክብሮትን አትርፈዋል፡፡
ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሶዶ ቀለም መሰናዶ ት/ቤት አካባቢ ዘንድሮ የ12ኛ ክፍልን ብሄራዊ ፈተና የወሰደ ልጃቸውን በማግኘት ጥቂት ጊዜ አብረውት ካሳለፉ በኋላ በፖሊስ የታሰረች አባልን ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣብያ ሲያመሩ ስልካቸው ይጠራል‹‹በስልኩ የሰሙት ሰው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በአካል ያገኙት ልጃቸው ከባለ ሶስት እግር ባጃጅ ነው በወረዱ ሁለት ሰዎች ታፍኖ የድረሱልኝ ድምጹን እያሰማ መወሰዱን ይነግራቸዋል፡፡
አቶ ማሞ ባጃጁ ሄደበት ወደተባለ ቦታ አጋራቸውን በማስከተል አምርተዋል፡፡ነገር ግን ልጃቸውን ሊያገኙት አልቻሉም፡፡እንዲህ አይነት ድርጊቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ለፖሊስ የአንድነት አባላት ሰሞኑን ሲያመለክቱ ቢቆዮም ፖሊስ የምትሉት ቅጥፈት ነው በማለቱ ጥበቃ ሊያደርግ አልቻለም፡፡ወዴት እያመራን ይሆን? የወላይታ ህዝብ በአዳራሽ ውስጥ እንዲሰበሰብና ከደህዴን /ኢህአዴግ የተለየ ሃሳብ እንዳለ በመስማት ያሻውን እንዲመርጥ በመጋበዙ የአቶ ማሞ ልጅ በጠራራ ጸሐይ ታፍኖ መወሰድ አለበት? #millionsofvoicesforfreedom #Ethiopia #UDJ