ወላይታ፤ ታርጋ አልባዎቹ ሞተር ሳይክሎችና – ዳንኤል ሺበሺ

ታርጋ አልባዎቹ ሞተር ሳይክሎችና ዳንኤል ሺበሺ
August 2, 2013 at 6:14pm

በወላይታ ሶዶ ከተማ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በ28/11/05 ለሚያደርገው የህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ ለማካሄድ በስፋራው የተገኙት የፓርቲው አመራሮችና በወላይታ የፓርቲው አባላት የተለያዮ ህገ ወጥ ድርጊቶች እየተፈጸመባቸው ይገኛል፡፡በአመራሩና በአባለቱ ላይ እየደረሰ የሚገኘው ህገ ወጥ ድርጊት የተለያየ መልክ የተላበሰ ሲሆን በዋናነትም ታርጋ አልባ በሆኑ ሞተር ሳይክሎች የተፈናጠጡ ወጣቶች የፓርቲውን አባላት ንብረት መንጭፈው መሰወራቸው ይጠቀሳል፡፡

በአባላቱ እጅ የሚገኝን ቦርሳ፣ በራሪ ወረቀት የያዙ ፌስታሎችና የጸረ ሽብር አዋጁን በመቃወም ዜጎች ፊርማቸውን እንዲያኖሩበት የተዘጋጀ ሰነድ በመቀማት የሚሰወሩት ሞተሮች በከተማው ውስጥ ከሚገኙት በተለየ ታርጋ ቁጥር አልባ መሆናቸው ነገሩን አስገራሚ አድርጎታል፡፡የፓርቲው አመራሮች መንግስትና የጸጥታ ሃይል አለ በሚባልበት አገር በጠራራ ጸሐይ እንዲህ አይነት ድርጊት መፈጸሙ አስገራሚም አስተዛዛቢም መሆኑን ለፖሊስ ለማስረዳት ወደ ዞኑ ፖሊስ ጣብያ ባመሩበት ወቅት የጣብያው ሃላፊ ‹ታርጋ የሌላቸውን ሞተር ሳይክሎች አስረናል፣አሽከርካሪዎቹንም እስከ 500 ብር ቀጥተናል፡፡አሁን ግን እንዲህ አይነት ሞተሮች የሉም››በማለት ምላሽ በመስጠት አመራሮቹን ያሰናብታሉ፡፡

አመራሮቹ የፖሊስ ጣብያውን በር እንደተሻገሩ አቶ ዳንኤል ሺበሺን ታርጋ አልባው ሞተር ሳይክል ተከተላቸው፡፡ ግጥምጥሞሹ አስደንቋቸውና ለፖሊሱ ሃላፊ ሞተሩን እጅ ከፍንጅ በመያዝ ለምስክርነት ለማቅረብ በማሰብ ሞተረኛውን ‹‹በህግ አምላክ ከዚህ ቦታ ንቅንቅ አንዳትል››በማለት ሌሎቹ አጋሮቻቸው ፖሊሶችን እንዲጠሩላቸው ያደርጋሉ፡፡እንዳለመታደል ሆኖ ግን አቶ ዳንኤልንና ጓደኞቻቸውን በቢሯቸው ያናገሩት ሃላፊ ‹‹እንዴት ይህንን ሰው ወንጀል እንደሰራ ሰው በአደባባይ ትይዘዋለህ በማለት ቁጣ ቅልቅል በመናገር ወደ ቢሯቸው አቶ ዳንኤልን ይዘው በመግባት ባለ ሞተሩን ከፈለገ መክሰስ እንደሚችል በመንገር ዳንኤል ተከስሰው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ይደረጋሉ፡፡
ፖሊሱ አቶ ዳንኤልን ዋስ በመጥራት መውጣት እንደሚችሉ ይናገሯቸዋል፡፡ነገር ግን የአንድነቱ አመራር ዋስ እንደማይጠሩ አጠንክረው በመግለጻቸው ፖሊሱ ከአቶ ዳንኤል ጋር የነበሩ የወላይታ ነዋሪዎችን ‹‹ለምን እናንተ ዋስ አትሆኑትም››በማለት ለማግባባት ሞክረዋል፡፡‹‹ምንም ባለማጥፋቱ አንዋሰውም ከፈለጋችሁ ልታስሩት ትችላላችሁ››የሚል ምላሽ ነዋሪዎቹ በመስጠታቸው ሃላፊው ‹‹ስንፈልግህ ትመጣለህ አሁን ግን መሄድ ትችላለህ ››በማለት አቶ ዳንኤልን ከ5 ሰዓታት እገታ በኋላ አሰናብተዋል፡፡በነገራችን ላይ ታርጋ አልባ ከሆኑትና ወንጀል ከሚፈጸምባቸው ሞተር ሳይክሎች መካከል የካሜራችን ቀለብ መሆን የቻለውን በዚህ ቦታ ለእይታ አብቅተነዋል፡፡
#millionsofvoicesforfreedom# Ethiopia udj
20214_10200342974237855_1798049873_n