ሰበር ዜና – የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የ14 አድባራት አስተዳዳሪዎችን ከሓላፊነት አነሣ

  • ዐሥራ አንዱ የተነሡት በዝውውር ነው፤ ቀሪዎቹ ሦስቱ ከአስተዳዳር ሥራ ውጭ ተደርገዋል
  • ከአስተዳደር ሥራ ውጭ ከተደረጉት ውስጥ የደ/ጽጌ ቅ/ዑራኤል እና የደ/ሰላም ቅ/እስጢፋኖስ አስተዳዳሪዎች ይገኙበታል

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ሙስናና ብልሹ አሠራር የገነገነባቸውን፣ የካህናትና ምእመናን አቤቱታ የበረታባቸውን 14 አድባራት አስተዳዳሪዎችን የማዘዋወር፣ ከአስተዳዳሪነት ሓላፊነት የማራቅ እና በጡረታ የማግለል ውሳኔ ማሳለፉ ተገለጸ፡፡

የአስተዳዳሪዎች ዝውውር የተካሄደባቸው አድባራት፡- የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የደብረ ነጎድጓ ቅዱስ ዮሐንስ፣ የደብረ ሰላም ቀጨኔ መድኃኔዓለም፣ የደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የደብረ ገሊላ ቅ/ዐማኑኤል፣ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ የመንበረ መንግሥት ቅ/ገብርኤል ገዳም፣ የሰሚት ኪዳነ ምሕረት፣ የመካኒሳ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና የመካኒሳ ቅ/ሚካኤል ይገኙበታል፡፡

የደብረ ሰላም ቅ/እስጢፋኖስ አስተዳዳሪ ወደ መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተዛውረው በሕግ አገልግሎት መምሪያ እንዲሠሩ፣ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ወደ ቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ተዛውረው በጸሎተ ቅዳሴ እንዲያገለግሉ እና በእርሳቸው ቦታ የደብረ ነጎድጓድ ቅ/ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እንዲተኳቸው ተደርጓል፡፡ ሰሞኑን እስከ 800 የደብረ ገሊላ ቅ/ዐማኑኤል ካቴድራል ምእመን አቤቱታ ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተሰለፈባቸው የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ወደ ደብረ ነጎድጓድ ቅ/ዮሐንስ ተዛውረዋል፡፡

የመንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም አስተዳዳሪ በጡረታ ተገልለዋል፡፡

የዜናው ዝርዝር ይቀጥላል