የኤፈርት ኩባንያ አካል የሆነው ሳባ ኢንጂነሪንግ የአስራ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር እዳ ያለበት መሆኑ ታወቀ
ከህወሃት የንግድ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ሳባ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ወያኔ በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩትን ንብረቶች ወደ ግል ለማዛወር ባወጣው ደንብ ከአራት አመታት በፊት ከመንግሥት በርካሽ ዋጋ የገዛውን የአዲስ ጡብ ማምረቻ ፋብሪካ ክፊያ ዋጋ እስከዛሬ ባለመፈጸሙ ክስ የቀረበበት መሆኑን ለአገዛዙ ቅርበት ያለዉ የሪፖርተር ጋዜጣ ዘገበ። እንደ ሪፖርተር ዘገባ ሳባ ኢንጂነሪንግ በገባው ውል መሰረት ክፍያውን በወቅቱ ባለመክፈሉ የ11.4 ሚሊዮን ብር ባለ ዕዳ መሆኑ ታውቋል።
በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩትን አብዛኛዎቹን የንግድና የማምረቻ ተቋሞች በሽያጭ ስም ወደራሱ የግል ድርጅት ያዞታ ያዛወረው የትግራይ ጉጂሌ በ1999 ዓም አዲስ ጡብ ማምረቻ ፋብሪካ የተባለውን የልማት ድርጅት ለመሸጥ የይስሙላ ጨረታ ያወጣ ሲሆን፣ ሳባ ኢንጂነሪንግ ጨረታውን አሸንፎ ድርጅቱን በ23 ሚሊዮን ብር ለመግዛት በመስማማት ጥቅምት 29 ቀን 1999 ዓ.ም. የግዢ ውል ተፈራርሟል ተብሎ ነበር፡፡ በወቅቱ ሳባ ኢንጂነሪንግ የሽያጩን ዋጋ 35 በመቶ የሆነውን 8,052,000 ብር ብቻ ከፍሎ ፋብሪካውን እንዲረከብ ከተደረገ በኋላ ቀሪውን 14.9 ሚሊዮን ብር በ5 አመት ዉስጥ እንዲከፍል ሁኔታዎች የተመቻቹለት ቢሆንም እስከዛሬ ድረስ ምንም ሳይከፍል መቆየቱን ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል። “ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች” እንደሚባለው ህወሃቶች በርካሽ ዋጋ ወደስማቸው ያዛወሩትን የመንግሥትና የህዝብ ንብረት ላለፉት 4 አመታት ያህል ሰርተውበት ከግዢው ዋጋ በላይ ትርፍ ያጋበሱበት ቢሆንም በዕዳነት ያለባቸውን የህዝብ ገንዘብ ለመክፈል ፍቃደኛ ያለመሆናቸውን ይህ ለህዝብ ይፋ የሆነው ዘገባ አጋልጧል።
የሳባ ኢንጂነሪንግን ሽያጭና ግዢ በሚመለከት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የኩባንያው ሰራተኛ በሰጡት አስተያየት ሻጭና ገዢ የሆነው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ብቻ ሳይሆን በህዝቦቿና በአገሪቱ ሉአላዊነት ላይ የፈለገውን ደባ ሲፈጽም የነበረ ስለሆነ ከ20 አመት አገዛዝ በኋላ ሥልጣናቸው የሚገረሰስ ስለማይመስላቸው ይፈንዱ ብለው ነው እንዲህ አይነት ዜና ወጣ እንጂ ኢፌርት የሚቆጣጠራቸው ድርጅቶች ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ መገኘታቸውን ህዝብ መቼ ያጣዋል ብለዋል ።
ኤፈርት በአሁኑ ሰዓት የአገሪቱን አብላጫ የንግድ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ባለ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ባለሃብት ኩባንያ ሲሆን የፋሽስቱ መለስ ዜናዊ ባለቤት አዜብ መስፍን በዋና ሥራ አስኪያጅነት የምትመራው ድርጅት እንደሆነ ይታወቃል።