ጉዞ ወደ ምድር ጥግ (ክፍል ሁለት)

ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ ወደ አውሮፕላኑ እንድንገባ ተጋበዝን፡፡ በቀኜም በግራዬም ከፊቴም ከኋላዬም የተቀመጡት የእስያ ዝርያ ያላቸው ተጓዦች ናቸው፡፡ እንዲህ ኤስያውያን በሞሉበት አውሮፕላን ስሄድ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ አስተናጋጆቹ ከዚህ በኋላ ወደ ቀጣዩ መዳረሻችን ለመድረስ የስምንት ሰዓት ከሩብ ጎዳና ይቀረናል አሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌላ አውሮፕላን እንይዛለን፡፡ ድሮ ሦስተኛ ክፍል ስንማር ‹ንብ አበባ ለመቅሰም የምታደርገውን ጉዞ በአንድ መሥመር ብታደርገው ኖሮ፣ ዓለምን ትዞር ነበር› የሚል ነገር ተምሬ ነበር፡፡ አሁንም የኔ ነገር እንደዚያ ሳይሆን አይቀርም፡፡
‹ይህ ነው ምኞቴ እኔ ለሕይወቴ› የሚል የቆየ የማርሽ መዝሙር  ትዝ አለኝ፡፡ እዚያ መዝሙር ውስጥ ደግሞ
ረዥሙን ጉዞ ትግሉን ዐውቄ
ተነሥቻለሁ ትጥቄን አጥብቄ
የሚል ነገር ነበረው፡፡ ምን ይደረግ ሰው ከሀገሩ ሲወጣ ትዝታ ነው የሚተርፈው፡፡ ከወሎ መቄት ወደ አዲስ አበባ መጥተው የኖሩት አለቃ ለማ ኃይሉ አይደሉ እንዴ ቢቸግራቸው ‹‹እግር አዲስ አበባ ልቡና መቄት›› ያሉት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ‹ሀገር ማለት ምንድን ናት?›› ያሰኛል፡፡ በሀገራችን ተሰቃየን፣ ታሠርን፣ ተንገላታን፣ ግፍ ተፈጸመብን ብለው ከሀገር የሚወጡ ወገኖቻችን እንኳን መልሰው ‹ሀገሬ› ሲሉ ሳያቸው ይህቺ ሀገር የምትባል ‹መንፈስ› ምንድን ናት? እላለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ከዋሽንግተን ዲሲ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ከጎኔ አንድ በጎልማሳነት እድሜ ላይ የደረሰ ኢትዮጵያዊ ወገን ተቀምጦ ነበር፡፡ አውሮፕላኑ ሲነሣ እጁ ይንቀጠቀጣል፡፡ ያመመው መሰለኝና ዘወር ብዬ ‹‹አመመህ›› ስል ጠየቅኩት፡፡ ግንባሩን በመሐረብ እየጠረገ ‹‹ደኅና ነኝ፣ ምንም አልል›› አለኝ በእንግልጣር፡፡ አሁንም እጁ ይንቀጠቀጣልና ዘወር አልኩ፡፡

‹‹ይገርምሃል ከሀገሬ ከወጣሁ ሠላሳ ዓመቴ ነው፡፡ ወደ ሀገር ለመሄድ ሳስብ ሁልጊዜ ሰውነቴ ይንቀጠቀጣል፡፡ አንዳች ነገር መጥቶ ይወርረኛል፡፡ ልቤ ምቱ ይጨምራል፡፡ አሁንማ አውሮፕላን ውስጥ ስገባ ባሰብኝ፡፡ ውስጤ ብርድ ብርድ ይለኛል፤ እንደገና ይሞቀኛል፡፡ ምን እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም›› አለኝ፡፡ እያየሁት እገረም ነበር፡፡ ከሕይወቱ አብዛኛውን፤ ያውም ነፍስ ያወቀበትን ዘመን ያሳለፈው አሜሪካ ነው፡፡ ግን ‹ኢትዮጵያ› የሚለውን ሲያስበው አንዳች ስሜት፣ እርሱም የማይገባው ስሜት ይወርረዋል፡፡ ‹‹ሀገር ምንድን ነው?››
ደግነቱ አንድ ወዳጄ ‹‹ዜጋን ከሀገሩ ማስውጣት ቀላል ነው፤ ሀገርን ከዜጋው ልብ ማስውጣት ግን አይቻልም›› ብሎኝ ነበር፡፡ እኛ ልብ ውስጥ ልዩ የሆነች ሀገር አለች፡፡ ማንም የማይነካት፣ ማንም የማይወስዳት፣ ማንም የማያጠፋት፡፡ አለቃ ለማ ‹ልቡና መቄት› ያሉትኮ መቄት ከልባቸው አልወጣ ብላቸው ነው፡፡
ይህንን ሁሉ እያሰብኩ አውሮፕላኑ ተነሥቶ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ አቅጣጫ ማምራት ጀመረ፡፡ እኔም የሕይወት ተፈራን Tower In The Sky አውጥቼ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ያ ትውልድ አሁንም አብሮኝ ሕንድ ውቅያኖስን ሰንጥቆ ሊጓዝ ነው፡፡ ዓላማ፣ ትጋት፣ ቆራጥነት፣ መሥዋዕትነት፣ ጽንዓት የነበረው አንድ ትውልድ ጠፍቷል፡፡
በማርክሲስት ሌኒኒስት ቀንበር ተቀይዶ፣ የሁሉንም ነገር መፍትሔ ከመጻሕፍት ውስጥ ሲያስስ፣ እርስ በርስ ተከራክሮና ተወያይቶ በመተማመን ወይም ባለመተማመን መፍታት ሲቻል፤ ተምሮ እንዳልተማረ፣ ዐውቆ እንዳላወቀ ሲጨራረስ ማየት አሳዛኝ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በሳጥን ውስጥ ብቻ ለመመልከት የሚተጋ ትውልድ የ‹ኢስት› ብዛት፡- ማርክሲስት፣ ማኦኢስት፣ ቾቭኒስት፣ ፌሚኒስት፣ ካፒታሊስት፣ አናርኪስት፣ ፋሺስት፣ ትሮትስኪስት፣ ኮሙኒስት፣›› የ‹ኢዝም› መዓት፡፡ ሁሉንም ሃሳቦች፣ ሁሉንም አመለካከቶች በሳጥኖች ብቻ አድርጎ የመመልከት አባዜ፡፡ ማርክስ፣ ሌኒንና ኤንግልስ የሚባሉ ሐዋርያት ያመጡት አዲስ ሃይማኖት፤ ቦልሼቪስት፣ ማኦኢስት፣ ማርክሲስት የሚባሉ ምእመናን፤ አናርኪስት፣ ትሮትስኪስት፣ የሚባሉ መናፍቃን፤ ኢምፔሪያሊስት፣ ፊውዳልና ቡርዧ የሚባሉ አጋንንት፣ ተፈጥረው አማኝና ከሃዲ ሲወጋገዙና ሲጫረሱ የኖሩባቸው ዘመናት፡፡
መጽሐፉ እያሳዘናችሁ እያስገረማችሁ፣ እያበሳጫችሁም ይጓዛል፡፡ የአንድ ፓርቲ ሰዎች ትናንትም ይከፋፈላሉ፤ ዛሬም እንዲሁ፤ ተከፋፍለውም ይወጋገዛሉ፤ ዛሬም እንዲሁ፤ ተወጋግዘውም ይገዳደላሉ፤ ዛሬም እንዲሁ፤ ለአብዮቱ ሲባል፤ ለትግሉ ሲባል፤ አድኅሮት ኃይላትን ለማስወገድ ሲባል በጓዶች ላይ ርምጃ ይወሰዳል፡፡ ድመት ይመስል አብዮት ልጆቿን ትበላለች፡፡ እስካን አይጥ ለማጥመጃ ስንት መሣሪያ ሲሠራ፤ ምነው ይህቺን ልጆቿን የምትፈጅ ‹የአብዮት ድመት› ማጥፊያ መድኃኒት ጠፋ?
የዚያ ዘመን ሰዎቹ ዐልፈዋል፤ ሥርዓቱ ዐልፏል፤ ታሪኩ ዐልፏል፤ መንፈሱ ግን አለ፡፡ ‹‹ግደል ተጋደል በርታ ወገኔ›› የሚለው ዛር ግን አለ፡፡ ፖለቲካዊ ጽንፈኛነት፤ ደጋፊነትና ጠላትነት፤ ሥር ነቀልነትና ደምሳሽነት አሁንም አሉ፡፡ ይህንን መንፈስ የሚያጠፋ ትምህርት፤ የሚደመስስ ጸሎት፤ የሚያስቀር ሥርየት አልተገኘም፡፡
መጽሐፉን እንዲህ እያነበብኩ እያለ አስተናጋጆቹ ምግብ ይዘው በጎናችን መጡ፡፡ ከጎኔ ላለው ሰውዬ የሰጠችው ምግብ ስሙን የጠራችው በቻይንኛ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የነዚህ የእስያውያን ነገርኮ ምን እንደሚበሉና ምን እንደማይበሉ አይታወቅም፡፡ ቢጨንቀኝ ዓሣ አዘዝኩ፡፡ የመጣውን ነገር አልነግራችሁም፡፡ ምናልባት ምግብ ላይ ትሆናላችሁና ይቅር፡፡ አንድ ወዳጄ ‹‹እነዚህ ሰዎችኮ ሰውን ባሕር ውስጥ ቢያገኙት ዓሣ ነው የሚሉት›› ያለኝ ትዝ አለኝ፡፡ እንኳን ልበላው ኢትዮጵያ የበላሁትም ምግብ ሆዴ ውስጥ ሆኖ እንደ ኤርታሌ ይተራመስ ጀመር፡፡
ከድኜ ተውኩትና መጽሐፉን ቀጠልኩ፡፡ አይ ሕይወት እግዜር ይይልሽ፡፡ ልደታ ብስኩት ቤት፣ ፒያሳ ጮርናቄ ቤት፣ ሐረር ምግብ ቤት፣ ምናምን ክትፎ ቤት እያለች የአዲስ አበባን ምግብ ቤቶችና ሻሂ ቤቶች ትዘረዝራለች፡፡ ይህም አልበቃ ብሏት በመቀሌ መንገድ ላይ ‹‹ምን የመሰለ ዱለት በላሁ›› ትላለች፡፡ እኔ እዚህ በአንድ በኩል የሚዘጋ ምግብ ከፊቴ ተቀምጦ ይተናነቀኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገሬን ምግብ ቤትና ምግብ እያነበብኩ ረሃቤ ይቀሰቀስብኛል፡፡ ተርቦ ስለ ረሃብ ማንበብን የመሰለ ቅጣት መቼም የለም፡፡
ዘሚካኤል ትዝ አለኝ፡፡ ዘሚካኤል ኤርትራዊ ነው፡፡ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ከዐሥራ ሁለት ዓመታት በፊት ባዘጋጀው አንድ ሴሚናር ላይ ለመሳተፍ ተጋብዘን ኡጋንዳ ኢንሴንዜ የምትባል መንደር ተገናኝተን ነበር፡፡ እዚያ ከአሥራ ስድስት የአፍሪካ ሀገሮች የመጡ ወጣቶች ነበሩ፡፡ ከሁሉም የእኔና የዘሚካኤል የምግብ ምርጫ ነበር የሚገርማቸው፡፡ ከምንበላው የማንበላው ይበልጣል፡፡ አንደ ቀን ሴሚናር ላይ ውለን አምሽተን ተመለስን፡፡ እኔ ቀደም ብዬ ጨለም ወዳለው የማምሻችን ቦታ መጣሁ፡፡ እሳት ነድዶ ጨዋታው ቀልጧል፡፡ ዘሚካኤል መታጠቢያ ቤት ገብቶ ዘገየ፡፡ ስደርስ የሆነ ነገር ሸተተኝ፡፡ አሻግሬ ሳይ ጠረጲዛው ላይ ያለውን ነገር ይሻሙበታል፡፡ በጨለማው ውስጥ ያለው የእሳት ብርሃን ብቻ ስለነበር ልለየው አልቻልኩም፡፡ ራቅ ብዬ ተቀመጥኩ፡፡
ዘሚካኤል መጣና ጠረጲዛ ላይ ያለውን ነገር አየው፡፤ ‹‹ዘቢብ ሳይሆን አይቀርም›› አለኝ፡፡
‹‹አይ እኔ ይቅርብኝ አንተ ሞክረው›› አልኩት፡፡
‹‹ዘቢብ መሆን አለበት፤ መልኩ እንደዚያ ነው›› አለና ሊያመጣ ሄደ፡፡ ልክ ጠረጲዛው ጋ ሲደርስ ‹‹ቧ፣ አተ›› አለና ፈጠን ፈጠን ብሎ ወደ ማደሪያው ገባ፡፡ ምን ሆነ ብዬ ደነገጥኩና ተከተልኩት፡፡ ባንኳኳ ባንኳኳ አልከፍትም አለ፤ በስንት መከራ ሳስከፍተው ፊቱ በውኃ ርሷል፡፡
‹‹ምን ሆነህ ነው?›› አልኩት
‹‹ጉድ ሠሩኝኮ›› አለኝ
‹‹ምን አደረጉህ››
‹‹ምን እንደሆነ ዐውቀሃል››
‹‹ምንድን ነው?››
‹‹የተጠበሰ ክረምት አግባ›› በሳቅ ፈረስኩ፡፡ ለካስ እንደ ዘቢብ አምሮ የታየው እኛ ክረምት አግባ የምንለውን ሰብስበው ቆልተውት ነው››
ዛሬ የደረሰብኝ በዘሚካኤል በሳቅኩት ግፍ ነው፡፡
ከዱባይ ወደ ብሩናይ መንገድ፣ ሕንድ ውቅያኖስ ላይ