ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን
የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ
- ከ15 – 20 ዓመት በሚያስቀጡ ቅርስን የማፍረስ፣ ከባድ የእምነት ማጉደል እና ሐሰተኛ ሰነድ የመፍጠር የወንጀል ተግባራት ይፈለጋሉ
- ‹‹ተራማጁ እና ልማታዊው›› በሚል የሚሞካሹት ቆሞሱ በመንበረ ጵጵስና ብፁዕ አቡነ ቄርሎስን የመተካት ምኞት ነበራቸው፤ በቀድሞው ዘመነ ፕትርክና ሁለት ጊዜ በሲሞናዊ መንገድ ለኤጲስ ቆጶስነት ለመታጨት ሞክረዋል፤ በውጭ ጉዟቸው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራውን ሲኖዶስ ማኩረፊያ አድርገውት ይኾን?
- ሙሰኝነታቸውንና የአስተዳደር በደላቸውን የሚቃወሙ ካህናትንና የመንግሥት ሓላፊዎችን በዞን፣ ክልልና ፌዴራል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስሞች በማሸማቀቅ ይታወቃሉ፤ የማስፈራሪያ ስሞቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር አማካሪ ሚኒስትር አቶ በረኸት ስምዖንን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን አቶ ደመቀ መኰንን፣ የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትና የግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ሓላፊ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውንና የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳዳሪን አቶ ጸጋ አራጌን ይጨምራል
- በተለያዩ የደመወዝ መክፈያ ቅጾች በወር ከብር 13,000 በላይ ይከፈላቸዋል፤ ለግል ጉዳያቸው በሚሄዱባቸው ቦታዎች ሁሉ ብር 200 ዕለታዊ አበል ይታሰብላቸዋል
- ደብሩ በ1.4 ሚልዮን ብር የገዛው የመካነ ልዕልት ካፌና ሬስቶራንት በ4.5 ሚልዮን ብር እንደተገዛ ተደርጎ ለጠቅ/ቤተ ክህነት ሪፖርት ቀርቧል፤ መካነ ልዕልት በሚባለው ቦታ ለሚሠራው የእንግዳ መቀበያ/ገስት ሃውስ/ በ8 ሚልዮን ብር የቀረበ ተጫራች እያለ 10 ሚልዮን ብር ያቀረበው ሥራ ተቋራጭ አሸናፊ ተደርጓል፤ ለደብሩ በስጦታ የተበረከተው የመቶ ሺሕ ብር ትርፋማው ሰባት ወይራ ሆቴል በአስተዳዳሪው ደብዳቤ ለጠቅ/ቤተ ክህነቱ ተላልፎ መሰጠቱ እየተነገረ ነው
- ከቤተ ደናግል ቤተ መቅደስ ጋራ አብሮ የተሠራው የደንጊያ መንበር ተነቅሎ ወደ ቤተ አብርሃም ሆቴል ተወስዶ ‹‹ሲጃራ መተርኰሻ እና መጠጥ ማቅረቢያ›› ኾኗል፤ በቤተ መድኃኔዓለም እና ቤተ ዐማኑኤል አቅራቢያ የነበሩና ከአብያተ መቅደሱ ጋራ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ አራት የሣር ቤቶች ‹‹ተቃጥለው›› የተወሰደ ርምጃ የለም
- ደብሩ ከቱሪዝም፣ ከሆቴሎች መስተንግዶ እና ሌሎች የልማት ተቋማት ከ7 -14 ሚልዮን ብር ዓመታዊ ገቢ ያገኛል የሚል ሪፖርት በአስተዳዳሪው የስንብት ንግግር እየቀረበ ባለበት ኹኔታ ቤተ ገብርኤል፣ ቤተ ጊዮርጊስ፣ ቤተ ጎልጎታ እና ቤተ መርቆሬዎስ በከፋ የመፈራረስ አደጋ ላይ ናቸው፤ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ዐማኑኤል እና ቤተ አባ ሊባኖስ በዩኔስኮ ላስቲክ ‹እንደተጠለሉ› ነው!
- በቃለ ዐዋዲው ከታዘዘው የሦስት ዓመት ገደብ በተፃራሪ አምስተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ተጨማሪ ስድስት ወራት እንዲሰጠው በአስተዳዳሪው የስንብት ንግግር ተጠይቆለታል፤ በሕዝብ ያልተመረጡ አባላት የሚበዙበት ሰበካ ጉባኤው ከአስተዳደር ሠራተኞች የተሻለ ሥልጣን የሌለው የአስተዳዳሪው ፈቃድ ፈጻሚ ነው፤ የደብሩ ሒሳብ በውጭ ኦዲተር እንዲመረመር ሲቀርብ የቆየውን ጥያቄ እንኳ በቅጡ የሚያስፈጽመው አልተገኘም
- የደብሩን ችግር አጣራኹ ያለው የመንበረ ፓትርያሪኩ አጣሪ ልኡክ የስምሪት ሪፖርቱን ማቅረብ ተስኖታል፤ የልኡኩ አባል የኾኑት የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መጋቤ ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ፣ የቅ/ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስ መኰንን ‹‹ወደ ከፍተኛው ማዕርግ ቢደርሱማ ኑሮ የሰማይ መና ሳያወርዱ አይቀሩም ነበር›› በማለት የኤጲስ ቆጶስነት ተስፋቸውን በጋዜጣው አጯጩኸውላቸዋል
