የበቅሎ ጥያቄ


በከበደ ሚካኤልኛ እንዲህ ይተረካል፡፡
አንዲት ግልገል በቅሎ እናቷን እንዲህ ብላ ጠየቀቻት፡፡ ‹‹እማዬ እኔ ግን ማነኝ››
እናቷም ገረማትና ‹አንቺማ በቅሎ ነሽ፤ ግን ለምን ጠየቅሽኝ››
ግልገሏም ጥቂት ጊዜ ዝም ብላ ከቆየች በኋላ ‹‹መጀመሪያ ግን አህያ ነበርኩ ወይስ ፈረስ›› አለቻት፡፡ እናቲቱም አንገቷን ነቅንቃ፡፡ ‹‹እንስሳ ነሽ ልጄ፤ እንስሳ፡፡ ፈረስም አህያም እንስሳ ነው፡፡ ስንፈጠር እንስሳ ነበርን፡፡ የቤት የዱር፣ የሸክም የግልቢያ፣ የእርሻ የሜዳ፣ የንጉሥ የባሪያ የሚለው በኋላ የመጣ ነው፡፡ አዳምኮ ሲፈጠር ቤት አልነበረውም፡፡ ስለዚህ የቤት እንስሳ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ሁላችንም ይህቺን ምድር እንደልባችን እንጠቀምባት ነበር፡፡ ነገር የመጣው በኋላ ነው፡፡ ለመኖር የሚደረግ ትግል ነው ይህንን አሁን ያለንበትን ሁኔታ የፈጠረው፡፡››
‹‹ጓደኛዬ የአንቺ አያቶች ጨቁነውናል አለኝ፡፡››

 ‹‹እንዴት አድርገው ነው የጨቆኑት፤ ለመሆኑስ የአንቺ አያቶች ስንት ናቸው? እርሱ የተነገረውን ብቻ ነው የሚያውቀው፤ ያልተነገረውስ? ከታሪካችንኮ በጣም ጥቂቱ ነው የተጻፈው፤ ከተጻፈውም በጣም ጥቂቱ ነው የተነገረው፡፡ ባልተጻፈው ታሪካችን ውስጥ ማን ምን እንደነበረ ማን ያውቃል? ለምሳሌ በሀገረ እሥራኤል አህዮች እጅግ የሚወደዱ የቤት እንስሳት ነበሩ፡፡ ነገሥታቱም፣ ካህናቱም፣ ነቢያቱም ዘመኑ ዘመነ ሰላም ሲሆን በአህያ ነው ይሄዱ የነበሩት፡፡ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በአህያ ነው፡፡ ድንግል ማርያም ወደ ግብጽ የተሰደደችው በአህያ ነው፡፡ በጥንታውያን ግብጾች ዘንድ አህያ የመኳንንትና የነገሥታት ሀብት ማሳያ ነበር፡፡ የናርማር ወይም  ሖር – አሃ መቃብር እንደሆነ በሚታመነው ቦታ ላይ በተደረገ ቁፋሮ አህዮች ከነገሥታቱ ጋር በክብር ተቀብረው ተገኝተዋል፡፡ በዚያ ጊዜ አህዮች የቤተ መንግሥቱን ምግብ እየተመገቡ፣ በቤተ መንግሥቱም እየተሸለሙ ኖረዋል፡፡ በሌላው ዘመን ደግሞ ይህንን ፈረሶቹ ወስደውታል፡፡››

‹‹ወደ ኋላ ተመልሰሽ ሁሉን እንስሳት ብታያቸው ታሪካቸው እንደዚሁ ነው ልጄ፡፡ በዘርሽ አትጨቁኝም፤ በዘርሽም አትጨቆኝም፡፡ የጭቆና መሠረቱ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ አቤልን የገደለውኮ ቃየል ነው፡፡ የአንድ ማኅፀን ልጆች ናቸውኮ፡፡ ቃየል አቤልን የገደለው ለጥቅም ሲል ነው፡፡ እስኪ የሰዎችን ታሪክ እይው አፍሪካውያንኮ በራሳቸው በአፍሪካውያን ይጨቆኑ ነበር፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ሰው መሰሎቹን ይሰበስብና ሌሎቹን የሀገሩን ልጆች ይጨቁናል፡፡ መጀመሪያ የገዛ ወገኖቻቸውን ለዐረቦች በባርነት ሲሸጡ የነበሩት የሀገራቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ አፍሪካውያን በባርነት ተሽጠው አሜሪካ ሲሄዱ ደግሞ ነጮቹ ጥቁሮቹን መጨቆን ጀመሩ፡፡ አየርላንዳውያን በእንግሊዞች መከራቸውን አይተዋል፡፡ ዓረቦች በዓረቦች ተሰቃይተዋል፡፡
አየሽ ቤተ መንግሥቱ ላይ ስትቀመጭ ሌላውን ለማግለል ሳጥን ትከፍቻለሽ፤ ከዚያ ሁሉንም በየሳጥኑ ታስቀምጭዋለሽ፡፡ የእምነት፣ የዘር፣ የመልክ፣ የአካባቢ፣ የቋንቋ ሳጥኖችን ከፍተው ሁሉንም እዚያ ስላስቀመጧቸው ተቀማጮቹ ሳጥኑን እንዳለ ተቀበሉት፡፡ ማንነታቸውም አደረጉትና ሳጥኑን ለማስቀረት ከመታገል ይልቅ ራሳቸውን ብቻ ከሳጥኑ ለማውጣት ይታገሉ ነበር፡፡ በሳጥኑ ዛሬ አህዮች ይገቡበታል፤ ነገ ፈረሶች፣ ከነገወዲያ ግመሎች፣ ከዚያም በጎች፣ ከዚያም ፍየሎች እየገቡበት ይቀጥላል፡፡ እኛም ዛሬ ያለሳጥን መኖር ከማንችልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ እኔን ሲያገኙኝ እንስሳ መሆኔን አይደለም የሚያዩት፤ የትኛው እንስሳ? ይላሉ፡፡ – ፈረስ፡፡ በዚህ አያቆሙም፡፡ ከዚያ ደግሞ የትኛው ፈረስ? የዱር ወይስ የቤት? ይቀጥላል፡፡ -የቤት፡፡ ለጭነት ወይስ ለግልቢያ? መቋጫ የለውም ልጄ፡፡ በትልቁ ሳጥን ውስጥ ራሳችን የሠራናቸው ትንንሽ ሳጥኖችም አሉ፡፡ በእነዚያም ውስጥ ሌሎች ትንንሽ ሳጥኖች አሉ፡፡››
‹‹ ለአንድ የገጠር ጉዞ በእኔ ላይ ይሄድ የነበረ አንድ ሰው ሲናገረው የሰማሁትን ታሪክ ልንገርሽ፡፡ ሰውዬው የከባድ መኪና ሾፌር ነበረ፡፡ ድሮ አሰብ እየተመላለሰ ዕቃ ይጭን ነበር፡፤ አንድ ጊዜ ወደ አሰብ ሲሄድ በረሃው ላይ መኪናው ይበላሽበታል፡፡ ከዚያም እዚያው ማደር ስለነበረበት ለምግቡ የሚሆን ፍየል ከአካባቢው የአፋር ሰው ይገዛል፡፡ አፋሩ ሰውዬው ፍየሏን መሸጥ ብቻ ሳይሆን አርዶ፣ ጠብሶ ያቀርብለታል፡፡ ሾፌሩ ምግቡን እየበላ የሸጠለትን የአፋር ሰው ‹‹እንግዲህ ትቼህ መብላቴ ነው፤ እንብላ እንዳልልህ የክርስቲያን ሥጋ አትበላም ብዬ ነው›› ይለዋል፡፡ አፋሩ ሰውዬ ይገርመውና ‹‹እኔው አዋልጄ፣ እኔው አሳድጌ፣ እኔው አርጄ፣ እኔው ጠብሼ ያመጣኋትን ፍየል ምንጊዜ ክርስቲያን አደረግካት?›› አለኝ ብሎ ሲያወራ ሰማሁት፡፡ አየሽ ሌላን ማግለል ስትፈልጊ የሆነ ነገር ትፈጥሪያለሽ፡፡ ማቅረብም ስትፈልጊ እንደዚያው፡፡››
‹ብዙ ዓይነት ነጻ አውጭዎች አሉ፡፡ እኔ አሁን የፈረስ ነጻ አውጭ ውስጥ ልግባ ወይስ የአህያ? ወይስ የበቅሎ?›› አለቻት ግልገሏ፡፡
‹‹የእንስሳት ነጻ አውጭ ካለ እዚያ ግቢ፡፡ አንቺ እንስሳ ነሽ፡፡ የቀረው ከመኖር የመጣ ስም ነው፡፡ እንስሳት ሁሉ ነጻ ሳይሆኑ በቅሎ ተለይታ ነጻ ልትሆን አትችልም፡፡ አንድን አካቢ ብቻውን ንጹሕ ማድረግ አትችይም፡፡ ምክንቱም ዝንቧ ከወዲያኛው ማዶ ትመጣለችና፡፡ ከእኛም ወገኖችኮ ሜዳ በመኖራቸው የተነሣ ‹የሜዳ ፈረስ›› ተብለው የቀሩ አሉ፡፡ እኛ ከሰው ተጠግተን ‹የቤት ፈረስ›› ለመሆን ቻልን፡፡ ‹‹የቤት አህዮች›› አሉ፡፡ ‹‹የሜዳ አህዮች›.ም አሉ፡፡ የስም ጉዳይ ነው፡፡ የአኗኗር ጉዳይ ነው፡፡ በቤተ መንግሥት ከነገሥታት ጋር የሚኖር አንበሳ ነበርኮ፡፡ የነገሥታቱ ዙፋን እንዲያውም የአንበሳ ቅርጽ ነበረው፡፡ በዚያው ዘመን ግን ንጉሡ ጫካ ወጥተው ሌላ አንበሳ ገድለው እየተዘፈነላቸው ይመጣሉ፡፡ ጀርባሽን ለመጋለብ ምቹ ካደረግሽው ምንጊዜም የተሻለ ተወዳጅ ትሆኛለሽ፡፡ እንግሊዞች ‹‹Better to ride on ass that carries me, than on a horse that throws me – የምትገለብጠኝን ፈረስ ከምጋልብ፣ የምትሸከመኝን አህያ ብጋልብ ይመረጣል›› ይላሉ፡፡
ቤት የቀረው ውሻ ዱር ከቀረው ውሻ ጋር በመለያየታቸው ዛሬ አንዱ አንዱን እንደ ጠላት ያባርረዋል፡፡ ሰው ብልጥ ነው፡፡ አንዱን ወደራሱ አቅርቦ ውሻ አደረገውና ‹‹ቦቢ›› እያለ በማቆላመጥ ነጻ የወጣ አስመሰለው፡፤ ሌላውን ደግሞ ቀበሮ፣ ተኩላ ብሎ ጫካ ተወውና እርሱን መግደል ጀግንነት እንዲሆን አደረገው፡፡ አሁን ውሾቹ የሠለጠኑና ነጻ የወጡ መስሏቸው ተኩላና ቀበሮ ሲያብርሩ ይኖራሉ፡፡ አየሽ ጉዳዩ የዘር አይደለም፡፡ በዘር ከሰው ተኩላ ለውሻ ይቀርበዋል፣ ቀበሮ ይዛመደዋል፡፡ ጉዳዩ የጥቅም ጉዳይ ነው፤ የመደብ ጉዳይ ነው፡፡ ከቀበሮውና ከተኩላው መካከል ደግሞ የተወሰነውን ይወስዱና ፓርክ ውስጥ አስገብተው ያለፈለት ያስመስሉታል፡፡ እርሱም ማግኘት የሚገባውን ሳይሆን ራሱን ከጫካው ኑሮ ጋር ስለሚያነጻጽር ‹ተመስገን› እያለ ይኖራል፡፡››
‹‹ነጻነት የፍጡር ሀብት ነው፡፡ ለእነ እገሌ ተብሎ የሚቆረስ አይደለም፡፡ ጨቋኙም ተጨቋኙም ነጻ ካልወጣ ሙሉ ነጻነት አይገኝም፡፡ ጨቋኝነት ከአስተሳሰብ ባርነት የሚመጣ ነው፡፡ ከአመለካከት ድህነት የሚከሰት ነው፡፡ ሙሉ ነጻነትን ለማግኘት እርሱን ነጻ ማውጣት አለብሽ፡፡ ካልሆነ ግን ጉዞው አንዱን ጨቋኝ በሌላ ጨቋኝ መተካት ነው የሚሆነው፡፡ አፍሪካውያንኮ ራሳቸውን ከአውሮፓውያን ነጻ ማውጣት አላቃታቸውም፡፡ ያቃታቸው ራሳቸውን ከራሳቸው ነጻ ማውጣት ነው፡፡ ነጭ ጨቋኞች በጥቁር ጨቋኞች ተተኩ፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ ሳጥኑን ካላጠፋሽው ታግሎ ከሳጥኑ የወጣው ሁሉ በፋንታው የተሸነፈውን እርሱ ወደወጣበት  ሳጥን መክተቱ የማይቀር ነው፡፡
‹‹ደግሞስ ለምን በማትቀይሪው ነገር ጊዜሽን ታጠፊያለሽ? አሁን አንቺ በቅሎ ሆነሻል፡፡ አለቀ፡፡ ከእንግዲህ አህያ፣ ፈረስ፣ አንበሳ፣ ጅብ ፣ ድመት ልትሆኝ አትችይ? መሆን ለምትፈልጊው ነው መታገል ያለብሽ? በእጅሽ ላይ ላሉት ዕድሎች ነው መታገል ያለብሽ፤ ልትለውጫቸው ለምትችያቸው ዕድሎች ነው መታገል ያለብሽ፤ ልታሸንፊያቸው ከምትችያቸው ነገሮች ጋር ነው መታገል ያለብሽ፡፡ ትናንትን በነገ ለመቀየር ታገዪ፤ ትናንት ውስጥ ገብተሸ ግን እቀይረዋለሁ አትበዪ፤ መጀመሪያ አንቺ ራስሽ ከትናንቱ ውጭ፤ ያ ያለፈ ነገር ነው፡፡ ታሪክ አይታረምም፤ ሆኗልና፡፡ በታሪክ ውስጥ የተፈጠረ ችግር ግን በቀጣይ ታሪክ ይታረማል፡፡ ምን ሆነ? የሚለው አይለወጥም፤ ምን ይሁን? የሚለውን መለወጥ ግን ይቻላል፡፡ ዛሬ ላይ ሆነሽ የመጣሽበትን ማስተካከል አትችይም፤ የሚትሄጅበትን ግን ትችያለሽ፡፡ ብዙዎቹ ነጻ አውጭዎች ትናንትን ነጻ ለማውጣት የተቋቋሙ ናቸው፡፡ አንቺ መግባት ያለብሽ ነገን ነጻ ሊያወጣ የተቋቋመ አካል ከተፈጠረ ብቻ ነው፡፡
‹‹አፍሪካውያን ‹‹until the lions have their own historians tales of hunt will always glorify the hunters- አንበሶች የራሳቸው ታሪክ ጸሐፊዎች እስኪኖሯቸው ድረስ ስለ አደን የሚጻፈው ታሪክ ሁሉ ምጊዜም አዳኞችን የሚያገንና የሚያከብር ይሆናል›› ይላሉ፡፡ ዛሬ ከአንድ ወገን ብቻ እየሰማን የምንፈርዳቸው ፍርዶች በታሪክ ተሠሩ ከምንላቸው ስሕተቶች በላይ እንድንሳሳት የሚያደርጉን ናቸው፡፡ የማናውቃቸውና ያልሰማናቸው፤ ምናልባትም ወደፊትም ልንሰማቸው የማንችላቸው ታሪኮችም አሉን፡፡ ትናንት ያለፈ በመሆኑ ለፍርድ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሰሎሞን ዴሬሳ የተባለ ሰው ‹አንተ ዘርህ ምንድን ነው?› ሲባል ‹‹በቅድመ አያቴ ደጅ ማን እንዳለፈ እኔ ምን ዐውቃለሁ›› ይል ነበር፡፡ በአንቺስ ቅድመ አያት በር ማን እንዳለፈ ምን ታውቂያለሽ? መጠኑና ዘመኑ ይለያያል እንጂ ‹ሌላ› የሚለውን አካል ሳይገድል፣ ሳያጠፋ፣ ሳይጨቁን፣ ሳይቀማ እዚህ የደረሰ የለም፡፡ ግን ታሪክ እንደተራኪው ነው፡፡
‹‹ሁላችንንም መከራውና ግፉ፣ ጭቆናውና የደረሰብን ነገር ሁሉ አስተባብሮናል፡፡ በየዘመናቱ ቤተ መንግሥቱን የተጠጋ ተሸልሟል፡፡ አምሮበታል፡፡ ሌላውን ለማስገበርም ዘምቷል፡፡ እኛ አህዮች፣ ፈረሶችና በቅሎዎች ነንኮ ሌሎች እንስሳት እንዲታደኑ አብረን ከሰዎች ጋር የዘመትነው፡፡ በእኛ ዘምተው ሌላ ሀገር የሚገኙ ፈረሶችንና አህዮችን እንዲዘርፉ አድርገናልኮ፡፡ ከዘመቻው በኋላ ለእኛ የተሻለ ነገር ጣል ሲደረግልን እነርሱ ግን በባዶ ሜዳ አድረዋልኮ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ለእኛ እነርሱ ይቀርቡን ነበር፡፡ ነገር ግን ቤተ መንግሥቱን ስትጠጊ እንዲህ አታስቢም፡፡ በታሪካችን ውስጥ የደረሱብንንና ያደረስናቸውን ብንቆጥራቸው ከምንለያይበት የምንመሳሰልበት ይበልጣል፡፡ ግን ምን ያደርጋል ከሳጥኑ ወጥቶ የሚያስብ የለም፡፡ ሳጥኑ ውስጥ ስትሆኚ ደግሞ ያንቺ ብቻ ነው የሚታይሽ፡፡
‹‹መቼም በእንስሳት ታሪክ ቀደምት ከሚባሉት አንደኛዎቹ ቲቤታውያን ናቸው፡፡ እንዲህ ይላሉ ‹‹አንጥረኛው ጥበበኛ ከሆነ ብረትና ነሐስ ሊዋሐዱ ይችላሉ››፡፡ አሁንም እኛ አንድ ልንሆን ያልቻልነው አንድ የሚያደረግን ነገር ስለሌለ ሳይሆን አንድ የሚያደርገን ጥበበኛ አንጥረኛ ስለሌለ ነው፡፡ እስኪ ተመልከቺው፤ ቤተ መንግሥት የኖረውን አንበሳኮ ነው ‹‹አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መጨዋቻ ይሆናል›› የሚሉት፡፡ ታድያ ከጫካው አንበሳ ምን የተለየ ነገር አገኘ? የቤት አህያም ሆነ የጫካ አህያ ሲያረጁ ሁለቱንም አውሬ ይበላቸዋል፡፡ ቤት ውስጥ የኖረውም ውሻ ሲያረጅ ዞር ብሎ የሚየው የለም፡፡ ስለዚህ ልጄ አሁን የሚያስፈልገን የእገሌ ነጻ አውጭ ድርጅት ሳይሆን ‹የአስተሳሰብ ነጻ አውጭ ድርጅት›› ነው፡፡ አስተሳሰብሽ ነጻ ሲወጣ ‹‹መጀመሪያ እኔ እንስሳ ነኝ ወይስ በቅሎ?›› የሚለውን ጥያቄ ራስሽ ትመልሽዋለሽ፡፡
ሲድኒ፣ አውስትራልያ