በከፍተኛ ሙስና የተጠረጠሩት የደብሩ ዋና ጸሐፊ በኀምሳ ሺሕ ብር ዋስ ተለቀቁ
- የደብሩ ምእመናን በፍ/ቤቱ ውሳኔ ግራ ተጋብተዋል
- ዋና ጸሐፊው ከሥራቸው ታግደዋል፤ በምትካቸው ሌላ እንዲመደብ ተጠይቋል
በሰነድ ማጭበርበር እና ሰነድ ማሸሽ በተፈጸመ ከፍተኛ ሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ምሩፅ ትኵዕ በኀምሳ ሺሕ ብር ዋስትና መለቀቃቸው ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት የደብሩ ዋና ጸሐፊ በኀምሳ ሺሕ ብር ዋስትናቸው ተጠብቆ እንዲወጡ ትእዛዙን የሰጠው ከጊዜ ቀጠሮ በፊት በተጠርጣሪው ጠበቃ ለችሎቱ በቀረበ አቤቱታ መኾኑ ተገልጧል፡፡
ችሎቱ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ሐምሌ ፲፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ለተጠርጣሪው የፈቀደው የዋስትና መብት፣ ዋና ጸሐፊው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ በዋናነት እና በተባባሪነት እንደፈጸሟቸው የተጠረጠሩባቸውን ሕገ ወጥ ድርጊቶች የሚያስረዱ ሰነዶች ከቢሯቸውና ሌሎች ቦታዎች በፖሊስ ፍተሻ መሰብሰባቸውን በምክንያት የተጠቀሰበት መኾኑ ተዘግቧል፡፡
ዋና ጸሐፊው ዲያቆን ምሩፅ ከተያዙበት ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ረፋድ ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ከቆዩበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ በአጀብ ወደ ቢሯቸው እየመጡ በተካሄደው ፍተሻ ሊያሸሿቸው አስበዋል የተባሉ የሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራ ቃለ ጉባኤዎችን ጨምሮ ለምርመራ ሥራ የሚጠቅሙ ሰነዶች መሰብሰባቸው ተነግሯል፡፡
ይህም ሐምሌ ፲፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ተጠርጣሪው በችሎቱ በቀረቡበት ወቅት ፖሊስ ‹‹ማስረጃ ያጠፋሉ፤ ምስክር ያባብላሉ›› በሚል የዋስትና ማመልከቻቸውን በመቃወም የጠየቀባቸውና ፍ/ቤቱ የፈቀደለት የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተሠብሮ ከጊዜው ቀጠሮ በፊት በዋስትና እንዲወጡ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡
ዲያቆን ምሩፅ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ይውጡ እንጂ፣ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤልን የፋይናንስ እንቅስቃሴና አሠራር በመመርመር ላይ የሚገኙ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት እና የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ልኡካን የማጣራት ሥራቸውን ከሚሠሩበት ቢሯቸው ትውር እንዳይሉ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ መወሰኑ ታውቋል፤ ውሳኔውንም እንዲያስፈጽሙ ለደብሩ ጠቅላላ አገልግሎትና የጥበቃ ሓላፊ የቃል መመሪያ መተላለፉ ተገልጧል፡፡ ከዚሁ በማከታተል አስተዳደሩ የደብሩ ጽ/ቤት ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ ተተኪ ዋና ጸሐፊ እንዲመድብለት ሀ/ስብከቱን በደብዳቤ መጠየቁ ነው የተሰማው፡፡
በዲያቆን ምሩፅ ላይ የተላለፈው እግድ ከፖሊስ የምርመራ ሂደትና የፋይናንስ እንቅስቃሴውን ከሚያጣሩት ልኡካን ሥራ ጋራ የተያያዘ እንደኾን የጠቀሱ የደብሩ ምንጮች፣ በአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ መሠረት እግዱ ከአንድ ወር በላይ ሊዘልቅ ስለማይችል የምርመራው መዳረሻና የማጣራቱ ውጤት በደብሩ ሀብት መመዝበር ተቆርቁረው አቤቱታ ሲያቀርቡ በቆዩ ወገኖች ሁሉ ዘንድ በተስፋ የሚጠበቅ ያደርገዋል ይላሉ፡፡
ሌሎች አስተያየት ሰጭዎች ሙስናን ከመዋጋት አንጻር ከመንግሥትም ይኹን ከቤተ ክህነት የወጡትን መግለጫዎች በመጥቀስ፣ ዋና ጸሐፊው በተጭበረበረ ሰነድ በፈጸሙት የኪራይ ውል ደብሩን ያሳጡትን የሦስት ሚልዮን ብር ገቢ እና የሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ቆጠራ ቃለ ጉባኤዎችን በማሸሽ ከጥቅመኞቻቸው ጋራ ሊያካብቱ የሚችሉትን ከፍተኛ ገንዘብ በማስላት ፍ/ቤቱ የዋስትና መብት መፍቀዱ ግራ እንዳጋባቸው ይናገራሉ፡፡ ተጠርጣሪው ‹‹ይረጫሉ›› ከሚሉት የገንዘብ መጠንና ይነግዱባቸዋል ከሚሏቸው አንዳንድ ድሉል የጸጥታ ኀይሎች አንጻርም በምርመራው/ማጣራቱ ሂደት ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉ፣ የሰው ምስክሮችንም ሊያባብሉ አልያም ሊያስፈራሩ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

