የሚኒሶታ ደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በከፋፋዮች ሴራ አትናወጥም!!! – ለአንድነት ከቆሙ ምእመናን

በስመ ሥላሴ አንድ አምላክ አሜን!
የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘርና በኃይማኖት በመከፋፈል እኩይ አላማውን በተለያየ መንገድ እያራመደ ያለው የወያኔ ‘መንግስት’ የተለመደውን የዘረኝነትና የከፋፋይነት ተግባሩን በተለይ በውጪ አገራት በሚገኙ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሚገለገልባቸው አብያተ ክርስቲያናትና ኮሚኒቲዎች በማተኮር በውጪው ዓለም የአልሞት ባይ ተጋዳይነት መፍጨርጨር እያደረገ ይገኛል። ይህ በውጪው አለም እየደረሰበት ያለውን ኪሳራ ለማስቆም ሲል ተቃዋሚ በመምሰል ሰርጎ በመግባት፣አንዳንዶችን በጥቅም፣ አንዳንዶችን በመደለል፣ የዋሃንንም በማጭበርበር ሰላምና አንድነትን ለመበጠበጥ የማቆፍረው ጉድጓድ የለም።

ከዚህ አንጻር በተለይ መውጪው አገር የሚገኘውን 90% ምእመን በማገልገል ላይ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት በማመስና በመከፋፈል የስደተኛውን ሕብረትና አንድነት በማናጋትእየደረሰበት ያለውን ተቃውሞ ለማብረድ ሲንፈራገጥ ይስተዋላል።

በቅርቡ በታላቋ ርእሰ አድባራት ለንደን ቅስት ማርያም ቤተክርስቲያን የተፈጸመውን አሳዛኝ ሁኔታ ስንመለከት የምንገነዘበው ይህንኑ እውነታ ነው። እርሱ ራሱ የፈጠረውን የቤተክርስቲያን አባቶች መከፋፈል እንዲያው በተዓምር የተከሰተ ጉዳይ በማስመሰል ለስልጣንና ለሹመት ባዘጋጃቸው ከሐዲያን መነኮሳትና ካሕናት እንዲሁም አንዳንድ ጥራዝ ነጠቅ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችና የዋሐን ምእመናን አማካይነት በውጪው አለም ምሳሌ የሆነቸውን ቤተክርስቲያን ለሁለት በመክፈል በታላቁ አብይ ጾም እንድትዘጋ/እንድትታሸግ/ በማድረግ በታሪክ የማይረሳ አሳፋሪና አስነዋሪ ተግባር በሆዳም መነኩሴና ጀሌዎቻቸው እንዲፈጸም አድርጓል። ይህም መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻል በሚል የተጀመረው ጉዳይ የወያኔና የእግዚአብሔር የሆኑትን ለይቶ በማውጣት የተጠናቀቀ ቢሆንም በሌሎች አድባራትና ቦታዎች ግን እንዳይደገም ነቅቶ መጠበቅ ይገባል።

ከዚህ አንጻር ይኸው ምእመናንን የመከፋፈል እግዚአብሔር የማይወደው ሥራ አሁን ደግሞ ትኩረቱን በታላቋና ዝነኛዋ የሚኔሶታ ደብረሰላም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ በማዞር ቤተክርስቲያኗን ለመከፈልና ሰላሟን ለመንሳት አሁንም አንዳንድ ባልገባቸውና በየዋሕነት በሚነዱ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና አንዳንድ ካህናት የሚደረገውን ቅስቀሳ የቤተክርስቲያኗ ተገልጋዮችና መላው የአካባቢው ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊያወግዘውና የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ ሊቃወመው ይገባል እንላለን። ባለፈው ግንቦት 25 ቀን 2005/ጁን 2 2013 ዓ.ም. በተደረገው የቤተክርስቲያኗ አጠቃላይ ጉባኤ የዚህን አሳፋሪ ሴራ አራማጆች በማሳፈር እንደታየው ያለ የማያዳግም የመጨረሻ ውሳኔ በመስጠት ሰላማችንን የምንጠብቅበት ጊዜም በቅርቡ ስለሚገለጽ ለዚሁ ከወዲሁ ዝግጁ በመሆን እንድትገኙ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በቤት ለቤትና በተለያዩ መገናኛ መንገዶች ይህንን የሐሰት የወያኔ ቤተክርስቲየን የውስጥ ጉዳይ መግባት ለማስተባበልና ምእመናንን ለመከፋፈል የሚንቀሳቀሱትንም ግለሰቦች በማጋለጥ እንድትተባበሩ እንጠይቃለን። አሁን በቤተክርስቲያን አካባቢ ያለው መለያየት የተፈጠረው ከላይ እንደተገለጸው ወያኔ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና በመጣስ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ በመሾሙ ምክንያት የመጣ እንጂ ከቤተክርስቲያን ሥርዓት የወጣ አንዳች ነገር እንደሌለ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል። ይኽም የቀኖና ጥሰት ካልተስካከለ ወይንም በእርቅና ሰላም ሂደት መፍትሔ ካላገኘ አሁን ሁለት የተከፈሉትን አባቶች በመደገፍ የሚመጣ ለውጥ ስለማይኖር መደገፍም ካለበት አጥፊውንና የችግሩ መንስዔ የሆነውን ሳይሆን እውነትን ብቻ መሆን ስለሚገባው ማወናበዳቸውን ሁላችንም ልናስቆመው ይገባል እንላለን።

በተጨማሪም ከቤተክርስቲያኗ መተዳደሪያ ደንብ ውጪም በመሆን ቤተክርስቲያኗን አሁን የምትተዳደርበት ባይሎው በመጻረር እንቅስቃሴ የሚያደርጉትንም አንዳንድ የቤተክርስቲያኗ ተቀጣሪ ካህናትና ዲያቆናት በማጋለጥ በሕግ ውለታቸውን ያፈረሱ መሆናቸውን የምንጠይቅና ርምጃ እንዲወሰድ ማንኛውንም ሕጋዊ መንገድ የምንጠቀም መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ልንገልጽ እንወዳለን።

የሚኒሶታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ምእመናንም በአገራችን ላይ ከደረሰብንና በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ካለው ግፍና ሰቆቃ አልፎ ወያኔ የጥፋት እጁን አዚህ ድረስ ዘርግቶ ይህን ያህልም መደፈራችን ሊያስቆጨንና ባንድነት እንድንነሳ ሊያደርገን ይገባል። ቤተክርስቲያናችንን ብቻ ሳይሆን ልጆቻችንም የወያኔን የተዛባና የክህደት ታሪክ እንዲማሩና ስርአት አልበኝነትን እንደትክክለኛ አካሔድ እንዲቀበሉ ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ ስለሆነ ይህንን ጉዳይ በጥብቅ ልንቃወመው ይገባናል። ልጆቻችን ሊያውቁት የሚገባው እውነተኛውን የኢትዮጵያና የቤተክርስቲያን ታሪክ ነው። ልናስተላልፍላቸው የሚገባውም ፓትርያክ እያለ ፓትርያርክ እንደማይሾም ይህ አይነቱ ድርጊትም ወደፊት በዘመናቸው ቢያጋጥማቸው እምቢ እንዲሉና እንደ እኛም እንዲቃወሙ እንጂ አድርባይና ሆድ አደር እንዲሆኑ አይደለም። የቀደሙት አባቶቻችን የእነ አቡነ ጴጥሮስ ታሪክ ይሔው እምቢ ባይነት ለኃይማኖትና ለሀገር ነጻነት መሰዋት ነውና። በዚያን ጊዜ ብዙ ሆድ አደር ካህናትና ምሁራን እንደነበሩ ነገር ግን ታሪክና አገር በአክብሮት የሚያስታውሳቸው ለኃይማኖታቸውና ለሀገራቸው ነጻነት ሰማእትነት የተቀበሉትን እንጂ ባንዳዎችን እንዳልሆነ አበክረን ልንነግራቸው ይገባል።

እውቁ የኢትዮጵያና የቤተክርስቲያን ታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በዚህ በቤተክርስቲያን አባቶች መለያየት ዙሪያና መፍትሔው በቅርቡ በሰጡት አስተያየት እንዲህ ብለዋል

‘‘ ችግራችን በአንድ ዘመን ሁለት ፓትርያርኮች መኖር ነው– በአንድ አካል ላይ ሁለት እራስ።
ፓትርያርኮቹ አንዱ ኢትዮጵያ አንዱ አሜሪካ ሆነው፥ “ያንኛውን ትታችሁ እኔን ተከተሉ”
ስላሉን ግራ ተጋባን። ግማሾቻችን አንዱን፥ ግማሾቻሻችን ሌላውን ተከተልን፤ ሌሎቻችን
ማንንም አልተከተልንም። ሆኖም፥ የአንዱ ፓትርያርክ ተከታይና የሌላው ፓትርያርክ ተከታይ
ወይም ገለልተኛው የሃይማኖት ወንድማማቾችና እትማማቾች ናቸው። እንዲያውም ቤተ
ክርስቲያን “ቤተ ክርስቲያን” የምትባለው ሕዝበ ክርስቲያኑን (ኤክሌሲያን) ለማመልከት ነው።
“ጉባኤ፡ ዘሐዋርያት፡” (የሐዋርያት ስብስብ) የተባለችውም ስለዚህ ነው።
ካህናቱ ከላይ እስከ ታች ልኡካን (ጸሎት በመምራትና ሃይማኖት በማስተማር ሕዝበ ክርስቲያኑን
እንዲላላኩ የተላኩ) ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ፥ “ሁላችሁም የክርስቶስ ምእመናን ስለሆናችሁ፥
እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ እኔ የአጵሎስ ነኝ ማለታችሁን ትታችሁ በክርስቶስ አንድነታችሁን ጠብቁ
ስላለን ከውዝግቡ ውስጥ በወገንተኝነት መግባትና ለውዝግቡ ሕይወት መስጠት የለብንም።
ይህ ብቻ ሳይሆን፥ በመብታችን ተጠቅመን መፍትሔ መፈለግና ውዝግቡን ማብረድ ግዴታችን
ነው። መፍትሔ ከተወዳዳሪዎቹ አይጠበቅም። ሆኖም፥ ያልተከፈለች አንድ ቤተ ክርስቲያን
ሁለት ፓትርያርክ ሊኖራት ስለማይገባ፥ አንዱን ብቻ እንከተላለን። ያንን ማድረግ
የምንችለው፥ በስሜትና በምኞት ሳይሆን፥ የችግሩ መንሥኤ ግልጽ ሲሆንልን ነው።”

ካሉ በኋላ መፍትሔውንም ሲጠቁሙ

‘‘ የተቃውሞ ዘዴያችን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፥ ማለት፥ በእኛ በምእመናኑ ላይ፥ የፈራነውን መከፋፈል የማያመጣብን መሆን አለበት። የአዲስ አበባው ፓትርያርክ ሲሞቱ ብዙዎች
(የስደተኛው ፓትርያርክ ደጋፊዎች ሳይቀሩ) ችግሩ የፓትርያርክ ጉዳይ ወይም ወያኔዎች የሞቱ
መስሏቸው፥ ቀና መፍትሔ ተጠባብቀው ነበር። እዚያም ሆነ እዚህ፥ ፓትርያርክ ሲሞት
ፓትርያርክ ሊተካ እንደሚችል ልብ አላሉትም። ችግር የፈጠረብን የወያኔ ኀይል መሆኑን
ሁላችንም ካመንበት፥ መፍትሔው ያንን ኀይል ማስወገድ ብቻ ነው። ስለዚህ ፥
መዓቱ እስኪያልፍ ድረስ፥ ቅዱስ ገብርኤል “ንቁም፡ በበህላዌነ፡” እንዳለው፥ ባለንበት ነቅተን
እንጽና፤ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ነፃነት ተባብረን በአንድነት እንሥራ።’’

ስለሆነም በድጋሚ ሁሉም ሊያጤነው የሚገባው አሁን ያለው መለያየት የሚያበቃው የችግሩ ፈጣሪ ሲወገድና ያበው አባቶች አንድነትና እርቅ ሲደረግ ብቻ መሆኑን ነው። ስለሆነም በጳጳሳት አበው መካከል የተከሰተውን መለያየት ለመፍታትና እርቅና ሰላም እንዲወርድ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ የነበሩ ታላላቅ የቤተክርስቲያኗን ልጆች ጥረት ፍጻሜ እንዳያገኝና የተላኩት ልኡካን እንኳን ተመልሰው ሪፖርት ሳያቀርቡ ለሆድ ያደሩና ለስልጣን የቋመጡ ‘ጳጳሳት ከአለቃቸው ወያኔ ጋር በመሆን ጥረቱን ያመከኑ ስለሆነ ከእነኝህ ሰላምን እምቢ ካሉ ‘አባቶች’ ጋር ‘አንድነት’ እያሉ ከሚያላዝኑ የቤተክርስቲያንንና የምእመናንን ሰላም ከሚያውኩ ወገኖች ሁላችንም እንጠንቀቅ።
ያዕ. 4፥7. እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ አሜን!