አንድነት በጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ የኢህአዴግ መደናገጥ ተባብሷል – ፍኖተ ነጻነት

አንድነት ፓርቲ ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ.ም. በደሴ ያደረገውን ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ትናንት ሐምሌ 16 ቀን 2005ዓ.ም. ደሴ በሚገኘው በወሎ ባህል አምባ አዳራሽ የተለያዩ የኃይማኖት አባቶችን ሰብስበው አንድነት ፓርቲ ያደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ቆራርጦ በአዳራሽ ውስጥ በማሳየት የኃይማኖት አክራሪነት ይደግፋል የሚል የማጥላላት ዘመቻ ማድረጉን ተሳታፊ ምንጮቻችን በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ የተጠሩት ታላላቅ የኃይማኖት አባቶችም የተጠሩት ስለሀገራዊ በተለይም ስለ ኃይማኖታዊ ጉዳይ ለመወያየት እንደነበር እንደተነገራቸው እንጂ ስለአንድነት ሰልፍ እንዳልነበር አስታውሰው ሁኔታውን በግርምት መታዘባቸውና ማዘናቸውም ተጠቁሟል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ በላይ አንድነት ፓርቲ በደሴ ባደረገው የተሳካ ሰላማዊ ሰልፍ ጋር በተያያዘ ከስልጣናቸው መውረዳቸው የተገለፀ ሲሆን እስካሁን የት እንደተመደቡ ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍልም ጉዳዩን ለማረጋገጥ የከተማው ከንቲባ አቶ አለባቸው የሱፍ ጋር እና ከስልጣናቸው ተነሱ ተባሉት የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ በላይ ጋ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ብንደውልም አልተሳካም፡፡