ጉዞ – ወደ ምድር ጥግ( ክፍል አንድ)

ከአዲስ አበባ ወደ አውስትራልያ ልጓዝ ነው፡፡
ትነሣላችሁ የተባልነው ከምሽቱ አራት ሰዓት ከ15 ነበር፡፡ ‹ነበር› ካልኩ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ የመሳፈሪያው አዳራሽ ውስጥ ተቀምጠን ግን የመሳፈሪያው ሰዓት በረረ፡፡ ሰዓቱ እኛን ጥሎን በሌላ አውሮፕላን ይብረር፣ ወይም የመሳፈሪያውን ሰዓት ያደረገው የአየር መንገዱ ሠራተኛ ሳይመጣ ይቅር የታወቀ ነገር የለም፡፡ ደግነቱ የአየር መንገዱም ሠራተኞች የተሰጣቸው መመሪያ ‹‹የመሣፈሪያ ሰዓት ካለፈ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ሳታስነቁ ወዲያ ወዲህ ማለት ነው› የሚል ሳይሆን አይቀርምና አንዳቸውም ምን አልተነፈሱም፡፡
መቼም ኢትዮጵያ ውስጥ መረጃ ለማግኘት የሚታወቅ መንገድ (system) ስለሌለ የሚታወቅ ሰው መፈለግ ነው፡፡ አንዱን የማውቀውን ሰው ጠጋ ብዬ ስጠይቀው ለንደን ላይ አውሮፕላናችን መጠነኛ ችግር እንደገጠመው ሹክ አለኝ፡፡ ምናልባት በዚያ ተደናግጠው ይሆናል ብዬ ይቅር አልኳቸውና መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላም ሕዝቡን ወደ ስታዮም እንደሚገባ ተመልካች አንጋግተው ይዘውት ወረዱ፡፡ ‹‹ሕጻናት ያላችሁ፣ የቢዝነስ ክፍል አባላት፣የሼባ ማይልስ የወርቅ አባላት›› ብሎ ነገር የለም፡፡ ‹‹እየየ ሲዳላ ነው›› አሉን፡፡ የሰው ጎርፍ ወደ ታችኛው ፎቅ በደረጃው ፈሰሰ፡፡ 

በአውቶቡሱ በኩል ተሸጋግረን ወደ አውሮፕላኑ ገባን፡፡ የመቀመጫ ለውጥ እንጂ የሰዓት ለውጥ አልነበረውም፡፡ ለነገሩ ብዙ ጊዜ በሀገሪቱ የመቀመጫ ለውጥ ነው የሚመጣውና አልተገረምንም፡፡ ‹መሣፈሪያ አዳራሹ ውስጥ መቀመጥ ሰለቸን› ያልናቸው ይመስል አውሮፕላኑ ውስጥ አንድ ሰዓት አስቀመጡን፡፡ ደግነቱ አብራሪው እየደጋገመ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ከተለያየ ሀገር የሚመጡ ተሸጋጋሪ መንገደኞች እየተጠበቁ መሆኑንም ይነግረናል፡፡ መቼም የመጣውን አስቀምጦ ያልመጣውን መጠበቅ የተለመደ ነውና አላዘንኩበትም፡፡ ሠርግም ላይ፣ ስብሰባም ላይ፣ ጉባኤም ላይ፣ ግብዣም ላይ በሰዓቱ አክብረው የመጡት የዘገዩት እስኪመጡ እንዲጠብቁ በሚደረግበት ባህል ውስጥ ስላለን የሚገርም አይደለም፡፡
ከመቅረት መዘግየት ይሻላል ብሎ አውሮፕላኑ ወደ ዱባይ ተነሣ፡፡ ከጎኔ አንዲት እንደኔ አፍሪካዊት የሆነች፣ እንደ እኔ ግን ኢትዮጵያዊት ያልሆነች ሴት ተቀምጣለች፡፡ እርሷ እቴ ወደ አውሮፕላኑ እየገባች ሳይሆን አይቀርም ዕንቅልፍ የጀመራት፡፡ ደግሞ ስፋቷ ለሚኒ ባስ ታክሲ የመጨረሻው ወንበር እንጂ ለአውሮፕላን ወንበር የሚሆን አይደለም፡፡ ከመደገፊያው ተርፎ እኔ ጋ እየመጣ አስቸገረኝ፡፡ ሦስት ትራስ ደራርባ፣ በዚያ ላይ ፎጣ መሳይ ነገር ለብሳ ትለጥጠዋለች፡፡
እኔን መከራ ያሳየኝ ዕንቅልፏ አይደለም፡፡ እየተረፈ የሚመጣው ሰውነቷ አልበቃ ብሎ እንደ ፔንዱለም ስትወዛወዝ ትከሻየ ላይ እየመጣች ዘፍ የምትለው ነገር ነው፡፡ ሴትዮዋ የመጣችው ‹ሶሪ› ከሌለበት ሀገር ነው መሰለኝ ትከሻዬን ገጭታው ስትመለስ ከጥቁሩ ፊቷ መካከል ብልጭ የሚል ባለ ቀይ ድድ ጥርሷን ብቻ አሳይታኝ ‹ካለፈው የቀጠለ› ብላ ወደ ዕንቅልፏ ትገባለች፡፡ ትቆይና ደግሞ ክላሲካል ትለቃለች፡፡ ‹‹ፉርርርርርር›› የሚል የኩርፊያ ክላሲካል፡፡
መቼም በዚህ ክላሲካል ታጅቦ እንኳን ዕንቅልፍ መተኛት ቅዠት መቃዠትም አይቻልምና ከያዝኳቸው መጻሕፍት አንዱን አወጣሁ፡፡ ‹‹የአሲምባ ፍቅር›› የሚል ካሕሣይ አብርሃ በተባለ የኢሕአሠ(የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ሠራዊት) ታጋይ የተጻፈ መጽሐፍ፡፡ መጽሐፉ ከሥነ ጽሑፍ አንጻር ብዙ የሚቀሩት ነገሮች ቢኖሩም የዚያን ዘመን ወጣቶች ታሪክ በማሳየት አንጻር ግን ማራኪ ነው፡፡  መቼም ሰው በአውሮፕላን ሲሄድ አውሮፕላኑ እንዳይወድቅ እንጂ ከአውሮፕላኑ ውስጥ ሰው እንዳይወድቅ የሚሰጋ አይመስለኝም፡፡ እኔ ግን አንድ ገጽም ሳላነብብ በቀኝ ትከሻዬ በኩል የሆነ ነገር ዘፍ አለብኝና ሰጋሁ፡፡ ተጠንቅቄ ዘወር ስል ሴትዮዋ ሳታስፈቅደኝ ትከሻዬን ተንተርሳዋለች፡፡ እንደምንም ታግዬ ሳስለቅቃት ነቅታ ጥርሷን ብልጭ ታደርግና ዕንቅልፏን ከተቋረጠበት ትቀጥላለች፡፡
አሁን ምን ተብሎ ይጸለያል? እኔ እስካሁን በቀኝ ትከሻ በኩል ዘፍ ለምትል ሴት መከላከያ የሚሆን ጸሎት የነገረኝ ሰው የለም፡፡ ከኔ መለስ ሳደርጋት በወዲያኛው በኩል ወደተቀመጠው ፈረንጅ ሄዳ ዘፍ አለች መሰል ‹ኦ ማይ ጎድ› ሲል ሰማሁት፡፡ ‹‹እስኪ ያንተ ጸሎት ከሠራ እኔም እጠቀምበታለሁ›› ብዬ ጠበቅኩት፡፡ ሲብስበት ጊዜ ከወንበሩ ተነሥቶ ወደ መጸዳጃ ቤት አመራ፡፡ የፈረንጅ ነገር፣ ለሁሉም ችግር ወደ መጸዳጃ ቤት ነው፡፡ ‹ከአፍርንጅ የምንለይበት›› የሚለው የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሀገራችን መጽሐፍ ትዝ አለኝ፡፡   
‹‹የአሲምባ ፍቅር›› የዚያ ዘመን ወጣቶች ለሀገራቸው የነበራቸውን ፍቅር፣ ለነጻነት የነበራቸውን ታጋይነት፣ ላመኑበት ነገር ይከፍሉት የነበረውን መሥዋዕትነት፣ በሌላው ዓለም ያዩትንና ያነበቡትን በሀገራቸው ለማምጣት የነበራቸው ሕልም፣ ለአብዮት የነበራቸውን ጽኑ ፍቅር ያሳያችኋል፡፡ ያንን የመሰለ ትውልድ በጦርነት፣ በእሥርና በግድያ፣ በስደትና በጉስቁልና ማጣት ሀገሪቱን ምን ያህል እንደ ጎዳት ታዩበታላችሁ፡፡ ውጊያና ትግል፣ ስብሰባና ግምገማ፣ ኮንፈረንስና የእርምት ንቅናቄ፣ ተሐድሶና የፖለቲካ ትምህርት፣ ቋንቋው የነበረ አንድ ትውልድ እንዴት እንደጠፋ ትታዘባላችሁ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአመራር እጦት፣ የብስለት መጥፋት፣ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያላስገባ የትግል ስልት፣ የግለሰብን ነጻነት ያጠፋ ቡድናዊ አምባ ገነንነት፣ ችግሮችን ሁሉ በመሣሪያ አፈሙዝ ለመፍታት የነበረው አመለካከት፣ ራስን በምሁራዊ አምባ ላይ አስቀምጦ ሌላውን የመናቅ አባዜ፣ ከተማ ላይ ተቀምጦ የገጠርን ትግል የመምራት ድንግርግር፣ በሀገሪቱ ትውልድ ላይ ያመጣውን ምስቅልቅልም ታያላችሁ፡፡
እነዚህን መሰል መጻሕፍት ሳነብ እጅግ የሚገርመኝ ነገር ያ ትውልድ ፈጽሟቸዋል ብለን የምናስባቸው ስሕተቶች ዛሬም እንደገና እየተመላለሱ መፈጸማቸው ነው፡፡ አሁንም ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ስንሞክር፣ አሁንም ድርጅቶች፣ ማኅበራት፣ ፓርቲዎች ከግለሰብ ነጻነት በላይ ሲሆኑ፣ አሁን የፓርቲ መሪዎች ችግሮችን በመከፋፈልና በመለያየት ሲፈቱ፣ አሁንም ሕዝብና ፀረ ሕዝብ፣ አንድነትና ፀረ አንድነት፣ አብዮታዊና ሊበራል፣ ኮሙኒስትና ካፒታሊስት የመከፋፈያ መሣሪያዎቻችን ሲሆኑ፣ አሁንም በጠላት መቃብር ላይ ሕንጻ የመሥራት አባዜ አልለቀን ሲል፣ አሁንም የተቃራኒያችንን አመለካከት ለማዳመጥ ትዕግሥት ሲያንሰን፣ ምን ያህል ከዚያኛው ዘመን ስሕተት እንዳልተማርን ያሳዩናል፡፡
ተዋጊዎቹ ወጣቶች በአንዳንዶቹ ውጊያዎች አይስማሙም፣ በአንዳንዶቹ ውጊያዎች ደግሞ ከአመራሮቻቸው ተቃራኒ የሆነ መረጃ አላቸው፣ ፓርቲውና ድርጅቱ እየተሳሳተ ያዩታል፣ ስሕተቶቹ የሚያስከፍሉትን ዋጋ በርግጠኛነት እያገኙት ነው፤ ነገሮች እንደማይሁኑ ሲሆኑ እየታዘቡ ነው፤ በተሳሳተ አመራር፣ በተሳሳተ የመፍትሔ ጉዞ፣ በተሳሳተ አሠራር የተነሣ ውድ የሀገሪቱ ልጆች ሕይወታቸውን ከጎናቸው ሲሠው እያዩ ነው፡፡ ነገር ግን ድርጅት፣ ፓርቲ፣ አመራር የሚባሉት ሰዎች አይሳሳቱም፣ እነርሱ ያሉት ሁሉ ቅዱስ ነው፣ እኔ ካየሁት ያላየው አመራር ይበልጣል፤ እኔ ስሕተት መሆኑን ባውቅም ፓርቲው ትክክል ነው ካለ ትክክል ነው፤ ሁለትና ሁለት ተደምሮ አራት የሚሆነው ፓርቲው ወይም ድርጅቱ አራት ነው ካለ ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን ሦስትም አምስትም ሊሆን ይችላል ብሎ የማሰብ አባዜ ዋጋ ሲያስከፍል እናያለን፡፡ ዛሬም ግን ይሔው አስተሳሰብ በዚህች ሀገር ውስጥ ሥሩን ተክሎ ቅጠል አውጥቶ፣ አብቦና አፍርቶ እየታየ ነው፡፡ ካለፈው ተምሮ እርሱን ለማረም የሚተጋ አይታይም፡፡
አውሮፕላናችን ሁለት ሰዓት ያህል ዘግይቶ ዱባይ ገባ፡፡ እኔ ዱባይ የገባሁት ቀጣዩን አውሮፕላን ለመያዝ 15 ደቂቃ ብቻ ሲቀረኝ ነው፡፡ ምድር ከወረደ በኋላ የበረራ አስተናጋጆች የተወሰን ሰዎችን ስም ጠርተው ውጭ የአየር መንገዱን ሰዎች እንድናነጋግር አሳሰቡን፡፡ እሺ ብለን ስንወጣ አገኘናቸው፡፡ የሆነች ወረቀት ሰጡንና እንዲህ ያለ ቦታ ሄዳችሁ የሆነ ሰው ታገኛላችሁ ሩጡ አሉን፡፡ መቼም አበበና ማሞ፣ ምሩጽና መሐመድ ከድር፣ ኃይሌና  ቀነኒሳ ከተወለዱበት ሀገር የመጣን ነን ብለን ወደተባለው ቦታ ሮጥን፡፡ ሲዖል ይዘጋላችሁና የነገሩን ቦታ ሁሉ ዝግ ነው፡፡ አንዳች ሰው በአካባቢው የለበትም፡፡ ‹አይ አየር መንገዳችን፤ እነ ክበበው ገዳ የት ሄደው ነው እርሱ እንዲህ ያለ ቀልድ የሚቀልደው› ብዬ ተገረምኩ፡፡ ማንን እናናግር፡፡ በኋላ አንድ የአውሮፕላን ማረፊያውን ፖሊስ አገኘነውና ችግራችንን ስንነግረው በፍተሻ ማለፊያው በኩል አድርጎ ወደ ምድር ቤት ወሰደን፡፡
 ምድር ቤት ወርደን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መስኮት ስንደርስ እነርሱ ምን አለባቸው አራት ሆነው ቁጭ ብለዋል፡፡ ‹‹ምናለ አንዳችሁ እንኳን እዚያ ተገኝታችሁ ብትረዱን›› አልኳቸው፡፡ ‹‹እገሊትኮ ነበረች›› አሉን፡፡ ትኬታችንን ተቀብለው አየት አደረጉና ‹‹አሁንማ ረፍዷል ቀጣይ አውሮፕላን ካለ እንይላችሁ›› አሉን፡፡ ለእነርሱ እየተባበሩን ነው፡፡ ስሕተቱን የፈጸሙት እነርሱ፣ የዘገዩት እነርሱ የምንቀጣው እኛ፡፡ እንዴው ግን እስከ መቼ ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የደንበኞቹ ግንኙነት የባላባትና የጢሰኛ የሚሆነው? በባላባቶች ፍርድ ‹‹ምን ባላባት ቢያጠፋ ጢሰኛ ይክሳል›› ይባላል፡፡ አየር መንገዳችንም እንዲህ ሆነብንኮ፡፡ ‹‹ይቅርታ፣ እስኪ ዐረፍ በሉ፣ ችግሩን እንፈታዋለን›› ከአማርኛችን ውስጥ የሌሉ ይመስል ምነው ከአንደበታቸው አልወጣ አሉ?
‹‹እናንተ ባጠፋችሁ ቁጥር እኛ መቀጣት አለብን?›› አልኳቸው ኃላፊ የመሰሉትን ሴትዮ፡፡ምንም አልመሰላቸውም፡፡ ከሌላው አየር መንገድ ጋር በስልክ ተነጋገሩ፡፡ ደግነቱ ያኛው አውሮፕላን አርፍዷል፡፡ ‹‹ትደርሳላችሁ ሂዱ አሉን፡፡›› ሄድን፡፡ እንደተባለውም ደረስን፡፡ ዛሬ ከአየር መንገዳችን ጋር የሚወዳደሩም የሚፎካከሩም አየር መንገዶች በበዙበት ጊዜ እንዲህ በደንበኞች አገልግሎት ላይ መቀለድ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ለአየር መንገዳችን ኃላፊዎች ደጋግሞ ማሳሰብ ይገባል፡፡ የያዛችሁት አየር መንገድ ‹የኢትዮጵያ› ነው፡፡ የእናንተ አይደለም፡፡ እናንተ በምትፈጥሩት ስሕተት ግን የምትቀጣው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ዛሬ እነ አልጀዚራ ስለ ኢትዮጵያ የሚወራ ክፉ ነገር ፍለጋ አሰፍስፈው በሚጠብቁበት ዘመን እናንተ ተባባሪ ሆናችሁ ክፉ ዜና የምትሰጡበትን ምክንያት እንኳን እኛ እናንተም የምታውቁት አልመሰለኝም፡፡
አሁን ከዱባይ ወደ ብሩናይ ለመጓዝ በሮያል ብሩናይ አውሮፕላን የመንገደኞች ማስተናገጃ ክፍል እገኛለሁ፡፡ ‹‹ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም›› ይባል ነበር፡፡ እዚህ ግን ፉርሽ ተደረገ፡፡ አየር መንገዳችን ያቃለለንን መንገደኞች የብሩናይ አየር መንገድ ሰዎች ጋብዘውና ተከባክበው ካሱን፡፡ ‹‹ብሩናይ የሚባል ስም ከዚህ ጉዞ በፊት ሰምቼ አላውቅም፡፡ በዙሪያየ የተቀመጡት እስያውያን ናቸው፡፡ ሰውነታቸው ቀጨጭ፣ ዓይናቸው ሰለምለም፣ ልብሳቸው ደመቅመቅ፣ ፀጉራቸው ወረድረድ ያሉ ሕዝቦች፡፡ በአካባቢው ያለሁት አፍሪካዊ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ከዐርባ ደቂቃ በኋላ እንነሣለን ተብሏል፡፡ እስኪ ቀጣዩን መንገድ ደግሞ ሰላም ያድርገው፡፡
ዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ዐረብ ኤምሬት