አቡጊዳ – የኢትዮጵያ ወታደር በሱዳን ሰላም አስጠባቂ ሊሆን ነዉ !

በቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ታቦ ኤምቤኪ ሸምጋይነት ደቡብና ሰሜን ሱዳን በድንብሮቻቸዉ መካከል ያለዉን ዉጥረት ለማርገብ፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሰላም ጠባቂ ኃይል ሆነዉ እንዲሰማሩ መስማማታቸዉን ብሉምበር ኒዉስ ዘገበ።

የደቡብ ሱዳን ህዝብ ከስድስት ወራት በፊት ባደረገዉ ሕዝበ-ዉሳኔ ከሱዳን ለመገንጠል መወሰኑ ይታወቃል። በሕዝበ-ዉሳኔዉ መሰረት ደቡብ ሱዳን ከአንድ ወር በኋላ ነጻነቷን ታዉጃለች ተብሎ ሲጠበቅ ፣ ከወዲሁ በደቡብና በሰሜን ሱዳን መካከል የድንበር ግጭቶችም እየተከሰቱ ነዉ። ወደ ባሰ ጦርነት ዉስጥ ይዘፈቃሉ የሚል ትልቅ ስጋት ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰሙ ነዉ።

በደቡብ እና በሰሜን ሱዳን ድንበር ላይ የሚሰማሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች የተባበሩት መንግስታት ወታደሮች ሆነዉ የሚያገለግሉ ሲሆን፣ በሱዳን ቆይታቸዉም ደሞዛቸዉንና ወጪያቸዉን የተባበሩት መንግስታት እንደሚችል ይነገራል።

ከአራት አመታት በፊት፣ ያኔ በእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሥር አንጻራዊ መረጋጋትና ሰላም የነበራትን ሶማሊያ፣ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት እንዲወር ፣ የኢሕአዴጉ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ፣ ማድረጋቸዉን ያስታወሱት ያነጋገርናቸዉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ «የሱዱኑ ተልእኮ ከሶማሊያዉ የተለየ ነዉ። በሶማሊያ ሰላም የነበረን ሁኔታ ነዉ መለስ ዜናዊ ያደፈረሰዉ። ይኸዉ ከእስላማዊ ፍርድ ቤቶች የባሰ ሽብርተኛ ቡድን በግዛታችን ድንበር እንዲያብብ ነው ያደረገዉ። መዘዙ ገና ብዙ ነዉ። በሱዳን የታሰበዉ ግን ሰላማዊና ለአካባቢዉም የሚጠቅም ነዉ” ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ዉሳኔንና የደቡብና ሰሜን ሱዳን ስምምነትን በአዎንታዊነት ይመለከቱታል።

የተባበሩት መንግስታት ለኢትዮጵያ ወታደሮች ቢያንስ በወር ከ17 ሺህ አምስት መቶ ብር (100 ዶላር) በላይ ደሞዝ የሚያስብ ሲሆን ፣ ወታደሮቹ ለነርሱ የተመደበዉን ደሞዝ የሚያገኙ እንደሆነና እንዳልሆነ ግን የሚታወቅ ነገር የለም። ከዚህ በፊት በዉጭ አገር በሰላም ጠባቂነት ያገለገሉ ወታደሮች፣ የተባበሩት መንግስታት ለነርሱ የመደበላቸዉን ገንዘብ የኢሕአዴግ መንግስት በእጅጉ ቀንሶ እንደከፈላቸው፣ በዚህ ምክንያት አንዳንድ ተቃዉሞዎች ተነስተዉ እንደነበረ ያታወቃል።

በተለያዩ አገራት የሚኖሩ እንደ አምባሳደር ግርማ ያሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በዶላር ፐር ዳይም እንደሚከፈላቸዉ፣ የሚኖሩበትን ቤት፣ ለልጆቻችዉ ትምህርት ክፍያ እና የተለያዩ ወጪያቸዉን የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚሸፍ የሚናገሩ ብዙ ናቸዉ። ከዲፕሎማሲ ሥራም ዉጭ አገር የሚገኘዉን ኢትዮጵያዊ ለመሰለል በርካታ በዶላር የሚከፈላቸው ካድሬዎች እንዳሉ ይነገራል።

እነዚህ በዉጭ አገር የሚኖሩ ሲቪል የመንግስት ሰራተኞችና ካድሬዎች አስፈላጊዉን እንክብካቤ እያገኙ፣ በሌላ በኩል በሰላም ጠባቂነት የሚያገለግሉ፣ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተዉ በበረሃና በጫካ የሚሰማሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ግን፣ የተባበሩት መንግስታት የሚመድብላቸዉን ዋጋ የኢሕአዴግ መንግስት ቀንሶ አሁንም ሊሰጥ ይችላል ተብሎ ይገመታል።

«ነገሩ በአንድ በኩል ለመለስ ቢዝነስ ነዉ። ለአንድ ወታደር በወር ከሚመደበዉ ምንም ሳይደክም፣ ሰባት ሺህ ከፍሎ አሥር ሺህ ወደ ኪሱ ያገባል። ለምሳሌ አንድ ሺ ወታደሮች ቢሰማሩ፣ በአንድ ወር በቀላሉ 10 ሚሊዮን ብር መለስ ዜናዊ ያገኛል። በአመት መቶ ሃያ ሚሊዮን ብር ይደርሳል » ያሉን ያነጋገርናቸው ተንታኝ፣ ድርጊቱን የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊትን ክብርና አስተዋጽኦ የሚያቃልልና የሚያጣጥል እንደሆነ ያስረዳሉ።