‹‹ታች በሌ››
የዛሬ ሃያ ዓመት ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ እንደተመረቅኩ የመምህርነት ሥራዬን የጀመርኩት እነዋሪ በምትባል በሰሜን ሸዋ ውስጥ ከምትገኛና ከአዲስ አበባ 165 ኪሎ ሜትር በምትርቅ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ እነዋሪ ከመርሐቤቴ እስከ ዜና ማርቆስ የሚኖረው ቆለኛና ደገኛው ጅሩዬ የሚገናኙባት የቀለጠች የገበያ ከተማ ናት፡፡ በተለይም በፍራፍሬ ምርቷ ትታወቃለች፡፡ ኤፍሬም እሸቴ የእነዋሪን ሙዝ ‹ከማጠሯ መጎጠሯ› እያለ ይቀልድባት ነበር፡፡
ከእነዋሪ እየተነሣሁ እስከ ዠማ ወንዝ ድረስ ለሠርግም፣ ለንግሥም ቆላውን እወርድ ነበር፡፡ ገበሬዎቹ ከቆላው ይመጡና እኔን በቅሎ ላይ አውጥተው በትከሻቸው ላይ ውጅግራ ጠበንዣቸውን ደልደል አድርገው ተሸክመው የጋቢያቸውን ግማሽ ጠቅልለው አናታቸው ላይ በማስቀመጥ፣ ከግራና ከቀኝ በቅሎዋን እየነዱ፣ ያንን እንደ ያሬድ መዝሙር በጆሮ የሚንቆረቆረውን ወጋቸውን እያወጉ፣ እንደ ዝንጀሮ ገደሉን በኩራት ይወርዱታል፡፡ ተረታቸው፣ ቀረርቷቸው፣ ፉከራቸው፣ ዘፈናቸው፣ የታሪክ ትረካቸው፣ ስለ ጀግኖቻቸው የሚገጥሙት ግጥም አሁንም በጆሮዬ እንደ መስክ ነፋስ ሲያልፍ ይሰማኛል፡፡
አንድ ቀን ታድያ አይዋ ሰጥ አርጌ የሚባሉ ቆፍጣና ገበሬ አብረውን ወደ ዠማ ሲጓዙ ታች በሌ ስለሚባል ሽፍታ አወጉኝ፡፡ ታች በሌ በተለይ በሞረቶች ዘንድ በጣም የታወቀ አስቂኝ ሽፍታ ነው፡፡ አንድ ሰው ያላሰበበትን፣ ያልተዘጋጀበትንና ያለ ዐቅሙ የሆነውን ነገር ጀመረ ሲባል ዠማዎች ‹‹ምን የእርሱ ነገርኮ የታች በሌ ሽፍትነት ነው›› ይሉታል፡፡ አንድ ሰው በስሜት ብቻ ተነሣስቶ እንዴው የጀብደኛነትን ሥራ ሲሠራ፣ አንድን ነገር አስቦ ከመሥራት ይልቅ ከሠራ በኋላ ሲያስብ ዠማዎች እንዲሁ ‹ታች በሌ› ይሉታል፡፡ ለምን?
ታች በሌ የዠማ ሰው ነው፡፡ የኖረው ከዛሬ ሁለት መቶ ዓመት በፊት በሸዋው አስፋ ወሰን ዘመን ነው አሉ፡፡ በዚያ ዘመን ሞረትን ይገዙት የነበሩት ጥዱ የተባሉ ኃይለኛ በላባት ነበሩ፡፡ እንዲያውም ጥዱና አስፋ ወሰን እርስ በርሳቸው የሚፎካከሩም የሚፈታተኑም ኃይለኞች ስለነበሩ ግጥሞቻቸው ዘመን ተሻግረው ደርሰውናል፡፡ አስፋ ወሰን ሞረትን ማስገበር ስለፈለጉ
ለሞፈር ለቀንበር የሚሆነኝን
ሳልቆርጠው አልቀርም ዘንድሮ ጥዱን፤
ብለው ለአዝማሪ ነገሩ አሉ፡፡ ይህን የሰሙት ጥዱም
አስፋ ወሰን ይፋት ጠንክረው ይረሱ
ሞረት ጥዷል ብለው ከሚመላለሱ፤
ብለው መለሱላቸው ይባላል፡፡
ጥዱ ኃይለኛ አስገባሪ፣ አስጨንቆ ገዥ ነበሩና ብዙ ገበሬዎችን እንደ ሰም አቅልጠው፣ እንደ ብረት ቀጥቅጠው፣ እንደ ጫማ ረግጠው ይገዙ ነበር፡፡ ከተገዥዎቹ ገበሬዎች አንዱ የነበረው ታች በሌ መረረው፡፡ በልጅነቱ በሰሜን ሸዋ በረሃዎችና ጫካዎች ሸፍተው ገዥዎችን ስላስጨነቁ ሽፍቶች እየሰማ ነበርና ያደገው መሸፈት አማረው፡፡ አንድ ቀን ከብት ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች መሸፈቱን ነግሮ የአጎቱን ቁመህ ጠብቀኝ መንትፎ ሸፈተ፡፡ ሸፍቶም ጫካ ገባ፡፡ አገሩም ‹ታች በሌ ሸፈተ› እያለ ከሚዳ እስከ እነዋሪ አወጋ፡፡ አንዳንዱ አደነቀ፤ ዘፈነለት፤ አንዳንዱ ተጠራጠረ፣ አንገቱን ነቀነቀበት፡፡ ‹በምን ልቡ ነው የሸፈተው›› ያሉም ነበሩ፡፡ ጥዱም እገለዋለሁ ብለዋል ተባለ፡፡
ታች በሌ ዠማ ወንዝ በረሃ ውስጥ ወርዶ አንድ ጫካ ውስጥ ተቀመጠ፡፡ መጀመሪያ ስሙ በድፍን ሸዋ ሲገንን፣ ስሙ በየሠርግ ቤቱና በየድግስ ቤቱ የዘፈን መቋጠሪያ ሲሆን እየታየው ልቡ በደስታ ሞቆ ነበር፡፡ ዋል አደር ሲል ግን ታች በሌን ጥያቄዎች ጭንቅላቱን እየሞሉ ያስጨንቁት ነበር፡፡ ለመሆኑ በቂ ስንቅ ይዘሃል? የሸፈትከውኮ በጀግናው ጥዱ ላይ ነው፤ ለመሆኑ በቂ ጥይት ታጥቀሃል? ለመሆኑ ቢመጡብህ የምትሸሽበት የማምለጫ ስርጥ መርጠሃል? አንተ መንደርህ እያለህ አንድ ቆቅ እንኳን አድነህ የማታውቅ እንዴት ጥዱን ለመዋጋት ጫካ ገባህ? ለመሆኑ ዛሬ የታጠቅከውን ቁመህ ጠብቀኝ ተኩሰህበት ታውቃለህ? ቢበላሽ ማን ይጠግንልሃል? ከዛሬ በፊት ለመሆኑ ጫካ ውለህ አድረህ ታውቃለህ? ከአውሬ ጋር ታግለህ ታውቃለህ?
እነዚህ ጥያቄዎች ጭንቅላቱን ሲወጥሩት ታች በሌ መልስ አልነበረውም፡፡ የዠማን በረሃ ወደ መርሐ ቤቴ ሲያልፍበትና ወደ ጅሩ ሲወጣበት እንጂ ውስጡ ገብቶ ሥር ማንሥሩን አይቶት አያውቅም፡፡ እንዲያውም አሁን ሲያስበው ትንሽ ፍርሃት ሳይኖርበት አይቀርም፡፤ እንደ ሌሎቹ እንኳን ቅራት (ከብትን በረሃ ውስጥ ሌሊት መጠበቅ) ለብቻው አድሮ አያውቅም፡፡ ደግሞ አሁን ሸፍቷልና የሚያወያየው እንኳን የለም፡፡ እየዋለ እያደረ ሃሳብ ሲበዛበት ታች በሌ ይጨንቀው ነበር፡፡ ሽፍትነት ሲያስቡትና ሲሸፍቱት አንድ አልሆነለትም፡፡ እርሱ እዚህ በረሃ ውስጥ ምን እንደሚያደርግ ጨንቆታል፣ እዚያ መንደር ውስጥ ግን በስሙ ይዘፈን ይሆናል፡፡ የልቡን ማን አየለት፡፡ ለእርሱ ከሚዘፍኑለት ስንቅና ትጥቅ ቢያቀብሉት ነበር የሚሻለው፡፡
ታች በሌ ለአንድ ሳምንት በረሃው ውስጥ ተቀመጠ፡፡ ስንቅና እድሜ እያደር ይቀላል እንዲሉ የያዘው ነገር ሁሉ እያደር ያልቅበት፣ እርሱም ብቸኛነትን አልለመደውም ነበርና እያደር ሆድ ይብሰው ጀመር፡፡ አንዳንዴም ሲያስበው መሸፈት እንዳልነበረበት ራሱን ይሞግታል፡፡ አሁን እንዴት አድርጎ ወደፊት መጓዝ እንደሚችል ያስባል፤ ግን ምንም ሃሳብ ሊመጣለት አልቻለም፡፡ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ሰው ምን ይለዋል? አንዳንዴ የተወለደበትን ቀን ትቶ የሸፈተበትን ቀን ይረግማል፤ አንዳንዴ ደግሞ እንኳን ሸፈትኩ ይላል፡፡ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ጥዱም ሆኑ የጥዱ አንጋቾች ወደ አካባቢው ዝር ሊሉ አልቻሉም፤ ታድያ ሳይዋጋ ሽፍታ ተብሎ እስከ መቼ ሊቀመጥ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነኮ ጥቂት ቆይቶ ይረሳል፡፡
ታች በሌ እየቆየ ነገር ዓለሙ መረረው፤ መሸፈቱንን እንጂ ለምንና ምን ሊያደርግ እንደሸፈተ ለኅሊናው ማስረዳት አልቻለም፤ ቀጥሎ ምን እንደሚያደርግና ከዚያስ መጨረሻው ምን እንደሆነ ሊያውቀው አልቻለም፡፡ እገሌ ሸፈተ ሲባል እንጂ ሽፍትነት ምን እንደሆነ፣ ሸፍቶ ምን እንደሚደረግ በልቡ ምንም ነገር አልያዘም፡፡
አንድ ቀን ታች በሌ ድንገት የሚኖርበት መንደር ያለች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅዳሴ ሰዓት ከች አለ፡፡ አገርም ጉድ አለ፡፡ ካህናቱም ጨዋውም እያየው አፉን ይዞ ቀረ፡፡ ታምር ተሰምቶ የሰንበት ቂጣ ሊታደል ሲል ታች በሌ ድንጋይ ይዞ ሕዝቡ እግር ሥር ወደቀና ይቅርታ ጠየቀ፡፡ ሰይጣን አሳስቶኝ ነው ብሎ በዚያ መከረኛ ላይ አላክኮ ካህናቱ ድንጋዩን አነሡለት፡፡
አንድ ሰሞን የታች በሌ ነገር የሞረቴ ሁሉ አፍ ማሟሻ ሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ ለሞረቴ መሸፈት ቀላል አልሆነም፤ ‹‹ደግሞ እንደ ታች በሌ ሲርብህ እንዳትመጣ›› የሚባለው ብዙ ነው፡፡ እንዲያውም አንድ ሰው ሸፈተ ሲባል አቅራሪዎቹ
ምከሩት፣
ምከሩት፣
ምከሩት፣
ይህንን ታች በሌ ለምን አትመክሩትም፤
ይህንን ታች በሌ ለምን አትነግሩትም፤
ልብ ካልሸፈተ እግር አይሸፍትም ….. ሃ!
እያሉ ይመክሩት ነበር፡፡ ታች በሌ ሳያስቡ ለሚወስኑና ሳያስቡ ለሚያደርጉ ሁሉ የሚሰጥ ቅጽል ሆነ፡፡
ታች በሌያዊ አስተሳሰብ የሀገራችን ተቋማት አንዱ ችግር ነው፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች፣ ማኅበራት፣ ድርጅቶች፣ ኩባንያዎችና ስብስቦች ሳይታሰቡ ተመሥርተው ሃሳብ የጠፋባቸው ናቸው፡፡ ለሃሳብ ተቋም ከመመሥረት ይልቅ ለተቋማቱ ነው ሃሳብ እየተፈለገ ያለው፡፡ ቁጭት ሁሉ፣ ብስጭት ሁሉ፣ ስብስብ ሁሉ፣ ገንዘብ ሁሉ፣ አጋጣሚ ሁሉ ድርጅት፣ ፓርቲ፣ ተቋም፣ ማኅበር ለመመሥረት መዋል የለበትም፡፡ እነ ዕገሌ ስለ መሠረቱ፣ እነ እገሌ ስለተሰባሰቡ፣ የዕገሌ አካባቢ ሰዎች በስማቸው ፓርቲ ስለመሠረቱ፣ የዚህ ዓይነት ሞያ ሰዎች ማኅበር ስላቋቀቋሙ፣ የዚያ ሀገር ሰዎች ኮሙኒቲ ስለ ፈጠሩ፣ እንቶኔና እንቶኔ ኩባንያ ስላቋቋሙ እኛም ማቋቋም የለብን፡፡
መጀመሪያ ሃሳብ ይቅደም፡፡ ማሰብ ማለት ደግሞ ሃሳብን ብልጭ ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ ይህማ ታች በሌን መሆን ነው፡፡ ብልጭ ያለውን፣ ቁጭት የፈጠረውን ሁሉ ሳያስቡበት ተጣድፎ ማድረግ፡፡ ማሰብ እንዲህ አይደለም፤ ግራ ቀኝ የታሰበበት፣ የተጠናና የተነበበበት፣ ከቀደምቶች ልምድ የተቀሰመበት፣ ከተሳካላቸውም ካልተሳካላቸውም ትምህርት የተወሰደበት፣ እንዴት እንደሚኬድ፣ ግቡ ምን እንደሆነ፣ የተሻለው መንገድ የትኛው እንደሆነ፣ የሚያስፈልጉ ነገሮች ምን እንደሆኑ፣ ከነ ማን ጋር መተባበር እንደሚገባ፣ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል፤የፍልስፍና መስፈንጠሪያው ምን እንደሆነ አጥልቆና አልቆ መመርመር ነው- ማሰብ፡፡
አንዳንድ ሰው አስቤያለሁ ሲል ‹‹ይህ ነገር በአእምሮዬ መጥቶልኛል›› ማለቱ ነው፡፡ ይህኮ ሰው በመሆኑ ብቻ የሚያጋጥመው ነው፡፡ በአምስቱ የስሜት ሕዋሳቱ መረጃዎች ወደ አእምሮው ሲገቡ ልክ በቁልፍ እንደሚነሣ መኪና ቅንጭሌውን ሊያስነሡት ይችሉ ይሆናል፡፡ ይህ ግን መኪናው በቁልፉ ስለተነሣ ብቻ ሄደ እንደማይባለው ሁሉ ሰውዬውም አሰበ አያስብለውም፡፡ መጀመሪያ የመኪናው ባትሪ ቀጥሎ ሞተሩ መነሣት አለበት፡፡ ሞተሩ ደግሞ ሌሎችን ሁሉ አንቀሳቅሶ ሙሉ መኪናው መሥራት አለበት፡፡ ያን ጊዜ መኪናው ሄደ ይባላል፡፡
ሰውም ሃሳብ ብልጭ ስላለለት፣ የሆነ ቁጭት ስለተፈጠረበት፣ ከሆነ ሰው አንዳች ነገር ስላገኝ፣ በአጋጣሚ አንድ መረጃ ስለደረሰው፣ ቅናት ስላደረበት፣ ዕድል ስለተፈጠረለት፣ ዘመዶቹ ክፈት እንረዳሃለን ስላሉት ብቻ ተቋም፣ ድርጅት፣ ፓርቲ፣ ማኅበር መመሥረት የለበትም፡፡ አንዳንዶች የሆነ ነገር ለማድረግ አስበው ከመሰባሰብ ይልቅ ተሰባስበው ምን እንናድርግ? ብለው ያስባሉ፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች እንደ ታች በሌ ሳያስቡ የሸፈቱ ናቸው፡፡ የተለየ ሃሳብ፣ የተለየ ፍልስፍና፣ የተለየ አቋም፣ የተለየ መንገድ ሳይኖራቸው እንዴው በፓርቲዎቻችን ቁጥር ላይ አንድ ለመጨመር ያህል ብቻ የተመሠረቱ፡፡ ፓርቲው ከተመሠረተ በኋላ ነው ፕሮግራም፣ መመሪያ፣ ፍልስፍና፣ መንገድ፣ የሚያዘጋጁት፡፡ በሃሳብ ስለማይመሠረቱ ከተመሠረቱ በኋላ በሃሳብ ይለያያሉ፡፡ ሳስበው እንዲያውም ለሁሉም ችግሮቻችን መፍትሔ ስጡ ስንባል ኮሚቴ ማቋቋም የሚቀናን ለማሰብ ጊዜ ስለማንሰጥ ይመስለኛል፡፡ የስብሰባ፣ሞቅታ የፈጠራቸው ኮሚቴዎች ሃሳብ አጥተው ሲላጉ አባሎቻቸውን አንጠባጥበው መቼ እንደፈረሱ እንኳን ሳይታወቅላቸው ይፈርሳሉ፡፡ ታች በሌዎች በቁጭት ብቻ ተነሥተው የመሠረቷቸው የሞያ ማኅበራትም ከዓመታዊ ጉባኤ ያለፈ ሃሳብ ሊመጣላቸው ስላልቻለ፡፡ በአንድ ሊቀ መንበር ሃያ ዓመት እያዘገሙ እንዴት ናችሁ? ሲባሉ ‹አለን›› እያሉ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆነው ይኖራሉ፡፡
አንዳንዶችም አሉ፤ ምን እንደሚጽፉ ሳያስቡ መጽሐፍ ለመጻፍ የሚነሡ፡፡ ምን እንደሚገጥሙ ሳያስቡ ግጥም ለማሳተም የሚውተረተሩ፡፡ ምን እንደሚያቀርቡ ሳያስቡ ፊልም ለማዘጋጀት ገንዘብ የሚያሰባስቡ፡፡ የተለየ ሃሳብ ሳይኖራቸው የሬዲዮ የዐየር ሰዓት የሚገዙ፡፡ ምን እንደሚጠይቁ ሳያስቡ የቃለ መጠይቅ ማይካቸውን ተጠያቂው ላይ የሚተክሉ ቀልደኞች፡፡ ለነገሩ በሠፈር አንድ ሱቅ ሲከፈት የሠፈሩ ሰው ሁሉ አጥሩን እየቀደደ ሱቅ መሥራት የተለመደበት ሀገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ያዋጣል ወይ? ከጎረቤቴ በምን እለያለሁ? እኔ ምን አዲስ ነገር አመጣለሁ? ብሎ ሳያስብ ነው ሱቁን ቦግ የሚያደርገው፡፡ ሱቁን ከሠራና ዕቃ ካስገባ በኋላ ነው ማሰብ የሚጀምረው፡፡ ይህ ነገር ወደ ተቋሞቻችንም ተጋብቷል፡፡ ምን ተቋሞቻችን ብቻ ትዳሮቻችንም እንዲህ እየሆኑኮ ነው፡፡ ማግባት የሚፈልግ እንጂ እንዴትና ለምን እንደሚያገባ፣ የጋብቻው ጠባይና አካሄድ ምን እንደሚመስል አስቀድሞ የሚያስብ ጥቂቱ ነው፡፡ የሆነ ቦታ ለመሄድ እያሰብኩ ነው፤ የሆነ ነገር ሳልከፍት አልቀርም፤ አንድ የሆነ መጽሐፍ ልጽፍ እያሰብኩ ነው፤ የሚላችሁ ሰው ሳያስብ አንዳች ነገር ሊያደርግ የተዘጋጀ መሆን አለበት፡፡
አስቦ መሥራት እንጂ ሠርቶ ማሰብ ኪሣራው ብዙ ነው፡፡ ገበያ መውጣታቸውን እንጂ ምን ሊገዙ እንደወጡ፣ ቤት መሥራትና መግዛት እንጂ ምን ዓይነት ቤት እንደሚገዙ ወይም እንደሚሠሩ፣ ውጭ ሀገር መሄድ እንጂ ለምንና እንዴት እንደሚሄዱ፣ የማያስቡ አሉ፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች የነበረውን መንግሥት ስለመቀየር እንጂ በቅያሪው ስለሚመጣው መንግሥት ስላልታሰበበት የመጣው ከሄደው የባሰበት ጊዜ አለ፡፡ ለዚህ ነው ታች በሌያዊ የሆነውን መንገድ ትትን ሃሳብ ከተቋም ይቅደም የምለው፡፡ ሃሳብ ከድርጊት ይቅደም፡፡ ሃሳብ ከመመሪያም፣ ከዐዋጅም፣ ከማፍረስም፣ ከመሥራትም፣ ከመሸለምም፣ ከመቅጣትም፣ ከመሄድም ከመምጣትም ይቅደም ፡፡
አንድ ሰው እንዲያውም ይህንን ነግሮኛል፡፡ የአንድ ገበሬ ውሻ ሁልጊዜ መንገድ ዳር እየቆመ አላፊ አግዳሚውን መኪና ለመያዝ እየተከተለ ይጮኻል፡፡ የገበሬው ጓደኛ ይኼ የውሻው ጠባይ ይገርመዋል፡፡ አንድ ቀን ገበሬውን ‹‹ለመሆኑ ይኼ ውሻህ መኪናውን ተከትዬ እይዘዋለሁ ብሎ ነው እንዲህ መከራን የሚያየው?›› ይለዋል፡፡ ገበሬውም ሳቅ ብሎ ‹‹እኔ ለመያዝ መታገሉ አይደለም የሚያስገርመኝ፤ የሆነ ቀን ሊይዘው ይችላል፡፡ እኔን የሚገርመኝ መኪናውን ቢይዘው ምን እንደሚያደርገው ውሻው አለማሰቡ ነው›› አለው ይባላል፡፡ ታች በሌያዊ አስተሳሰብ ማለት ይህ አይደለም ታዲያ፡፡