ሕዝቡ በአንድነት ፓርቲ ላይ ያለዉን ቅሬታና ድጋፍ ገለጠ
አቡጊዳ – ነሐሴ 28 ቀን 2002
ከመቶ ሃምሳ በላይ የሚሆኑ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አደራጆች፣ የተዘጋጁ ቃለ መጠይቆችን በመዉሰድ፣ ከሕዝቡ አስተያየት ሲሰበስቡ ቆይተዉ፣ የሥራቸዉን ዉጤትና የሕዝቡን አስተያየት የያዘ ዘገባ በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክር ቤት በቅርቡ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሕዝቡን ያላቀፈ ትግል የትም እንደማይደርሰ የገለጹት፣ ያነጋገርናቸዉ አንድ ከፍተኛ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል፣ «ሕዝቡ የሚለዉን መስማት አለብን። ከላይ ወደ ታች ብቻ ሳይሆን ከታች ወደ ላይ፣ ሃሳብ፣ ትችት፣ ወቀሳ መምጣት አለበት። እንደዚያ ሲሆን ነዉ እንደ አንድ ተያይዘን ወደፊት መሄድ የምንችለዉ » ሲሉ አደራጆቹ የሚያቀርቡትን ሪፖርት ለመስማት እንደጓጉ ገልጸዋልናል።
የአንድነት ፓርቲ ከሕዝቡ አስተያየቶች ከመሰብሰብ በተጨማሪ በአባላቱ መከካል፣ ከሥራ አስፈጻሚ ጀምሮ እሰከ ወረዳ ጽ/ቤቶች ድረስ የዉስጥ ግምገማ ያደረገ ሲሆን፣ ከፍተኛ የአሰራርና የስትራቴጂ ለዉጦች ይዞ ብቅ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።
በርካታ በተለይም በእድሜ ባለጸጋ የሆኑ፣ ለትግሉ ብዙ ያበረከቱ አንጋፋ የቀድሞ የሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ ከሥራ አስፈጻሚነት ተነስተዉ በአማካሪነት ይሰራሉ የሚል ግምት እንዳለ፣ በምትካቸዉም ወጣቶችና ሴቶች ሃላፊነቱን እንደሚይዙ የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል።
በተያያዘ ዜና ከፍተኛ የመድረክ አመራር አባላት፣ በዚህ ሳምንት መጨረሻ በአዉሮፓ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ለማናገገር ወደ አዉሮፓ እንደሚሄዱ ለማወቅ ችለናል። የአመራር አባላቱ በአዉሮፓ ቆይታቸዉ በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያንንም ያነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።