ከየመን ህዝባዊ አብዮት ምን እንማራለን?

ህዝባዊ አብዮት ከተቀጣጠለባቸው የአረብ አገራት ሁሉ በመልክዓ ምድር አቀማመጥ የየመንን ያህል የሚቀርበን የለም። የኢትዮጵያና የየመን መመሳሰል በመልክዓ ምድር አቀማመጥ ብቻ አይደለም፤ መመሳሰላችን በብዙ ጉዳዮች ነው።

  1. የመን የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የነገሰባት አገር ናት፤ ወይም ነበረች። አሊ አብደላ ሳልህ ለሰላሳ ሶስት ዓመታት ገዝቷታል። ኢትዮጵያም የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የነገሰባት አገር ናት። መለስ ዜናዊ ለሃያ ዓመታት ገዝቷታል።
  2. የመን በበርካታ ዘውጌ ማኅበረሰቦች (ብሄር፣ ብሄረሰቦች) የተገነባች አገር ስትሆን አሊ አደብላ ሳልህ በተግባር የየመንን ህዝብ እርስ በርሱ እያጋጨና እያስታረቀ ሲገዛ፤ በወሬ ደግሞ ተበታትና የነበረችውን የመን አገናኝቶና አዋድዶ ያቆያት አስመልሎ ሲሰብክ ኖሯል። የኛው ጉድም ኢትዮጵያን ከመበታተን ያዳንናት እኔና ጓደኞቼ ነን ማለቱ ሳያንሰው ለወደፊቱም እኛ ከሌለንም መበታተኗ አይቀሬ ነው እያለ ያስፈራራል።
  3. የመን ከአረብ አገሮች ሁሉ በድህነት የመጨረሻው ደረጃ ላይ ያለች አገር ናት። ኢትዮጵያም በድህነት ከአፍሪቃ – በዚህም ምክንያት ከዓለም – አገሮች የመጨረሻ ደረጃ ላይ ያለች ናት።የአሊ አብደላ ሳልህ አገዛዝ “ስለፈጣን እድገት” ሲናገር የቆየ ቢሆንም የመን ዜጎቿ በመሃይነትና በበሽታዎች የተጎዱባት እና ኋላ ቀር ባህል የሰፈነባት አገር ናት። የኛዋ ኢትዮጵያዋም የፈጣን እድገት መዝሙር የሚዘመርባት ቢሆንም ዜጎቿ ከየመን በባሰ ሁኔታ በመሃይምነትና በበሽታ እየማቀቁ ያሉባት አገር ናት።
  4. “የመን የአሊ አብድላ ሳሊህ የከሰረ የቤተሰብ ቢዝነስ ነች፤ መንግስቷም ከወደቁ መንግሥታት ተርታ ነው” ተብሏል። ኢትዮጵያም የመለስ ዜናዊና ቡድኑ የግል ሃብት ሆናለች። በመለስ እጅ ያለችው ኢትዮጵያዊ እየተመዘበረች፤ ለአረቦችና ህንዶች እየተሸጠች ከስራለች፤ እየከሰረችም ነው። መለስ የሚጫወትባት ኢትዮጵያችንም ከወደቁ መንግሥታት ተርታ ገብታለች።
  5. የመን ውስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚው እጅግ በጣም አነስተኛ በመሆኑ በዘመናዊ የመገኛና ዘዴዎች ለአመጽ መጠራራት የማይሞከር እንደሆነ ሲነገር ነበር። በዚህም ምክንያት የአሊ አብደላ ሳልህ ካድሬዎች ብቻ ሳይሆኑ ገለልተኛ የሆኑ ምሁራንም ሳይቀሩ የቱኒዚያና የግብጹ አይነቱ አብዮት የመን ውስጥ የማይሞከር ነው ሲሉ ነበር። ኢትዮጵያም ውስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚው ቁጥር እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ተመሳሳይ ህዝባዊ አብዮት የመቀስቀሱ እድል አሳንሰው የሚያዩ በርካቶች ናቸው።
  6. አሊ አብደላ ሳልህ ራሱን የፀረ-ሽብርተኝነት ትግል አጋር አድርጎ በማቅረብ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግሥታትን ድጋፍ በሰፊው ሲያገኝ ቆይቷል። የኛው መለስም የአካባቢው ፀረ-ሽብርተኝነት ትግል አጋር ሆኖ በመቅረብ እያጭበረበረ ነው።
  7. ኣሊ ኣብደላ ሳልህ በሰላዮቹና አልሞ ተኳሽ ወታደሮቹ ብዛት ህዝብን በማስፈራራቱ አንዳችም የተቃውሞ እንቅስቃሴ የማይታሰብ መሆኑ ሲወራ ነበር። የኛው መለስም ጆሮጠቢዎችና አጋዚዎችን በብዛት በማሰማራቱ፤ ህዝብም እርስ በርሱ እንዳይተማመን በማድረጉ አብዮት የማይታሰብ ነው የሚሉ አልጠፉም።
  8. የመናዊያን “ጫት አፋቸውን ስለሞላው የተቃውሞ ጩከት ማሰማት አይችሉም” ተብሎ ተቀልዶባቸው ነበር። በኢትዮጵያ ህዝብና ወጣት የትግል ሞራል ላይ የሚሳለቁም ብዙዎች ናቸው።

በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለችው የመን ውስጥ ህዝባዊ አብዮት ተቀሰቀሰ። የመናዊያን እንደ ቱኒዚያና ግብጽ የዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት አልሳቡም። አልጀዚራም ቢሆን የየመንን አብዮት እንደግብጽ በተከታታይ አልዘገበም። ይህ ሁሉ ግን የመናዊያንን ተስፋ አላስቆረጠም።

የመናዊያን ከአራት ወራት በላይ የአሊ አብደላ ሳልህን አገዛዝ ተጋፈጡት። በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለው እነሆ ዛሬ ለድል ተቃርበዋል።

“እኔ ከሌለሁ አገሪቷ ትበተናለች፤ ስለዚህም በጭራሽ ስልጣኔን አልለቅም” ያለው አሊ አብደላ ሳልህ በባሩድ ፊቱና ጀርባው ተለብልቦ ሳውዲ ዓረቢያ ውስጥ የአልጋ ቁራኛ ሆኗል። ለብዙዎች የአሊ አብደላ ሳልህ የስልጣን ዘመን አብቅቷል። ከቁስሉ አገግሞ ወደ የመን ቢመለስ እንኳን የምትጠብቀው እሱ የማያውቃት የመን ናት።

ለመሆኑ እኛ ከየመን ምን እንማራለን?

  • ድህነታችን፣ ኋላቀርነታችን፣ የበርካታ ዘውጌ ማኅበረሰቦች ውጤት መሆናችን ህዝባዊ አብዮቱን ያከብዱት እንደሆነ እንጂ እንዳይነሳ እንደማያደርጉት ከየመን መማር እንችላለን።
  • በጽናት የታገለ ህዝብ ድልን ሳይቀዳጅ ቤቱ እንደማይመለስ ከየመን እንማራለን።
  • በህዝብ መጠላታቸው ፊት ለፊት ሲነገራቸው ለማይገባቸው ለእንደ አሊ አብደላ ሳልህ ዓይነቱ አምባገነኖች ከሰላማዊው ትግል ጎን የጡንቻ አስፈላጊ የቱን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ከየመን እንማራለን።

ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የየመን የነፃነት ታጋዮች ላደረጉት ተጋድሎ ያለውን አድናቆት እየገለጸ ለተቀጃጁት ድል የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላልፋል። ኮርተንባችኋል። በቅርቡ የተሟላ ድል እንደምትቀዳጁ ባለሙሉ ተስፋ ነን።

እኛም በቅርቡ የናንተን መንገድ እንከተላለን። አምባነንነት፣ ረሃብና እርዛት፣ ግፍ እኛም እንደናንተው መሮናል፤ አንገፍግፎናል። እንደናንተው እኛም “በቃ!” ብለናል።

በቃ!!! ጋዬ!!! ይአከል!!! አሎኒ!!! ዲታህ!!! ወጣንደም!!! በስ!!! ጊዴስ!!!