የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› አመራሮች ላይ የእስር ቅጣት ወሰነባቸው


(ደጀ ሰላም፤ ጁን 4/2011)፦ የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚያዝያ ወር ውስጥ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ባስነሡት ብጥብጥ በንጹሐን ምእመናን ላይ ከፍተኛ የድብደባ ወንጀል ፈጽመዋል ባላቸው አራት የ‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት›› ማኅበር አመራር በሆኑ ተከሳሾች ላይ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሐሙስ፣ ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት ገዛኸኝ አበራ እና አየነው የተባሉት ግለሰቦች በ8 ዓመት፣ ተስፋዬ በ5 ዓመትና ጌታሁን የተባሉት ደግሞ በ3 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

ውሳኔው በተላለፈበት ዕለት ምሽት የእኒሁ ወንጀለኞች ጥቂት ደጋፊዎች በገዳሙ ዐውደ ምሕረት ላይ በመውጣት በድምጽ ማጉያ ‹‹ወንድሞቻችን ተፈረደባቸው፤ ታሰሩ፤›› እያሉ የከተማውን ደጋግ ምእመናንን እና የማኅበረ ቅዱሳንን ስም እየጠሩ ሲወነጅሉ እንደነበር ተገልጧል፡፡ እኒሁ ግለሰቦች በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ተመርጠውና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተመድበው የሄዱትን አዲሱ ሥራ አስኪያጅ ወደ ቢሯቸው እንዳይገቡ ለመከላከል ሞክረው እንደነበር ታውቋል፡፡ ይሁንና በፖሊስ ኀይል ከአካባቢው እንዲርቁ ከተደረገ በኋላ ሥራ አስኪያጁ ሥራ ለመጀመር መቻላቸው ተመልክቷል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ አላግባብ ከተሰጣቸው ሥልጣን እንዲወገዱ የተደረጉት ‹‹ሊቀ ካህናት›› ጌታቸው ዶኒ በተሰራጨው ቪ.ሲ.ዲ ስሜ ጠፍቷል ያሉበትን ክስ በዚያው በሐዋሳ ከተማ ሆነው እየተከታተሉ ሲሆን ግንቦት 27 ቀን 2003 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ምክትል ሐላፊ ሆነው መሾማቸው ተነግሯል፡፡