ጎንደሮች በሰልፉ ለመገኘት የትኛውንም ዋጋ እንከፍላለን እያሉ ነው!

ጎንደሮች በሰልፉ ለመገኘት የትኛውንም ዋጋ እንከፍላለን እያሉ ነው!
ሐምሌ 5 ቀን 2005 ዓ.ም

በጎንደር የአንድነት አመራሮች ፖሊስ ካሜራ እየነጠቀ ነዉ !
‹‹እኛ ሰላማዊ ታጋዮች ነን። የያዝነው ጥያቄ እንጂ መሳሪያ አይደለም»
አቶ ዘካሪያስ የማነአብ ፣ የአንድነት ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ
———————————————————–
በ30/10/2005 በጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ ለማከናወን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ያቀረበውን ጥያቄ የከተማው አስተዳደር ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት፣ ፓርቲው ለህግ ያለውን ተገዢነት ለማሳየት፣ ሰልፉን ለአንድ ሳምንት ማራዘሙ አይዘነጋም፡፡ፓርቲው ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ የወሰደውን ውሳኔ እንደ ፍርሃት የተመለከቱት አስተዳደሮች ግን የአንድነትን አባላት በመለቃቀም ወህኒ ቤት እያጎሩ ናቸው፡፡

ዛሬ ማለዳ ደግሞ ብዛት ያላቸው የቀበሌ ካድሬዎች ፖሊሶችን በማስከተል የአንድነት የጎንደር ጽ/ቤትን በመክበብ ለቅስቀሳ ስራ ለመውጣት የተዘጋጁ አባላትን አግተዋል፡፡… የቅስቀሳ ስራ የሚሰሩ አባላት በያዙት ካሜራ የፖሊሶቹንና የካድሬዎቹን ህገ ወጥ ድርጊት በካሜራቸው ቀርጸው ለማስቀረት ሲሞክሩ፣ ፖሊስ ካሜራውን ነጥቆ ወስዷል፡፡ ከሁሉም አስገራሚው ግን ካድሬዎቹ ፣ የአንድነት ጽ/ቤት እንዲሆን ፣ ቤታቸውን ያከራዩትን ወይዘሮ ለማስፈራራት መሞከራቸው ነው፡፡ ወይዘሮዋም ከፍተኛ ጫናና ወከባ ስለደረሰባቸው፣ ለአመራሩ «ቤትን ብትጠቀሙ ደስ ይለኝ ነበር። ግን ችግር ዉስጥ ልገባ ነዉ። ባካችሁ ሌላ ቦታ ተከራዩ »በማለት ተማጽንኦ አቅርበዋል፡፡

ፖሊሶችና ካድሬዎች እጅና ጓንት ሆነው የአንድነትን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማኮላሸት የሚፍጨረጨሩ ቢሆንም፣ የጎንደርና የአካባቢዋ ነዋሪዎች፣ ከሰልፉ የሚያስቀራቸው ምንም አይነት ምድራዊ ሃይል እንደሌለ እየተናገሩ ነው፡፡ የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክርቤት ሰብሳቢ አቶ ዘካሪያስ ‹‹እኛ ሰላማዊ ታጋዮች ነን። የያዝነው ጥያቄ እንጂ መሳሪያ አይደለም» በማለት የሰላማዊ ሰልፉ ተልእኮ «ሰላማዊ» ብቻ መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት !