አሕጽሮት
በቀደም በቀለበት መንገድ ላይ በመኪና ስሄድ ከጎናችን አንድ ነጭ ፒክ አፕ መኪና ይጓዝ ነበር፡፡ ዘወር ብዬ ሳየው በሩ ላይ የመሥሪያ ቤቱን ስም ለጥፏል፡፡ ያየሁትን ለማመን ስላቃተኝ በሞባይል ፎቶ አነሣሁት፡፡ የድርጅቱ ስም ግምማአድ (AISA) ይላል፡፡ ምን ሆነው ነው እንዲህ ያለ ለክፉ ትርጉም የሚያጋልጥ ስም የሚያወጡት፡፡ ለመሆኑ ድርጅቱ በአማርኛ ሲጠራ ምንድን ነው የሚባለው? ‹ግም ማአድ› ማለትኮ በአማርኛ መልካም ትርጉም የለውም፡፡ አሁን እዚያ የሚሠራ ሰው የት ትሠራለህ ሲባል ‹ግምማአድ እሠራለሁ› ይላል ማለት ነው?
አንዳንድ ድርጅቶች የባለቤቶቹን ወይም የረጅዎችን ፍላጎት ማሳካታቸውን እንጂ በባለቤቶቹ ላይ የሚያመጡት ተጽዕኖ ግምት ውስጥ አይገባም፡፡ ያ ስም ከአካባቢው ባህልና እምነት አንጻር በተጠቃሚውም ሆነ በሠራተኛው ላይ ተጽዕኖ ማድረሱ አይገመገምም፡፡ በአንድ ወቅት ጃፓኖች ያመረቱትን መኪና የሰየሙበት ስም በፈረንሳይኛ ‹ሞት › የሚል ትርጉም በመስጠቱ ምክንያት የነበረውን ክርክር አስታውሰዋለሁ፡፡
ባለፈው ጊዜ በደቡብ ጎንደር በንፋስ መውጫ ከተማ በኩል ስናልፍ ‹ዝሙት በኛ ይብቃ› የሚባል የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ አየን፡፡ ስሙ ገረመንና ለመጠየቅ ጠጋ አልን፡፡ ሱቁ የተከፈተው ከዚህ በፊት በዝሙት አዳሪነት ይተዳደሩ የነበሩ ሴቶችን ከዚህ ዓይነት ተግባር በማውጣት መሆኑ ተነገረን፡፤ ይሁን ሃሳቡ መልካም ነው፡፤ ነገር ግን አንድ ሰው ምንስ ቢሆን ‹እኔ ዝሙት አዳሪ ነበርኩ› ብሎ በአደባባይ እንዲናገር እንዴት ይደረጋል? የእነዚያ ሴቶች ልጆችስ ‹ዝሙት በኛ ይብቃ ሱቅ የኛ ነው› ብለው በኩራት ይናገራሉ? ሰዎችስ ‹ዝሙት በኛ ይብቃ ሱቅ አጠገብ እንገናኝ› ተባብለው ይቀጣጠራሉ? እዚህ አልጽፈውም እንጂ የአካባቢው ሰዎች ሱቁን የሚጠሩት በሌላ ስም ነው፡፡
እስኪ ለዛሬ ‹ግምመአድ› የሚባለው ተቋም ወዳስታወሰኝ በሀገራችን ለንግድ፣ ለመንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ስለሚወጡት ስሞች በተለይም ስለ የአሕጽሮት ስሞች እናውጋ፡፡ በታላላቅ ከተሞቻችን ውስጥ ድርጅትንና ሕንፃን በእንግሊዝኛ አሕጽሮት መሰየም እየተለመደ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ስያሜዎች እንኳን እኛ ተመልካቾቹ ቀርተን ባለቤቱም ቢሆን ለመጥራት የሚቸገርባቸው ዓይነት ናቸው፡፡ ESLPTYGQ ሕንፃ የሚለውን እስኪ ምን ብላችሁ ትጠሩታላችሁ? አንድ ቦታ ደግሞ በአማርኛ ‹ትግድብም› የሚባል ሕንፃ አይቻለሁ፡፡ አሁን ይህንን እንዴት አድርጎ ማስታወስ ይቻላል? በተለይም በሀገራችን አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የወከሏቸውን ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ ለማካተት ሲጥሩ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ‹ዴግ› የሚል ሲጨምሩበት ስማቸውን ጠርቶ ከመጨረስ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን አንብቦ መጨረስ ቀላል ይሆናል፡፡
እንደ ፈረንሳይ ባሉ ባደጉት ሀገሮች ለድርጅቶች ስምን የሚያወጡ የታወቁ ኩባንያዎች አሉ፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች የድርጅት ባለቤቶችን ሀሳብ፣ የስሙን ትርጉም፣ ለመጥራት ቀላል መሆኑንና ከሥነ ምግባር ጋር አለመጋጨቱን በማየት ስም ያወጣሉ፡፡ እኛ ሀገር ግን ብዙ ጊዜ የድርጅቱን ባለቤቶች ወይም የቤተሰቦቻቸውን አለበለዚያም ደግሞ የትውልድ ቦታቸውን ስም የመጀመሪያ ፊደሎች ብቻ በያዙ አሕጽሮቶች የሚጠሩ ድርጅቶችና ሕንጻዎች ናቸው ያሉት፡፡ እነዚህን ስሞች ራሳቸው ባለቤቶቹ ይመስሉኛል የሚሰጧቸው፡፡ እነርሱ የፈለጉትን ማድረጋቸውን እንጂ እኛ ደንበኞቻቸው ይመቸን አይመቸን፣ ይስማማን አይስማማን ግድ የላቸውም፡፡
የአሕጽሮት ስሞች እንዲሁ በፈቀደ የመጀመሪያ ስሞችን በመገጣጠም ብቻ የሚወጡ አይደሉም፡፡ የራሳቸው የሆነ መንገድና ሥነ ምግባርም አላቸው፡፡ ባለሞያዎቹ የአሕጽሮት ስሞችን ለሚያወጡ ሰዎች ቢያንስ እነዚህን አራት ነገሮች ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ይመክራሉ፡፡
- አጭር መሆን፡- የአሕጽሮት ስም ሲወጣ በተቻለ መጠን ለመጻፍም ሆነ ለመጥራት አጭር የሆነ ቢሆን ይመረጣል፡፡ በእንግሊዝኛ ከሆነ ከሦስት እስከ ስድስት ፊደል፣ በአማርኛ ከሆነ ደግሞ ከሦስት እስከ ሰባት ፊደል ቢሆን ይመረጣል፡፡ UNESCO ከእንግሊዝኛው ጅንአድ ከአማርኛው መልካም ምሳሌዎች ናቸው፡፡
- ለመጥራት ቀላል የሆነ፡- የምንኖረው ኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ የምናወጣቸው የአሕጽሮት ስሞች ለአንድ ኢትዮጵያዊ ለመጥራት ቀላል የሚሆኑ መሆን አለባቸው፡፡ ከላይ እንዳየነው ESLPTYGQ እንደሚለው ዓይነቱን ስም አንድ ኢትዮጵያዊ እንዴት አድርጎ በቀላሉ ይጠራዋል? ይህንን መሰሎቹን አሕጽሮቶች ባለሞያዎቹ ‹የፊደላት ሾርባ› Alphabet soup ብለው ይጠሯቸዋል፡፡
- ሌላ ትርጉም የማይሰጡ፡- የምናወጣው አሕጽሮት የባለቤቶቹን ስም መያዙ ብቻ መታየት የለበትም፤ በእንግሊዝኛም ሆነ በአማርኛ ወይም በሌላም ቋንቋ ቢሆን ሌላ ዓይነት ትርጉም የማይሰጥ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ‹ግምመአድ› ለአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ የመልካም ነገር መገለጫ አይደለም፡፡
- ልዩ የሆነ(ያልተደገመ) የምንሰጠው አሕጽሮት የራሳችን የሆነና ከዚህ በፊት ያልተደገመ ቢሆን መልካም ነው፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች አሕጽሮቶችን የሚመዘግቡ መዛግብት አሉ፡፡ የታወቁ አሕጽሮቶችን የሚይዙ ድረ ገጾችም አሉ፡፡ በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ ብሎም በታወቁ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የታወቁትን አሕጽሮቶች መጠቀም ክርክርና መምታታትን ያስከትላል፡፡
የአሕጽሮት ስሞችን ለድርጅቶቻቸው ማውጣት ለሚፈልጉ አካላት በዓለም ላይ የተሻሉ መንገዶች ተብለው የሚመከሩትን ዘዴዎች ቢከተሉ ያዋጣቸዋል፡፡ ከእነዚህ የአሕጽሮት ማውጫ ዘዴዎች መካከል የሚከተሉት መንገዶች ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ናቸው፡፡
1. ትርጉም የሚሰጥ ቃል መፍጠር፡- ቃላቱን በማሳጠር አሕጽሮት ስናወጣ በተቻለ መጠን ትርጉም እንዲሰጡ አድርጎ ማውጣት ማለት ነው፡፡ ለዚህ በሀገራችን ምሳሌ የሚሆነን ለረዥም ዘመን የምናውቀው ኩባንያ ‹በርታ› ነው፡፡ በርታ በአንድ በኩል በእንግሊዝኛው ‹ብርሃኔና ታደሰ› የሚባሉት ባለቤቶቹ ስም አሕጽሮት ሲሆን በአማርኛ ደግሞ ‹ጎብዝ፣ ጀግን› ማለት ነው፡፡ አንድ ቦታም ‹ድንበሩና በርይሁን› የተባሉ ጓኛሞች የመሠረቱትን ‹ድንበር› የተባለ ኩባንያ አይቻለሁ፡፡ በእንግሊዝኛም Radar – Radio Detention and Ringing, Interpol- International Police, በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህንን ዓይነት ስያሜ ለመስጠት የግድ የስሞቹ የመጀመሪያ ፊደሎች ብቻ ሳይሆን ከስሞቹ የተወሰኑትን መውሰድ፣ ወይም አያያዦችንም ማካተት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ MATYAS ሕንፃ በአንድ በኩል የባለቤቶቹ ስሞች አሕጽሮት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ትርጉም ያለውን የሐዋርያ ስም ይሰጣል፡፡
2. የመጀመሪያ ፊደል አሕጽሮት፡- የስሞቹን የመጀመሪያ ፊደል ብቻ በመውሰድ ቢቻል ትርጉም ያለው፣ ባይቻል ለአጠራር ምቹ የሆነ ስም መፍጠር ነው፡፡ ለዚህ በሀገራችን መልካም የሚሆነው ምሳሌ አዕማድ (አነስተኛ ዕደ ጥበባት ማስፋፊያ ድርጅት) ነው፡፡ አዕማድ የሚለው ስም በአንድ በኩል የድርጅቱ ስም አሕጽሮት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በግእዝና በአማርኛ ‹ምሰሦዎች› ማለት ነው፡፡ እነ FAO, WTO, FIFA, እና ሌሎቹ በዚህ መልክ የተፈጠሩ ናቸው፡፡
3. ድቅል አሕጽሮት፡- ፊደልን ከቃላት ጋር በማጣመር የሚፈጠሩ የአሕጽሮት ስሞች ናቸው፡፡ በእንግሊዝኛው Dormat – Digital format በዚህ መልኩ የተፈጠረ ሲሆን እስካሁን በአማርኛ የማውቀው ስም አላገኘሁም፡፡
እነዚህን መንገዶች እንዲያው ለማመላከት ያህል የጠቀስኳቸው አሕጽሮት እንዴው በደፈናው በዘፈቀደ የሚወጣ ሳይሆን አስበውበትና ተጠብበውበት የሚያወጡት መሆኑን ለመጠቆም ያህል ነው፡፡ ቢቻል ደግሞ ሞልቶ ከተረፈን ቋንቋ የራሳችንን ሀገር ቋንቋ አሕጽሮቶች ብንጠቀም ኩራትም ማንነትም ይሆንልናል፡፡ ባለሞያዎቹ እንዲያውም ቋንቋው ባለሆኑ ፊደሎች የተመሠረቱ አሕጽሮቶችን ‹‹Immigrant acronyms› ይሏቸዋል፡፡ የተሰደዱ አሕጽሮቶች እንደ ማለት ነው፡፡ ሰሞኑን እንዲያውም ሕገወጥ ስደት የሀገሪቱ መወያያ ጉዳይ እየሆነ ነውና እኛም ቢያንስ በሕገ ወጥ መንገድ እየተሰደዱ የሚመጡ ቃላትን ሃይ ብንላቸው ከመደናገረም፣ ከመወናገርም እንድን ይመስለኛል፡፡
