የወያኔ አገዛዝ የህዝብ ገንዘብ መዝረፉን እንደቀጠለ የአለም የምግብ ፕሮግራም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የምግብ ጥገኞች መሆናቸውን ገለጸ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል የሆነው የአለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ባወጣው ሪፖርት በያዝነው የፈረንጆች አመት 9.4 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የእርዳታ ጥገኞቹ ሆነው እንደቆዩ አስታውቋል።

ድርጅቱ፥ ከጥር እስከ ታህሳስ ላለው ጊዜ 880 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል እንዳስፈለገ እና ይህም በገንዘብ ሲሰላ 652 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር (ወይም ከ8.8 ቢሊዮን ብር በላይ) እንደሆነ ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ “ፎሬን ሎቢንግ ዳት ኦርግ” የተባለ እና የአለም መንግስታት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተጽእኖ ለማድረግ የሚያደርጓቸውን ሙከራዎች እየተከታተለ የሚያወጣ ድረ-ገጽ የወያኔ አገዛዝ ለዚህ ጉዳይ ያፈሰሰውን የገንዘብ መጠን አጋልጧል። እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2007 እና 2008 ብቻ የወያኔ አገዛዝ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብ ገንዘብ በአሜሪካን አገር ለሚገኙ ተሟጋቾች መክፈሉ ታውቋል። ከተሟጋች ድርጅቶቹ ውስጥ የከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ዘገባዎቻችን ርእስ የነበረው ዲ.ኤል.ኤ ፓይፐር ከግማሽ በላይ የሆነውን ክፍያ መውሰዱም ታውቋል።

በጉዳዩ ላይ ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየት የላኩ የፖለቲካ ተንታኝ፥ “ይህንንስ በቀጥታ ከአሜሪካ መንግስት ጋር የሚገናኝ ጉዳይ ስለሆነ በግልጽ አየነው፤ የወያኔ ባለስልጥናት የእርዳታ ጥገኛ ከሆነው ህዝብ ጉሮሮ እየነጠቁ በቀጥታ ወደ ኪሳቸው የሚያስገቡትን በአለም ዙሪያ ያሉ ባንኮች ይቁጠሩት” ብለዋል።