የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርት አቆሙ
(ሪፖርተር) — በደቡብ ክልል ከአዲስ አበባ በ500 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ‹‹ሳይነገረን እንዴት የምግብ ፕሮግራማችን ይለወጣል?›› በሚል በፈጠሩት ረብሻ፣ ከግንቦት 22 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርት ማቆማቸውን አንዳንድ ተማሪዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የተወሰኑ ቀናትን ሽሮ፣ የተወሰኑ ቀናትን ደግሞ ሥጋ እንደሚመገቡ የገለጹት ተማሪዎቹ፣ ግንቦት 22 ቀን 2003 ዓ.ም. ለምሳቸው መዘጋጀት የነበረበት ሥጋ ቢሆንም ሽሮ ተዘጋጅቶ ስለጠበቃቸው ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡
ተማሪዎቹ ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ለምግብ አዘጋጆቹ ሲያቀርቡ ‹‹የተለጠፈውን ማስታወቂያ ተመልከቱ›› የሚል ምላሽ ሲሰጣቸው፣ በማስታወቂያ ቦርዱ ላይ የተለጠፈውን ካነበቡ በኋላ በመጮህና የተለያዩ የተቃውሞ ማቅረባቸውን ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
የሥጋ ፕሮግራም ወደ ሽሮ መለወጡን የሚገልጸው ማስታወቂያ የተለወጠበትን ምክንያት ቢያውቁም፣ ‹‹ለምንም ይለወጥ ለምንም ተነግሮን፣ ልንስማማና ልንፈርም ይገባ ነበር፤›› በማለት ወደ ጩኸትና ረብሻ የተሸጋገሩት ተማሪዎቹ፣ የዩኒቨርሲቲው ሕንፃዎችንና የካፌ መስታወቶችን መሰባበራቸውንም ተናግረዋል፡፡
የተማሪዎቹ ረብሻ ያሳሰበው ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢ ፖሊስ ደውሎ ኃይል እንዲመጣ በማድረግ ፖሊሶች ቢደርሱም፣ ሊቋቋሙት እንደማይችሉ በመታወቁ የፌዴራል ፖሊስ ደርሶ የተማሪዎቹ ረብሻ ከግቢው እንዳይወጣ መቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ከግንቦት 22 እስከ ትናንትና ምሽት ድረስ ምግብም ሆነ ውኃ ሳያገኙ መቆየታቸውን ተማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ተማሪዎቹ፣ ‹‹መብታችን ያለፈቃዳችን ለምን ይነካል?›› በሚል ምግብ አዘጋጆቹ ከግቢው እንዲወጡላቸው ባደረጉት ተቃውሞ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር ሆነው እንዳስፈራሯቸውም ተናግረዋል፡፡
በተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ምክንያት ፌዴራል ፖሊስ ረብሻውን ለማስቆም ወደ ላይ በተከታታይ በሚተኩስበት ወቅት በድንጋጤ ራሳቸውን የሳቱ ተማሪዎች ወደ ጤና ጣቢያ መወሰዳቸውን፣ ረብሻውን አባብሰዋል የተባሉ ጥቂት ተማሪዎች መታሰራቸውንም ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያነሱትን ተቃውሞ ለማርገብና ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ ለመስጠት የደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በትናንትናው ዕለት በግቢው ተገኝተው ተማሪዎቹን አነጋግረዋቸዋል፡፡
‹‹ያለፈቃዳችን ለምን የምግብ ፕሮግራም ይቀየርብናል? የምግብ እጥረት አለብን፤ ምግብ አዘጋጆቹ ይቀየሩልን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች አስፈራርተውናል፣ ፖሊሶችም ደብድበውናልና ይጠየቁልን፤›› የሚሉና ሌሎችም 15 ጥያቄዎችን አንስተውላቸው፣ ‹‹ሁሉንም ባፋጣኝ ምላሽ እንሰጣለን፤ ባጠፉት ላይም ዕርምጃ እንወስዳለን፤›› የሚል ምላሽ መስጠታቸውንና ተማሪዎቹን እንዳረጋጓቸው ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
ሁለት ቀን ሙሉ ምግብ ያላገኙት ተማሪዎች ትናንትና ምሽት ላይ ራታቸውን ሊመገቡ መቻላቸውንም ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፈለቀ ታደሰን በስልክ አግኝተናቸው ስለተፈጠረው ችግር ማብራሪያ እንዲሰጡን ስንጠይቃቸው፣ ‹‹ገና ጉዳዮች ተጣርተው ያላላቁ ስለሆነ መግለጽ ያስቸግረኛል፤›› በማለት ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
በታምሩ ጽጌ