‹በባል እንዲህ አርገሽ ትጫወጫለሺ›


ሴትዮዋ ባሏ ሞቶ ዐርባውን ታወጣለች፡፡ እንዳጋጣሚ የባሏ ዐርባና የቅዱስ ገብርኤል በዓል ይገጥማል፡፡ እርሷም ሁለቱንም እደግሳለሁ ብላ ትነሣለች፡፡ ቅልጥ ያለ ድግስም ትደግሳለች፡፡ ‹ፈረስ የሚያስጋልብ› የሚባል ዓይነት ዳስ ይጣላል፡፡ አገሩ በሙሉ አልቀረም ይጠራል፡፡ በሀገራችን ድግስ ሲደገስ የተጋባዥ አጠራር ወግ አለው፡፡ ከካህናቱ ጀምሮ እስከ ጨዋው የሚጠራበት ሰዓት፣ የሚቀመጥበት ቦታና የሚቀርብለትም ነገር ይለያያል፡፡ ሴትዮዋ ይህንን አላወቀችም ሀገሩን ሁሉ በአንድ ላይ ጠርታ ድብልቅልቁን አወጣችው፡፡ ሁሉም ለመቀመጫና ለምግቡ ሲሻማ ድግሱ ተበለሻሸ፡፡ በተለይ የተዝካሩ ምንነትና ሥርዓት ያልገባቸው ሕጻናት ልጆች የሚያደርጉት ሩጫ አስገራሚ ሆነ፡፡ አብዛኞቹ ተጋባዦች በተዝካር ላይ የሚባለውን፣ የሚመረቀውንም ሆነ ሲወጣ የሚነገረውን የማያውቁ ነበሩ ፡፡ አስተናጋጆቹም ልምድ የሌላቸውና ነገሩ ያልገባቸው ነበሩና ችግሩን ከመፍታት ይልቅ እነርሱ ራሳቸው ችግሮች ሆኑ፡፡
በሁኔታው የተገረሙ የኔታ እንግዳው የተባሉ ካህን
ወይዘሮ አሰለፈች ታስገርሚያለሺ
ብስል ከጥሬውን ሁሉንም ጠርተሺ
በባል እንዲህ አርገሽ ትጫወቻለሺ
(‹በባል› ሲሉ በሰምና ወርቅ በአንድ በኩል ‹በባልሽ ላይ›[የባሏ ተዝካር ነበርና] በሌላም በኩል ‹በበዓሉ ላይ› ማለታቸው ነበር)
ብለው በመጨረሻ አሸበሸቡ ይባላል፡፡

 ይህ ታሪክ ትዝ ያለኝ ቅዳሜ ዕለት ነበረ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ ተጉዤ፡፡ ጥሪው ከቀኑ ሰባት ሰዓት ይል ነበርና በሰዓቱ ነበር የደረስነው፡፡ በቦሌ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መኪና አቁመን ወደ ታች ስንወርድ ሕዝቡ እንደጎርፍ ይወርድ ነበር፡፡ ‹ሃይገር› መኪኖች ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ እያመጡ ይዘረግፋሉ፡፡ እናቶች፣ አባቶች የተወሰኑ ወጣቶች፣ አንዳንዶቹም ከግንባታ ላይ ተነሥተው የመጡ የሚመስሉ ሠራተኞች ወደ ታች ይወርዳሉ፡፡ እኔም መርሐ ግብሩ ምን ዓይነት ቢሆን ነው ይህንን ሁሉና ይህንን ዓይነቱን ሕዝብ የሚያሳትፈው እያልኩ ጉጉቴን ጨመርኩ፡፡ በ‹ሃይገር› መኪኖቹ የፊት መስተዋት ላይ ‹የወረዳ እንትን ተሳታፊዎች› የሚል ተለጥፎባቸዋል፡፡ ከየወረዳው የተወጣጡ ነዋሪዎች መሆናቸውን ተረዳሁ፡፡ በምን መሥፈርት ይሆን ከአንድ ወረዳ ሕዝብ መካከል እነዚህ ተመርጠው የመጡት? እያልኩ እገረም ነበር፡፡

ወደ ሚሊኒየም አዳራሹ መግቢያ ስንደርስ ሰልፉ ከበሩ ግራና ቀኝ እንደ ዘንዶ ተጥመልምሏል፡፡ እኔ ደግሞ ሲፈጥረኝ ሁለት ነገር አልወድም ‹ሰልፍና ግፊያ›፡፡ መንግሥተ ሰማያት በሰልፍና ግፊያ የሚገባ ቢሆን ኖሮ ክርስትናዬን ዛሬውኑ እተወው ነበር፡፡ ተሰልፌና ተጋፍቼ እንደማልገባ አውቃለሁና፡፡ በኋላ ግን ‹ባጅ› የተሰጣችሁ ግቡ ሲባል ቅድሚያ አግኝቼ ገባሁ፡፡ የደኅንነት ሳጥኑን ፍተሻ አልፈን ስንገባ ሕዝብ ግጥም ብሏል፡፡
አስደናቂው ነገር የሚጀምረው እዚህ ነው፡፡
የተለያዩ ዓይነት እንግዶች ወደ አዳራሹ ተጋብዘዋል፡፡ ለእነርሱ የሚሆን ቦታ ግን አልተዘጋጀም፡፡ የተዘጋጀው ለመሪዎቹና ለተከታዮቻቸው ብቻ ነው፡፡ ከተለያዩ ሀገሮች የመጡ፣ ልዩ መግቢያ የተሰጣቸው ሰዎች በአዳራሹ ውስጥ እዚህም እዚያም ቆመዋል፡፡ ወንበሮቹ ከየወረዳው በመጡ ነዋሪዎች አስቀድመው ተይዘዋል፡፡ የቀሩት ወንበሮች ከዐሥር አይበልጡም ነበር፡፡ አንዳንዶቹ በፈረንሳይኛ፣ ሌሎቹም በእንግሊዝኛ ያማርራሉ፤ በዐረብኛና በፖርቹጊዝ የሚራገሙም ነበሩ፡፡ በሌሎች በሮች በኩል ወደሚገባባቸው ሌሎች መቀመጫዎች ለመግባት ይጠይቃሉ፤ የሚከለክል እንጂ ለምን እንደተከለከለ መልስ የሚሰጥ ግን አልነበረም፡፡ ‹የአስተባባሪዎቹ ቢሮ› የሚል ወደተለጠፈበት ክፍል ብዙዎች ይገቡና የሚያስተናግዳቸው አጥተው ንዴታቸውንና ቁጣቸውን ጨምረው ይመለሳሉ፡፡  
ወንበሮቹ የተደረደሩት በመካከለኛው መደዳ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ወንበሮች እንደተከመሩ ናቸው፡፡ መቆሙ የሰለቻቸው የአዲስ አበባ ወረዳዎች ተሳታፊዎች ከተከመሩት ወንበሮች መናድ ጀመሩ፡፡ ያኔ አዲስና በፕሮግራሙ ያልተካተተ የሃምሳኛ ዓመት ትንግርት ተፈጠረ፡፡ ወንበር ለማግኘት የሚደረግ ትርምስ፡፡ እርግጥ ነው በአፍሪካ ወንበር እንዲሁ በቀላሉ አትገኝም፤ በብዙ ትርምስ እንጂ፡፡ አንዳንዱ አትርፎ ለመሸጥ በሚመስል መልኩ ስድስትና ሰባት ወንበር ተሸክሞ ይሄዳል፣ ሌላው ወንበሬን ወሰድክብኝ ብሎ ይጣላል፡፡ ወንበር ያገኘው ደግሞ በመሰለው መልኩ እየደረደረ ጓደኛውን ይጣራል፡፡ እናቶችና አዛውንት፣ ዐቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞችን ያስታወሳቸውና ያዘነላቸው አልነበረም፡፡
እየቆየ የተከመረውም ወንበር አለቀና ሕዝቡ መሬት ላይ መቀመጥ ጀመረ፡፡ ይኼኔ ነበር አስገራሚ ማስታወቂያ ከመድረኩ መሰማት የጀመረው፡፡ ‹‹የፊተኞቹ ወንበሮች ለዐለም ዐቀፍ እንግዶች የተያዙ ስለሆነ፣ እንግዶቹም ቦታ አጥተው ስለቆሙ እባካችሁ ተነሡ ይላሉ አዘጋጅ ግሩፖቹ›› የሚል ማስታወቂያ ተደጋግሞ ተነገረ፡፡ ይህ በሠፈራችን ሠርግ እንኳን የማይደረግ ስሕተት እንዴት በአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት ሊከሰት እንደቻለ አስገራሚ ነው፡፡ በብዙ ሠርጎች ለሙሽሮች አጃቢዎች የሚዘጋጁ ወንበሮች ፊታቸውን በዞሩ ወንበሮች ታጥረው በተመደቡ ሰዎች ይጠበቃሉ፡፡ እዚህ ግን ለእንግዶች የተዘጋጁ መሆናቸውን የሚናገሩ ጠባቂዎች እንኳን አልነበሩም፡፡ ሌላው ቀርቶ በገመድ አጥሮ ጠብቆ ማቆየት ይቻል ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ካለፈ በኋላ ራሳቸው እንግዶቹ ቆመው ‹ተነሡላቸው› የሚል ቀልድ መቀለድ ግን ራስን ከማስገመት ያለፈ ዋጋ አልነበረውም፡፡ ማስታወቂያውን ሰምቶ ቦታ የለቀቀም አልነበረም፡፡ እንዲያውም ብዙዎች ወንበሮቻቸውን ወደፊት እያስጠጉ መተላለፊያውንም ዘጉት፡፡
በዚህ ክርክር መካከል አውቶቡሳቸውን ሞልተው የአፍሪካ ኅብረት ሠራተኞች መጡ፡፡ ከመላዋ አፍሪካ የተወጣጡትና አህጉሪቷን ወክለው የሚሠሩት እነዚህ ሠራተኞች አዳራሽ ሲገቡ ተዘጋጅቶላችኋል የተባሉት ቦታ ሞልቶ ነበር፡፡ ‹ሸክላ ሠሪ በገል ይበላል› የሚባለው እነርሱ ላይ አልሠራም፡፡ ከመድረኩም ‹እባካችሁ እንግዳ እናክብር፣ ተነሡ› የሚለው ማሳሰቢያም ሰሚ አላገኘም፡፡ ‹ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም› በሚል ሕዝብ መካከል ይህንን ማሳሰቢያ መናገር ድሮም ፍሬ ሊኖረው የሚችል አልነበረም፡፡
ፕሮግራሙ ተጀመረ፡፡ የአልጀሪያ ሙዚቀኛ በቤኒን ከበሮ መቺዎች ታጅቦ አምስት ሙዚቃዎችን አከታትሎ አቀረበ፡፡ ለአንድ ሙዚቀኛ፣ ያውም ከወንበሩ ሳይነሣ አምስት ሙዚቃ የማቅረብ ዕድል ከተሰጠው መላው ቀልጧል ማለት ነው አልን፡፡ እርሱም ቢሆን ‹ራሴን በራሴ ካላንቆለጳጳስኩት ማን ያንቆለጳጵስልኛል› የሚለውን የአማርኛ አባባል ሰምቶ ነው መሰል እርሱ የአልጀርያ ሰው መሆኑን፣ ከበሮ መቺዎቹም ከቤኒን መምጣታቸውን ራሱ ነገረን እንጂ የተናገረለት መርሐ ግብር መሪ አልነበረም፡፡ ምናልባት የአዲስ አበባ ወረዳዎች ተሳታፊዎች ያውቁታል ተብሎ ተገምቶ ይሆናል፡፡
እየቆዩም የልዩ ልዩ የአፍሪካ ሀገሮች ሙዚቀኞች እየመጡ እየሄዱ ባህላዊ ሙዚቃቸውን አቀረቡ፡፡ አልፎ አልፎ በስክሪኑ ላይ ከሚጻፈው በቀር አዳራሹን ለሞሉት የአዲስ አበባ ወረዳዎች ተሳታፊዎች ማን የት ሀገር እንደሆነና የሚያቀርበውም ነገር ትርጉም ምን እንደሆነ የሚነግረን አልነበረም፡፡ በአካባቢያችን የነበሩት እናቶችና አባቶች እንደ ሰርከስ ትርዒት እግራቸውን ወዲያና ወዲህ የሚያደርጉትን ሴት ዳንሰኞች እያዩ ‹ኤዲያ ምኒቷ ናት ባካችሁ› እያሉ ይገረሙ ነበር፡፡ ሙዚቃው እየጨመረ ሲሄድ በአዳራሹ ውስጥ ከአፍ እስከ ገደቡ ሞልቶ የነበረው ሕዝብ እንደ ስንቅ እየቀለለ መጣ፡፡ እንዲያ ለወንበር ሲሻማ የነበረው ሰው፣ ታግሎ ያመጣውን ወንበር እየተወው ሄደ፡፡ ለነገሩ ልማድ ነው ታግለው ያገኙትን ወንበር እየተው መሄድ፡፡
ብዙዎቹ በፈረንሳይኛና በእንግሊዝኛ የሚተላለፈውን መልእክት ሊረዱት አልቻሉም፡፡ ከአሥር ሺ በላይ የወረዳ ነዋሪዎችን ጠርቶ ፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ ማውራት ባሎን በሚሊኒየም ነው የሆነው፡፡ ምናለ እነዚህን ቋንቋዎች ወደ አማርኛ የሚተረጉም ሰው ከመድረክ ቢኖር፡፡ ያለበለዚያ ደግሞ ቋንቋዎችን ሊረዳ የሚችል ተጋባዥ ቢጠራ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬ 50 ዓመት በአዲስ አበባ ሲመሠረት የመክፈቻውን ንግግር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያደረጉት በአማርኛ ነበር፡፡ የዛሬ ሃምሳ ዓመት መክፈቻ የነበረ ቋንቋ ሃምሳኛ ዓመቱ ሲከበር መተርጎሚያ እንኳን መሆን አቃተው፡፡
መሪዎቹ መምጣታቸው ተነግሮ ዋናው መርሐ ግብር በአፍሪካ ኅብረት መዝሙር ተከፈተ፡፡ ተነሡና አብራችሁ መዝሙሩን በሉ ተባልን፡፡ አሁን ምን አለ በግራና በቀኝ በነበሩት ስክሪኖች የመዝሙሩን ስንኞች ቢያቀርቡልን? ከየት አምጥተን ነው የአፍሪካ ኅብረትን መዝሙር አብረን የምንለው? ስክሪኑ ቅዳሜ ማታ የሚተላለፈውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ እየደጋገመ ሲያስተዋውቅ እንዴት ይህንን ማድረግ አቃተው?
ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ዴላሚና ዙማ የእንግሊዝኛ ንግግር በኋላም የልዩ ልዩ ሀገሮች ሙዚቀኞች ቀጠሉ፡፡ የየት ሀገር ባህል ነው? ምን እያሉ ነው? በዐሥር ሺዎች ለሚቆጠሩት የወረዳ ተሳታፊዎች የሚነግራቸው አልነበረም፡፡ እነርሱም ነገር ዓለሙ አልጥም ሲላቸው ‹ዋናው ፊት ማስመታታችን ነው› ብለው ነው መሰል አዳራሹን እየለቀቁ ወጡ፡፡ ከዐሥር ሰዓት በኋላም አዳራሹ ድግስ እንዳለቀበት ተዝካር ባዶውን መቅረት ጀመረ፡፡
መሪዎቹም ሆኑ መርሐ ግብር መሪዎቹ፣ በስክሪን ብቅ እያሉ ንባብ የሚያሰሙንም ተናጋሪዎቹ ስለ አፍሪካ የነገው ትውልድ እየደጋገሙ ያነሡ ነበር፡፡ በአዳራሹ የታደሙት አብዛኞቹ ‹የየወረዳው ተሳታፊዎች› ግን የነገው ትውልዶች› ሳይሆኑ ‹የትናንትናው› ነበሩ፡፡ የነገው ትውልድ እንዲሳተፍ ከተፈለገ ከየወረዳዎቹ ከማምጣት ከየኮሌጆቹ፣ ከየትምህርት ቤቶቹና ማሠልጠኛዎቹ ወጣቶችን መጥራት ይቻል ነበር፡፡ በአንድ በኩል ሙዚቃውም የሚመስጣቸው፣ በሌላም በኩል ቋንቋውም የሚገባቸው እነርሱ ነበሩ፡፡ ከዚህም ባለፈ ደግሞ ስለ ነገው ትውልድ የሚነገረውን ሰምተው ለመተግበር እድሉ የነበራቸውም እነርሱ ናቸው፡፡
ከሁሉም በላይ ይህንን መሰል ዝግጅቶችን ለመሳተፍ ፍላጎት ይጠይቃል፡፡ በወረዳ ውክልና የሚሆን አይደለም፡፡ ከየወረዳዎቹ ይምጡ ከተባለም መርሐ ግብሩን የሚመጥኑ፣ ነገሩም የሚስባቸውና የሚገባቸው ቢሆኑ መልካም ነበር፡፡
በመርሐ ግብሩ መገባደጃ ላይ የነፍስ ኄር ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊን አጭር የሕይወት ጉዞ የሚያሳይ ፊልም ቀርቦ ነበር፡፡ በዓሉ የመላ አፍሪካውያን በዓል እንደመሆኑ መጠን ከሁሉም መሪዎች ተነጥሎ የአቶ መለስ ታሪክ ብቻ ባይቀርብ መልካም ነበር፡፡ እንደ እርሳቸው ሁሉ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያጣናቸው ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችም አሉ፡፡ የእነዚህን መሪዎች አጭር ታሪክ አካትቶ ቢቀርብ ኖሮ ከበዓሉ ጋር ይሄድ ነበር፡፡ ፓን አፍሪኒዝም የሚለውን ሃሳብ በሰፊው እየሰበኩ የአንድን ሀገር ጉዳይ ብቻ በአፍሪካ በዓል ላይ ማቅረብ ከሃሳቡ ጋር አይሄድም፡፡ የግድ መቅረብ ነበረበት ከተባለ ደግሞ ሕዝብ ከመሄዱ በፊት እንዲቀርብ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ 
አሁን ግራና ቀኝ ዘወር ስል በአዳራሹ የማያቸው የሌሎች ሀገሮች ዜጎችንና በጉባኤው ውስጥ ሥራ ተሰጥቷቸው የግድ መቀመጥ ያለባቸውን ሠራተኞች ብቻ ነው፡፡ የሚከልሉት ሰው አለመኖሩን ሲያዩ ጋዜጠኞችም በኋላ በኩል ከተሰጣቸው ቦታ እየለቀቁ ፊት ለፊት መጥተው ካሜራዎቻቸውን ተከሉ፡፡ ሰው ከሄደ፣ አዳራሹም ወና መሆን ከጀመረ በኋላ ነበር የብዙዎቹ መሪዎች ንግግር መደረግ የጀመረው፡፡ እኔ የምለው ይሄ ረጅምና ለጆሮ የማይስብ ንግግር ማድረግ የአፍሪካ መሪዎች ጠባይ ነው እንዴ፡፡ እንዲያ ባለ አዳራሽ፣ በዚያ በረፈደ ሰዓት እጥር ምጥን ያለ ጆሮ ገብ የሆነ ንግግር ቢያደርጉ ምናለ፡፡ አፍሪካ ተረቶች፣ ምሳሌዎችና አፈ ታሪኮች የሞሉባት አህጉር ናት፡፡ ምናለ እነዚህን ተጠቅመው ንግግራቸውን ቢያንስ ደስ ብሎን እንድናዳምጠው ቢያደርጉ፡፡ እኔ ከዑጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በቀር አፍሪካዊ ተረትና ምሳሌ የጠቀሰ መሪ አልሰማሁም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም አንድ ደስጣ ወረቀት የሚያህል ንግግር  ይዘው ብቅ ሲሉ ልባችን ድክም ይል ነበር፡፡ እንዲያም ቢሆን ሲሰሙት የሚጥም፣ ጆሮ ገብ የሆነ ስሜት ያለው ንግግር ቢያደርጉ ምን አለ? ንግግርኮ የተጻፈ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ሰው ሊሰማው በሚችል መልኩ ማቅረብም ነው፡፡ ያ መሆን ካልቻለ ደግሞ ‹የንግግር ጥበብ መጀመሪያ ነገር ማሳጠር ነው› የሚለውን መተግበር ነው፡፡
ከዩዌሪ ሙሴቪኒ ንግግር በቀር  ቅርጽና መልክ ያለው፣ ነገሮችን ነጥብ በነጥብ ያስቀመጠ፣ ፍልስፍናዊና ተጠየቃዊ የሆነ ንግግር አልሰማሁም፡፡ ሙሴቪኒ አፍሪካውያን ሊያነሷቸውና ሊመልሷቸው ይገባል ብለው ያቀረቧቸው አምስት ጥያቄዎችና የሰጧቸው መልሶች አስገራሚ ነበሩ፡፡ ለቅኝ መገዛታችን፣ በባርነት ለመሸጣችንና ላለማደጋችን አውሮፓውያንን ብቻ ሳይሆን ቀደምቶቻችንንም ሆነ ራሳችንን ጭምር መውቀስ አለብን ሲሉ ያቀረቡት ንግግር በአዳራሹ የነበሩትን በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ቁጭ ብድግ ያስደረገ ነበር፡፡ 
የመሪዎቹ ንግግር እየቀጠለ ሲሄድ አንድ ወር ሙሉ ሲያጠኑ የከረሙት ሕጻናት የማቅረቢያ ጊዜያቸው እያለፈ ነበር፡፡ እነዚህ ልጆች አንድ ወር ሙሉ ለአፍሪካ ኅብረት ሃምሳኛ በዓል ታቀርባላችሁ ተብለው ሲያጠኑ መቆየታቸውን፣ ዛሬም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምረው ወደ አዳራሹ መምጣታቸውን እናቶቻቸው በኀዘንና በምሬት ነበር የሚተቹት፡፡ የልጆቹ መርሐ ግብር ግን ይቀርባል ከተባለበት ሰዓት እያለፈ፣ እነርሱም ወደ ድካምና ረሃብ እያመሩ መሆኑን ነበር የሚናገሩት፡፡ ለአልጀሪያው ሙዚቀኛ አምስት ሙዚቃ ከመስጠት ለእነዚህ ልጆች አንድ ዕድል መስጠት እንዴት ሳይቻል ቀረ፡፡ ሲሆን ልጆች ናቸውና አስቀድመው አቅርበው ወደየቤታቸው መጓዝ ነበረባቸው ካልሆነ ደግሞ ሳይመሽ እነርሱን መሸኘት ይገባ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል፣ የአፍሪካ ሕዳሴ በሚነገርበት አዳራሽ የሕዳሴው ተስፋዎች ጊዜ የሚሰጣቸው አጥተው ከአዳራሹ ጀርባ እያዛጉ ነበር፡፡
ሕጻናቱ ያዛጋሉ፤ መሪዎቹ ንግግራቸውን ተራ በተራ ይቀጥላሉ፡፡ የየወረዳዎቹ ተሳታፊዎችም ጠቅልለው ከአዳራሹ ወጥተዋል፡፡ የሚያጨበጭብ እንኳን አልነበረም፡፡ ወደ ሁለት ሰዓት አካባቢ የሕጻናቱ መርሐ ግብር መታጠፉ ለልጆቹ ተነገራቸው፡፡ በየደቂቃው ስለ ነገዎቹ የአፍሪካ ትውልዶች እየተነገረ የእነዚህን ትውልዶች ፕሮግራም በማጠፍ ስለ አፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት መልካም ትዝታ እንዳይኖራቸው ተደረገ፡፡ መሪዎቹ ሁሉ በየንግግሮቻቸው በአፍሪካ ሕጻናትና ወጣቶች ላይ ያላቸውን ተስፋ ነበር የሚናገሩት፡፡ ሕጻናቱ ግን ፕሮግራማቸው ተሠርዞ በኀዘን እየወጡ ነበር፡፡
እኛም ተዳክመን ሁለት ሰዓት ላይ ለመውጣት ስንዘጋጅ ‹የለመደብኝ አይቅርብኝ› ብሎ መብራት ኃይል መብራቱን ድርግም አደረገው፡፡ መሪዎቹ በጨለማ ተዋጡ፡፡ እኛም እንዲህ ችግራችንን እዩልን እንጂ፡፡ መብራት ኃይልኮ እራት እየበላን፣ ሠርግ እየደገስን፣ በዓል እያከበርን፣ ትምህርት እየተማርን፣ ቅዳሴ እየቀደስን እንዲህ ድንገት ነው ድርግም የሚያደርግብን አልን በልባችን፡፡ የአዳራሹ ጀነሬተር ‹አውቶማቲክ› አልመሰለኝም፡፡ ሞተሩ እስከሚነሳ ረዥም ሰዓት ፈጅቷል፡፡ በዚህ መካከልም መሪዎቻችን በሞባይል መብራቶች በያሉበት ተቀምጠዋል፡፡ አዳራሹ በጨለማ ከመዋጡ ጥቂት ቀደም ብሎ ግን መሪዎቹ ‹አፍሪካ የጨለማ አህጉር እየተባለች ስሟ በመጥፋቱ›  እየተቆጩ ነበር፡፡ ይህንን ቁጭት ከሰማን ከደቂቃዎች በኋላ ግን አዳራሹ በጨለማ ተዋጠ፡፡
ስንወጣ ‹ፓን አፍሪካኒዝምና የአፍሪካ ሕዳሴ› የሚለውን ፖስተር በመውጫው በኩል በትልቁ ተሰቅሎ እያየነው ነበር፡፡