ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት (1935-2013) ዐረፉ
click here for pdf
በኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ሊቅ የሆኑትና አያሌ መጻሕፍትንና የጥናት ጽሑፎችን በልዩ ልዩ ብሔራዊና ሀገር ዐቀፍ መድረኮች ያቀረቡት፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም እንዲመሠረት ተጋድሎ ካደረጉ ምሁራን አንዱ የሆኑት፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ መዛግብት በማይክሮ ፊልም እንዲሰባሰቡ፣ እንዲጠኑና እንዲታወቁ ከደከሙት የመጀመርያዎቹ ሊቃውንት መካከል የሚቆጠሩት፣ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ግንቦት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. በአሜሪካን አገር ቺካጎ ከተማ ዐረፉ፡፡
የኢትዮጵያ መካከለኛው ዘመን ታሪክ ሊቅ የነበሩት ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በተመራማሪነትና በተለያዩ የአመራር ኃላፊነቶች እጅግ ስኬታማ ሕይወት የመሩ ምሁር ነበሩ፡፡ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክን በተመለከተ አያሌ የምርምር ሥራዎችን ለአገርና ለዓለም ያበረከቱ ሲሆን፤ በተለይም ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት በኢትዮጵያ (Church and State in Ethiopia, 1270-1527) የተሰኘው መጽሐፋቸው በመስኩ እስካሁንም ወደር ያልተገኘለት የምርምር ውጤት በመሆኑ ዓለም አቀፍ እውቅናን አስገኝቶላቸዋል፡፡
የረቀቀ የምርምር ችሎታቸው ለተማሪዎቻቸው ትልቅ ተምሳሌት የነበረ ሲሆን፤ ይህንኑ የምርምር ቴክኒክም ለተማሪዎቻቸው በድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ውስጥ ያካሂዱ በነበረው ልዩ የመስክ ምርምር ዘይቤና በከፍተኛ ጥንቃቄ ያርሟቸው በነበሩት ድርሳኖች አማካይነት ለተማሪዎቻቸው ለማስተላለፍ የበቁ ምሁር ነበሩ፡፡ የምርምር ሥራዎቻቸው ዓለም አቀፍ እውቅናን አትርፈውላቸው፣ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ (ሎስ አንጀለስ)፣ በኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ፣ በበክኔል ዩኒቨርሲቲ እና ኧርባና ሻምፔን በሚገኘው ኢሊኖይ ዩኒቨርሲቲ በጎብኚ ፕሮፌሰርነት ለማገልገል በቅተዋል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የኮሌጅ ደ ፍራንስ የክብር ሜዳይና የድኅረ ምረቃ ትምህርት ያካሄዱበት ከነበረው የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን የአፍሪቃና እስያ ጥናት ማዕከል የክብር ፌሎውነት ሽልማት አስገኝቶላቸዋል፡፡
ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ከምርምር መስኩ ባሻገር ለአያሌ ዓመታት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በተለያዩ የአመራር ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡- እ.ኤ.አ. ከ1977-84 በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተርነት፤ ከ1986-92 በሳሻል ሳይንስ ኮሌጅ ዲንነት፤ ከ1995-99 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ዳይሬክተርነትና ዋና ኤዲተርነት፡፡ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተርነታቸው፣ ተቋሙን ፈታኝ በሆኑ ዓመታት ብቁ አመራር ከመስጠታቸውም በላይ 8ኛውን ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ በማዘጋጀት የኢትዮጵያ ጥናት ባለቤቱ ወደ ሆነችው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ምንጊዜም የማይዘነጋ ውለታ ጥለው አልፈዋል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስም አሁን እንደምናየው ትልቅ አሳታሚ ድርጅት ለመሆን የበቃው ፕሮፌሰር ታደሰ በጣሉት መሠረት ላይ ነው፡፡
በአያሌው የደከሙለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የማይክሮ ፊልም ቤተ መጻሕፍት ክፍል እስካሁንም በስማቸው እየተጠራ ይገኛል፡፡
ፕሮፌሰር ታደሰ ያረፉት ባደረባቸው ሕመም ለረጅም ጊዜ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሲሆን፤ ባለቤታቸውን ወ/ሮ አልማዝ ሥዩምን ከ10 ወር በኋላ ተከትለው ነው፡፡ ሦስት ሴት ልጆቻቸው በአሜሪካን አገር በከፍተኛ ኃላፊነት ሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡
