ይድረስ ለማታውቁን ለምናውቃችሁ


እንዴው በዚያ የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ሰሞን እጅግ የታወቁት የእንግሊዝ እግር ኳስ አሠልጣኝ አንዱን እንኳን የብሔራዊ ቡድናችንን ተጫዋች ስም መጥራት አቃታቸው አሉ፡፡ ትዝብት ነው፡፡ እኛ ከነጫማና ከነከናቴራ ቁጥራችሁ ልቅም አድርገን ስናውቃችሁ፤ ምነው ጃል እንዲያ ሠላሳ ዓመት ለፍተን ያፈራናቸውን ተጨዋቾች እንዴት ስማቸውን አያውቋቸውም፡፡
ለመሆኑ ኢትዮጵያን የማያውቅ ሰው የእንግሊዝን እግር ኳስ ማሠልጠኑ ራሱ ተገቢ ነበር? ይህችን በአፍሪካ ውስጥ ቅኝ ያልተገዛች፣ በአድዋ ጦርነት ነጭን ያንበረከከች፣ የራስዋ ፊደልና ዜማ ያላት፣ የራስዋ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ያላትን፣ በዓለም አንደኛ የሆነችውን ኢትዮጵያን ሳያውቁ እንዴት የእንግሊዝን ትልቅ ክለብ ሊያሠለጥኑ በቁ፡፡ እነዚህ ፈረንጆች ለእግር እንጂ ለጭንቅላት ግድ የላቸውም ማለት ነው? እነዚህን ልጆች ለማፍራት ሠላሳ ዓመት እንደፈጀብን እንዴት አድርገን በነገርንዎ፤ ታድያ እነዚህን ዓለም ያወቃቸውን ልጆቻችንን ካላወቋቸውማ ሌሎቻችንንማ ከነመፈጠራችንም አያውቁንም ማለት ነው፡፡

እኛ እዚህ በእናንተ ምክንያት ስንት መከራ እንዳየን አያውቁልንም ማለት ነዋ፡፡ ስንት ስብሰባ ዛሬ የማንቸስተር ጨዋታ ስላለ፣ አርሴናል ስለሚጋጠም እየተባለ እንደተሠረዘ አታውቁልንም ማለት ነዋ፤ መጋቢት 3 ቀን የተወለደ ልጅ በእናንተ ጨዋታ ምክንያት ‹የአርሴናል ጨዋታ ከሚያልፍ አንተ መጋቢት ስድስት ብትወለድ ይሻላል› ተብሎ ልደቱ መጋቢት ስድስት መከበሩን አታውቁልንማ፡፡ ይህንን ሁሉ ተውት፤ በስንት ጭቅጭቅ የቆረጡትን የሠርግ ቀናቸውን አርሴና ማንቼ ይጋጠማሉ ብለው፣ እነርሱ የተሸነፉ እንደሆነ እኔና አንቺ ከምንገጥም የእነርሱ ጨዋታ ከእኛ ሠርግ ጋር እንዳይገጥም እናድርገው ብለው መሠረዛቸውን አታውቁልንማ፡፡
የእናንተማ ድፍረት መች ተዘርዝሮ ያልቃል፡፡ እንኳንና ዓለማዊው መንፈሳዊው ፕሮግራም ሲወጣ እንኳን መጀመርያ የእናንተ ፕሮግራም ታይቶ ነው፡፡ እናንተ በቴሌቭዥን ብቅ ካላችሁ ድመት ብቅ እንዳለበት የአይጥ ሠፈር አንድ ሰው በሠፈሩ ዝር አይልም፡፡ ደግነቱ አውቃችሁትም ይሁን ሳታውቁት በቅዳሴና በሶላት ሰዓት አለመጫወታችሁ በጀ እንጂ አስቀዳሽና ሰጋጅ ከየት ይመጣ ነበር፡፡
እና ይህንን ሁሉ ለእናንተ ፍቅር ስንል ማድረጋችንን አታውቁልንማ፡፡
እናንተኮ እዚህ ሀገር የጫት ቤት ስም ሆናችኋል፤ የሐበሻ ቀሚስ ሆናችኋል፤ የቦሎ መለጠፊያ ሆናችኋል፤ ሻርፕ ሆናችኋል፤ ነጠላ ሆናችኋል፤ የምግብ ትሪ ሆናችኋል፤ ሻሂ ቤት ሆናችኋል፣ የምግብ ዓይነት ሆናችኋል፤ እኛ እናንተ ምን እንደበላችሁ፣ ምን እንደ ጠጣችሁ፣ ምን እንደምትወዱ፣ ምን እንደምትጠሉ፤ የትኛው ጭማቂ፣ የትኛው ሾርባ፣ የትኛው ጥብስ፣ የትኛው ቴላቲሊ እንደሚማርካችሁ፤ ከነ ሜኖ ዝርዝሩ ስናጠና እየዋልን፡፡
ቆይ ታድያ የማታውቁልን ከሆነ ልብሳችሁን ለብሰን፣ ማልያችሁን አጥልቀን፣ ሻርፓችሁን ተከናንበን፤ ዐርማችሁን አንግበን፣ ስማችሁን ቡዳ እንደያዘው ሰው ስንጠራ የምንውለው ለምንድን ነው? ቆይ ታድያ ካላወቃችሁን ቤታችንን ትተን፣ አዳራሽ ከትመን፣ አንዳንድ ጨብጠን፣ ዕንቅልፋችን አጥተን፣ በሆታ እየዘመርን እስከ ዕኩለ ሌሊት ለምን እንደግፋችኋለን፡፡
ደግሞ ስንሰማ እናንተ የምታውቁት የ ‹ኤ› ቡድን፣ የ‹ቢ› ቡድን የ‹ሲ› ቡድን ብቻ ነው አሉ፡፡ እዚህ እኛ ሀገር በእናንተ ስም የተቋቋምነውን ቡድኖች ምንም አታውቁንም ማለት ነው፡፡ ታድያ ማነው ያደራጀን፤ ያደለው ቅድመ ዕውቅናና ዕውቅና ይሰጣል፤ እናንተ ከነመፈጠራችንም አታውቁትም፡፡ ትዝብት ነው ትርፉ፡፡
እናንተ ምን ታደርጉ፤ እናንተ በሚሊዮን እየተከፈላችሁ የምትጫወቱትን ጨዋታ እኛ የአንድ ብር ዳቦ ገምጠን እናይላችኋለን፡፡ እናንተ ለእግራችሁ፣ ለጥፍራችሁ፣ ለጣታችሁ ሳይቀር ኢንሹራንስ ተከፍሏችሁ ስትጫወቱ፣ እኛ ለነገ ምሳ ማግኘታችንን እንኳን ዋስትና ሳይኖረን የተተመነውን ሁሉ ከፍለን እናያችኋለን፤
ለነገሩ በኛም አይፈረድም፡፡ ድሮ ድሮ ‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ› ነበር የሚባለው፡፡ አሁንማ ተቀይሮ ‹በእንግሊዝ ጨዋታ አይቆጡም ጌታ› ሆኗልኮ፡፡ አሸነፋችሁም፣ ተሸነፋችሁም፣ ደከማችሁም፣ በረታችሁም፣ ባለጋችሁም፣ ተቀጣችሁም፣ ወጣችሁም፣ ገባችሁም ስለ እናንተ እንደልብ ማውራት ይቻላል፡፡ መጻፍ ይቻላል፡፡ ፈቃድ የሚቀማ የለ፤ ፍርድ ቤት የሚያቆም የለ፡፡ በእናንተ ላይ ለመተቸትና፣ ለመራቀቅ፣ ለመተንተንና ለመከራከር የምናገኘውን ነጻነት በማን ላይ እናገኘዋለን፡፡ ይህ ነጻነትኮ እንኳን በፖለቲከኞቹ ላይ በጊዮርጊስና በቡና፣ በደደቢትና በንግድ ባንክ፣ በመብራት ኃይልና በአዋሳ ከነማ ቡድኖች ላይ እንኳን አይገኝም፡፡ ይህን ይህን ሳስበው እንኳን ኖራችሁ ያሰኘኛል፡፡ እናንተ ባትኖሩ ስለምን እንከራከር ነበር?  
ረስቼው ነበር፤ ይልቅ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ እንዲህ የማታውቁን ከሆነ የት ልትሰሟቸው ነው ታድያ የሀገራችን ጋዜጠኞችና የሀገራችን ስፖርት ተንታኞች ቬንገር ይህን ማድረግ አለባቸው፣ ፈርጉሰን ይህንን ማድረግ የለባቸውም፡፡ ሩኒ እንዲህ ቢያደርግ ጥሩ ነው፣ ቫምፐርሲ ይህ ምግብ ይሻለዋል፣ ላምፓርድ ከእንትና ጋር መጣላት አልነበረበትም እያሉ ልባቸው እስኪወልቅ ምክር የሚሰጧችሁ፤ እና ይህንን በኤፍ ኤም የሚሰጣችሁን ምክርና ተግሣጽ፣ ይህንን ሁሉ የባለሞያዎቻችንን ትንታኔ፣ አትሰሙትም ማለት ነው? እኛኮ አንዳንድ ሬዲዮ ጣቢያዎች ‹በኦን ላይን እንገኛለን› ሲሉን የምትሰሟቸው ይመስለን ነበር፡፡ እንዴው ማ ይሙት አንዳንድ አሰላለፋችሁን የምትቀይሩት እኛ የሰጠናችሁን ሃሳብ ሰምታችሁ አይደለም፤ ወይስ በኮፒ ራይት እንዳትከሰሱ ፈርታችሁ ነው፡፡
እንዴው ግዴለም ለእኔ ንገሩኝ፤ ከአንዳንድ ጋዜጠኞቻችን ጋር በስልክ አትገናኙም? ኢሜይል አትደራረጉም? ምሥጢር አታሾልኩላቸውም? ታድያ እንዴት ነው ነገሩ፤ ዛሬ ማታ እዚህ አመሹ፣ እንዲህ ዓይነት ሕልም አዩ፣ አሟቸው ነበር፣ ሲያቃዣቸው ነበር፣ የበሉት ምግብ ሌሊቱኑ አልተስማማቸውም ሲሉንኮ ደውለውላችሁ ወይም ደውላችሁላቸው የተገናኛችሁ ይመስለን ነበር፡፡ ለካስ ጥንቆላ ነው፡፡
ይኼው ልጆቻችን ወደፊት እንደ ቴዎድሮስ ጀግና፣ እንደ ምኒልክ ጥበበኛ፣ እንደ ዓምደ ጽዮን ደፋር፣ እንደ ላሊበላ አርቆ አሳቢ፣ እንደ ዮሐንስ ታጋሽ፣ እንደ ሐዲስ ዓለማየሁ ደራሲ፣ እንደ በዓሉ ግርማ ጋዜጠኛ፣ እንደ ቅጣው እጅጉ ሳይንቲስት፣ እንደ አፈወርቅ ተክሌ ሰዓሊ፣ እንደ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ባለ ቅኔ፣ እንደ በላይ ዘለቀ ቆፍጣና ወታደር እንሆናለን አይሉምኮ፡፡ አቆራረጣቸው፣ አካሄዳቸው፣ አጨዋወታቸው እንደ እናንተ ሆኗል፡፡ መሆን የሚፈልጉት ሁሉ ሩኒን፣ ቫምፐርሲን፣ ሜሲን፣ ድሮግባን፣ ሮናልዶን ሆኗል፡፡ ከመቼ አድገን፣ ታዋቂ ተጨዋች ሆነን ለእንግሊዝ በተሸጥን ይላሉ፡፡
አይ የአድዋ ጀግኖች ተሸወዳችሁ፡፡ እናንተ ሰው ተሸጦ ወደ ፈረንጅ ሀገር እንዳይሄድ ብላችሁ አልነበረም እንዴ የተዋጋችሁት? እኛ እንደ ሌሎቹ አፍሪካውያን ወገኖቻችን በሠንሠለት ታሥረን፣ ከሀገራችን ወጥተን፣ ባዕድ ምድር ተሽጠን እንዳንሄድ አልነበረም እንዴ የተዋደቃችሁት? አሁንማ መሸጥ ልማድ ሆኖ፣ ልጆቻችሁ ይኼው የሚሸጡበትን ቀን በተስፋ እየጠበቁ ናቸው፡፡ አይ አርሴና ማንቼ የማትሠሩን ነገር የለ፡፡
 ‹እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ› አሉ የዋሑ ቴዎድሮስ፤ እስኪ ቀና ብለው ይመልከቱ፤ ስንቱ እጁን ብቻ ሳይሆን ልቡንም እንደሰጠልዎ፡፡ እርስዎ ክንዴን ለጠላት አልሰጥም ብለው ነው ጥይት የጎረሱት፤ ልጆችዎኮ አርሴናል ተሸነፈ ብለው ነው ጥይት የሚጎርሱት፡፡ እርስዎ እንግሊዞችን ሰብስበው መድፍ ማሠራትዎን ትውልዱ ረስቶልዎ ዛሬ የመድፈኞቹ ነገር ሲያስጨንቀው ቢያዩ፣ ቴዎድሮስ ሆይ የጠጡትን ጥይት በኦፕሬሽን ያስወጡት ነበር፡፡ ዛሬ የርስዎ ሀገር ልጅ
‹ገደልንም እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው
ማረክንም እንዳይሉ ሰው የለ በጃቸው›
የሚለውን ቴዎድሮስ ይሙቱ ረስቶታል፡፡ እርስዎ እንግሊዞች ሲመጡ እንዴት እንደተቀበሏቸው አያውቅም፣ አያጠናምም፣ አይጨነቅምም፡፡ አሁን እርሱን እየጨነቀው ያለው፡፡ የዘንድሮን ዋንጫ የወሰደው ማንቼስተር ዩናይትድ የተባለው ቡድን እርስዎ መድፍ ያሠሯቸውን የዛሬዎቹን መድፈኞች ለመግጠም ኤምሬት ስታድዮም ሲገባ መድፈኞቹ ተሰልፈው እያጨበጨቡ ይቀበሏቸው ወይስ አይቀበሏቸው? የሚለው ነው፡፡ የለም ቴዲዬ እርስዎና ዐፄ ዮሐንስ ሳይሸወዱ አልቀሩም፡፡
እና ይህንን ሁሉ ሆነንላችሁ ደግሞ ስማችንን አታውቁትም አሉ፡፡ እኛን ካላወቃችሁ ታድያ ምንድን ነው የምታውቁት፡፡ ይኼው ሂሳብ በእናንተ ከመማር በላይ ምን እናድርግ እንግዲህ፡፡ ሜሲ ትናንት ሦስት ጎል አገባ፣ ዛሬ ደግሞ ሁለት ጎል አገባ፤ በጠቅላላው ስንት ጎል አገባ? ካልተባሉኮ ልጆቻችን ሊደምሩ አልቻሉም፡፡ ከአሥራ አንዱ የፉልሃም ተጨዋቾች ሁለቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጡ ስንት ተጨዋቾች ሜዳ ላይ ይቀራሉ፤ ካላልን ማን ይቀንስልናል፡፡ ሩኒ በሳምንት የሚያገኘው ገቢ 120 ሺ ፓውንድ ነው፡፡ በዓመት 52 ሳምንቶች አሉ፡፡ ሩኒ በዓመት ስንት ያገኛል? ካላልን ማን ያባዛልናል? እና ይህንን ሁሉ ሆነን አታውቁንም? እኛ ብቻ ነን የምናውቃችሁ? እንዲህ ጥናታችንን ትተን እናንተን እያጠናን፣ እንዲህ ከአድዋ ጦርነት ታሪክ ይልቅ የእናንተን የዌምብልደን ፍልሚያ ታሪክ እያጠናን፣ እንዲህ ከሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ይልቅ የእናንተን የገቢ ዕድገት እየተከታተልን፣ ከብር የመግዛት ዐቅም መዳከም ይልቅ የሜሲ የማግባት ዐቅም መዳከም እያሳሰበን፣ ከምግብ ዋጋ መጨመር ይልቅ የዳኝነት መዛባቱ መጨመር  እያስጨነቀን፤
ተው እንጂ አርሴና ማንቼ አስተያየት አድርጉ፤
እናንተ የመጀመርያውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ስትወስዱ ሥጋ እኛ ሀገር 20 ብር ነበር፤ ዛሬ ሃያኛ ዋንጫችሁን ስትወስዱ ግን ሥጋ 100 ብር ገብቷል፡፡ እና የናንተ ሃያኛ ድል በኑሯችን ላይ 500% ዋጋ ተጨምሮበት የምናከብረው መሆኑን እንኳን አታውቁልንም አይደል፡፡ እናንተ የማታውቁን እኛ የምናውቃችሁ፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፤ በሌላ ተመሳሳይ ሚዲያ መጠቀም አይፈቀድም