እውነትን ለመቅበር

እውነት እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ዘለዓለማዊ ነው፡፡ እውነትም ዘለዓለማዊት ናት፡፡ <የሰዎችን ልጆች ጥላዎች> ሲያስበረግጉ ከኖሩት ነገሮች አንዷ እውነት ናት፡፡ ‹የሰዎች ልጆች ጥላዎች› ያልኩት ሰው ከሚለው ስያሜ ለመለየት ነው፡፡ እነዚህ እውነትን የሚፈሯትና የሚጠሏት አካላት ሰዎች አይደሉም፡፡ ሰው እውነትን ይወዳል፣ በእውነትም ይኖራል፣ ለእውነትም ይሞታል፡፡ እርሱ በእውነት እጆች የተፈጠረ ነውና፡፡ ነገር ግን <የሰው ጥላዎች> አሉ፡፡ ሰዎች ያልሆኑ፤ ነገር ግን የሰው መልክ ያላቸው፣ ራስ ያላቸው ነገር ግን አእምሮ የሌላቸው፣ ሆድ ያላቸው፣ ነገር ግን ልቡና የሌላቸው፣ አፍ ያላቸው ነገር ግን አንደበት የሌላቸው፣ ጉሮሮ ያላቸው ነገር ግን አንገት የሌላቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች አይደሉም፡፡ እነዚህ ‹የሰው ጥላዎች› ናቸው፡፡ ጥላ እንደሚጠፋው እነርሱም ይጠፋሉ፤ ጥላን ብርሃን እንደሚያጠፋው እነርሱንም የእውነት ብርሃን ያጠፋቸዋል፡፡
በሰሞነ ሕማማት የተፈጸመው ድርጊት ይኼው ነበር፡፡ የሰው ጥላዎች እውነትን ለመግደል ያደረጉት ሙከራ፡፡ እነዚህ የሰው ጥላዎች ራሳቸውን እውነተኛ ከማድረግ ይልቅ አውነትን በመግደል ሐሰተኛነታቸውን መሸፈንና እንደማንነታቸው ሁሉ በእውነት ጥላ መኖር ነበር የፈለጉት፡፡ ክርስቶስ እውነት ነው፤ ያስተማረውም እውነት ነው፤ ለሐሰት አንድም ቦታ ሳይሰጥ የገለጠው እውነትን ነው፡፡ ይህ እውነት ግን መኖሪያቸውንና ማንነታቸውን ሐሰት ላደረጉት ‹የሰው ጥላዎች› አልተመቻቸውም፤ አመማቸው፤ በየጊዜው ራሳቸውን እንዲያዩና ራሳቸውን እንዲወቅሱ ስላደረጋቸው አመማቸው፤ የእውነት መኖር ሐሰትን ማንጸርያ ስለሚያመጣባት አመማቸው፤ ብቻቸውን ሆነው ያለምንም ማንጸሪያ ነን ያሉትን ሁሉ እየታመኑ እንዲኖሩ ነበር ሃሳባቸው፤ ነገር ግን እውነት መጣችና ከጎናቸው ስትቆም በቀላሉ ጥላው ከብርሃኑ ተለየ፡፡ ብርሃን ከሌለ ጨለማን፣ ቀን ከሌለ ሌሊትን፣ ሕይወት ከሌለ ሞትን፣ ክብር ከሌለ ውርደትን፣ ነጻነት ከሌለ ባርነትን በምን መለየት ይቻላል፡፡

 እነዚህ በሰሞነ ሕማማት እውነትን ለመግደል የተነሡት የሰው ጥላዎች ሦስት ነገሮችን ነበር የተጠቀሙት፡- ሥልጣን፣ ገንዘብና ያልተማሩ ሰዎችን፡፡ ይህ ደግሞ በእነርሱ የተጀመረ ወይም በእነርሱ ያቆመ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ እውነትን እንገድላለን ብለው የተነሡ አካላት ሁሉ የሚጠቀሙት እነዚህን ሦስቱን ነው፡፡ ከሐዋርያት መካከል ይሁዳን በገንዘብ ገዙ፡፡ ምስክሮችንም ገንዘብ እየከፈሉ አዘጋጁ፡፡ በሥልጣናቸው ራሳቸው ከሳሽ ራሳቸው ዳኛ ራሳቸውም አስፈጻሚ ሆኑ፡፡ ጲላጦስ እንኳን እውነቱን ተረድቶ ‹የለም፣ ክርስቶስ ምንም ነገር አላደረገም› እያለ ሲሞግታቸው እነርሱ ግን ያልተማሩትንና ከችግራቸው በቀር ሌላ ነገር የማይረዱትን ሰዎች ሰብስበው በጲላጦስ ላይ ተነሡበት፣ በሥልጣኑም አስፈራሩት፡፡
በዓለም ላይ ሥልጣን፣ ገንዘብና ያልተረዱ ሰዎች ሲገጥሙ እውነት ፈተና ውስጥ ትወድቃለች፡፡ ሥልጣንን እውነት ካልገራቺው የማጥፊያ መሣርያ ይሆናል፣ ገንዘብንም እውነት ካልገራቺው የመግደያ መርዝ ይሆናል፣ ማኅበረሰብም እውነትን ለመረዳት የሚያስችል ዐቅም ከሌለው የጥፋት ተባባሪ ማድረግ ቀላል ነው፡፡ ለእነዚህ ለሦስቱም እውነት ወሳኝ ናት፡፡ ብዙ ጊዜ ግን እነዚህ ሦስቱ እውነትን አይፈልጓትም፡፡ እውነት ካለች ገደብ አለና፡፡ ባለ ሥልጣናት በሥልጣናቸው ላይ ገደብን አይፈልጉም፣ ባለ ገንዘቦችም በገንዘባቸው ላይ ልክና መጠን እንዲደረግበት አይሹም፣ አንዳንድ ማኅበረሰብም ለዕውቀት የሚከፈለውን መሥዋዕትነት አይሻውም፡፡ ስለዚህም እውነትን እንደ ጠላት ያዩዋታል፡፡
ዓርብ ዕለት እውነት ለፍርድ ቀረበች፡፡ በታሪክ ብዙ ጊዜ እንደታየው እውነት ስለ ራሷ ትመሰክራለች እንጂ ከእውነት ጋር የሚቆም አካል የሚገኘው በጭንቅ ነው፡፡ ከእውነት ጋር መገኘት ዋጋ ያስከፍላልና፡፡ ክርስቶስ በዕለተ ሆሳዕና በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ተቀምጦ ሲመጣ ‹ሆሳዕና› እያሉ የኢየሩሳሌምና የአካባቢዋ ሕዝብ በሆታ ተቀብለውት ነበር፡፡ ሆሳዕና ማለትም ‹አሁኑኑ አድን› ማለት ነው፡፡ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አበርክቶ ሲያበላቸው ‹አሁኑኑ ንገሥ› ብለው አስጨንቀውት ነበር፡፡ አሁን ጊዜ ፊቷን ስታዞርና እውነት ስትከሰስ ግን እነዚያው ሰዎች ካልተሰቀለ ሞተን እንገኛለን አሉ፡፡
እውነት በተከታዮቿ ብዛት አትመዘንም፣ በደጋፊዎቿ ብዛትም አትለካም፤ እውነት ደጋፊም ብታገኝ ባታገኝ፣ ተከታይም ብታፈራ ባታፈራ፣ ምንጊዜም ብቻዋን ናት፡፡ እውነት የምትቆመው እውነት ስለሆነች እንጂ ሌላ የሚያቆማት ኃይል ስላለ አይደለም፡፡ እውነት ራሷ ኃይል ናትና በራሷ ትቆማለች፡፡ ለዚህ ነው ሐሰተኞች ራሳቸውን የሚያስመኩት በደጋፊዎቻቸው፣ በአባሎቻቸው፣ በቲፎዞዎቻቸውና በተከታዮች ብዛት የሚሆነው፡፡ ሐሰት ያለ ቲፊዞና ድጋፍ ብቻዋን አትቆምምና፡፡ ሐሰት እንደ ሐረግ መደገፊያ ትፈልጋለች፡፡ ሐሰት ዐቅም ስለሌላት የገንዘብንና የሥልጣንን ዐቅም መጠቀም ትፈልጋለች፡፡
አንዳንድ ሰዎች እውነትን የሚከተሏት ሐሰት መስላቸው ነው፡፡ አንዳንዶች በእውነትና በሐሰት መካከል ያለውን ልዩነት አይለዩትምና፡፡ ያንን የመለየት ዕድል የሚያገኙት እውነት መሥዋዕትነት ማስከፈል ስትጀምር ነው፡፡ ያን ጊዜ ከእውነት መሸሽ ይጀምራሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እውነት እንደ ሐሰት ጥቅም ብቻ የምትሰጥ መስላቸው ይከተሏታል፡፡ መሥዋዕትነቱ ሲመጣ ግን ይሸሻሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እውነትን ለመሸከም የሚያስችል ዐቅም ሳይኖራቸው ከእውነት ጋር ይቆማሉ፡፡ ዐቅም የሚያስፈልግበት ጊዜ ሲመጣ ግን ጥለው ይሸሻሉ፡፡
የክርስቶስ ተከታዮች በአራት የተከፈሉት በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ አምስት ገበያ ሞልተው ሲከተሉት የነበሩት ብዙዎች እውነትና ሐሰትን መለየት አልቻሉም ነበርና ሲከተሉ ኖሩ፡፡ በዕለተ ዓርብ እውነት ከሐሰት መለየት ስትጀምር ግን ጓዛቸውን ጠቅልለው ከሐሰት ጎራ ተቀላቀሉ፡፡ እንደ ይሁዳ ያሉት ደግሞ እውነትን ለጥቅም እንጂ ለእውነትነቷ አልተከተሏትም ነበር፡፡ በሂደት ግን ይሁዳ ከእውነት ያሰበውን ምድራዊ ጥቅም አላገኘም፤ ስለዚህም በጊዜ ወደምትሻለውና ወደምትስማማው ሐሰት ኮበለለ፡፡ የፈለገውንም ጥቅም አገኘ፡፡ ሌሎቹ ሐዋርያት ደግሞ እውነትን ለመሸከም የሚያስችል ዐቅም አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህም ፈታኟ ሰዓት ሰትመጣና የመሥዋዕትነቱ ጊዜ ሲቀርብ መምህራቸውን ጥለው ተበተኑ፡፡ ዮሐንስ ግን የእውነትን መሥዋዕትነት ተረድቶ ነበረ፡፡ መከራውንም ችሎ እስከ እግረ መስቀል ደረሰ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ከዮሐንስ የለየው እውነትን ለመሸከም የሚያስችል ዐቅም ማጣት ነው፡፡
እውነትን የሚያስችል ዐቅም ማለት የዮሐንስ ዐቅም ማለት ነው፡፡ ያንን ራቁቱን የተሰቀለውን፣ ሞት የተፈረደበትን፣ አላፊ አግዳሚው የሚተፋበትን፣ በጎኑ የተሰቀሉ ሽፍቶች እንኳን የሚቀልዱበትን፣ ደቀ መዛሙርቱ ጥለውት የሄዱትን ጌታ ‹እከተለዋለሁ፣ ከእርሱ ጋር ነኝ› ብሎ መቆም ውሳጣዊ ዐቅምን ይጠይቃል፡፡ አሁን በመስቀል ላይ የሚታየው ጌታ በዚያ ሰዓት እንጀራ እያበረከተ፣ ዓይነ ሥውር እያበራ፣ ሽባ እየተረተረ፣ ተአምራትና ድንቆች እያደረገ አይደለም፡፡ ተላልፎ ተሰጥቶ ምስኪን በመሰለበት ጊዜ ነው ዮሐንስ አብሮ የቆመው፡፡ በዚህ ጊዜ አንዳች ክብርም ሆነ ጥቅም የለም፣ ስድብና ግልምጫ እንጂ፤ በዚህ ጊዜ አንዳች ሥልጣንና ዝና የለም ተዋርዶና ንቀት እንጂ፡፡ ይህንን ሁሉ ለመቻል ነው ከእውነት ጋር የመቆም ዐቅም የሚያስፈልገው፡፡
የሰው ልጅ እውነትን ለመግደል እንዲጥር የሚያበረታቱት ሁለት የማሳሳቻ ወቅቶች ናቸው፡፡
በእውነት ሂደት ውስጥ ካሉት ሦስት ወቅቶች መካከል ሁለቱ ወቅቶች አሳሳች ወቅቶች ናቸው፡፡ ሦስቱ ወቅቶች የሁካታ ወቅት፣ የዝምታ ወቅትና የትንሣኤ ወቅት ናቸው፡፡ ‹የሁካታ ወቅት› ሥልጣን፣ ገንዘብና ያልተረዳ ማኅበረሰብ አንድ የሚሆኑበት፣ ፍትሕ ተደፍጥጣ ፍርደ ገምድልነት የሚነግሥበት፣ ለምን? እንዴት? የሚል ጥያቄ ቀርቶ፣ ይውደምና ይቅደም፣ ይጥፋና ይሙት፣ ‹ውረድ በለው ግፋ በለው› ቦታውን የሚይዙበት፤ ወቅት ነው፡፡ ያኔ ማንም ሊቅ፣ ማንም ሽማግሌ፣ ማንም የእምነት ሰው ‹ተዉ› ቢል የሚሰማው የለም፡፡ ሁሉም እንደ አህያ ጆሮ እንደ ጦር ጉሮሮ አንድ ሆኖ ‹ስቅሎ ስቅሎ› እያለ የሚጮኽበት ጊዜ ነው፡፡
ይህ ወቅት ሥልጣን ያላቸው፣ ገንዘብን የያዙና ያልተረዳን ማኅበረሰብ መቀስቀስ የቻሉ ሰዎች እውነትን መግደል የቻሉ የሚመስላቸው ጊዜ ነው፡፡ እውነት አብሯት የሚቆም የምታጣበትና ራቁቷን በገዥዎች ፊት የምትቀርብበት ጊዜ ነው፡፡ እንደሚሸለት በግ በሸላቾቿ ፊት ዝም የምትልበት ጊዜ ነው፡፡ ጌታም የተገረፈው፣ የተሰቀለውና የሞትን ጽዋ የቀመሰው በዚህ የሁካታ ወቅት ነው፡፡ ለቀያፋና ለሐና፣ ለአይሁድና ለሮማውያን እውነትን ገደልን ብለው ደስ አላቸው፡፡ የጨረሱም መሰላቸው፡፡ ይህ ጊዜ ኀሙስ ሌሊት ተጀምሮ ዓርብ አሥራ አንድ ሰዓት የተፈጸመ ነው፡፡ ይህ ወቅት ሲያልቅ ሁለተኛው ወቅት ይጀምራል፡፡ ይህም የዝምታው ወቅት ነው፡፡ የዝምታው ወቅት እውነት ድምጽዋን የምታጠፋበት፣ በመቃብር ውስጥ የምትውልበት፣ የእርሷ ታሪክ የሞት ታሪክ ነው ተብሎ የሚወራበት ረዥሙ ጊዜ ነው፡፡ ዓርብ አሥራ አንድ ሰዓት ተጀምሮ ቅዳሜ ለእሑድ እኩለ ሌሊት ድረስ የሚደርስ ነው፡፡ ሐዋርያት በዚህ ጊዜ ተስፋ ቆርጠው ነበር፡፡ በኤማሁስ መንገደኞች ላይ እንደታየውም አንዳንዶቹ ነገሩን ወደ ትዝታ ቀይረውት ነበር፡፡ ሌሎቹም ክስተት አድርገው ቆጥረውትም ነበር፡፡ ሥልጣን፣ ገንዘብና ያልተረዳ ማኅበረሰብን የያዙት አካላትም በመቃብሩ ላይ ድንጋይ ገጥመው በወታደር ማስጠበቅ ጀምረው ነበር፡፡
ይህ ወቅት ነው አንዱ የማሳሳቻ ወቅት፡፡ ይህ ወቅት ባለጊዜዎቹን፣ ለእውነት ለማድላት የሞከሩትንና ከሐሰት ጋር የቆሙትን አካላት ያሳስታል፡፡ ባለጊዜዎቹ ሁሉንም ነገር በገንዘብና በሥልጣን እንጨርሰዋለን እንዲሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ለእውነት የሚያደሉትም ከእውነት ጋር መቆም ጥቅም የለውም፤ እውነት አታዋጣም እንዲሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ከሐሰት ጋር የቆሙትንም መንገዳቸው ትክክል ለመሆኑ ማረጋገጫ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ይህ ሁሉ ግን እስከ እኩለ ሌሊት ብቻ ነው፡፡ በርግጥ ከወቅቶቹ ሁሉ ረዥሙ ጊዜ ይህ ነው፡፡ እውነት ተዳፍና ለረዥም ጊዜ የምትቆይበት አሳሳች ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት ፍርሃት የሚወድቅበት የድንጋጤ ወቅት ነው፤ ይህ ወቅት አንዳንዶችም ተስፋ የሚቆርጡበት ወቅት ነው፡፡
በዚህ መጨረሻ ነው ሦስተኛዋ ወቅት የምትመጣው፡፡ የትንሣኤ ጊዜ፡፡ ቅዳሜ ለእሑድ እኩለ ሌሊት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል፣ ጠባቂዎቹ እንኳን ሳያዩት ክርስቶስ ተነሣ፡፡ ገንዘብና ሥልጣን፣ ያልተረዳም ማኅበረሰብ አንድ ላይ ሆነው እውነትን ሊገድሉ፣ እውነትንም ሊቀብሩ አለመቻላቸውን የሚረዱበት፤ አሸናፊዎቹ የሚሸነፉበት ጊዜ ደረሰ፡፡ እውነት ከመቃብር በላይ፣ ሐሰትም ከውርደት በታች ሆነች፡፡ የሥልጣን ጡጫ፣የወታደር ኃይል፣ የገንዘብ ዐቅም፣ የብዙዎች ጩኸት፣ እውነትን ገድሎ ሊቀብራት፣ ቀብሮም ሊያስቀራት እንደማይችል ታወቀ፡፡
ከእውነት ጋር ሲጣሉ ለሚኖሩ ሁሉም ትምህርት ይሆን ዘንድ፤ በዐርባኛው ቀን ሁሉም እያያት እውነት ዐረገች፡፡ በልዕልናም ተቀመጠች፡፡  ከእውነት የተጣሉ የሰው ጥላዎች ግን ከመቃብር በታች እነሆ አሉ፡፡ 

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፤ በሌላ ተመሳሳይ ሚዲያ መጠቀም ክልክል ነው
ለተወደዳችሁ አንባብያን

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ምእመናንን በማስጎብኘትና በማስተማር ላይ ስለነበርኩ የየዕለቱም መርሐ ግብር የሚያልቀው አምሽቶ ስለነበር ጽሑፎቹን ማዘጋጀትና ማተም አልቻልኩም ነበር፡፡ አሁን ተመልሻለሁ፡፡ እንደ ቀድሟችንም እንቀጥላለን፡፡ ብዙዎች አስባችሁ ጽፋችሁልኛል፡፡ ፈጣሪ ያስባችሁ፡፡