አንዳርጋቸው ፅጌ ዘፈን ጋብዞን ሄደ !

ከአንበሳው ይብራ

መስከርም 22 ቀን 2013 እ.ኤ.አ ቀመር በእለተ ሰንበት ግንቦት ሰባት በአርሊንግቶን ቨርጂኒያ ፤ ህዝባዊ ስብሰባ ጠራ ። በስብሰባው መክፈቻ ላይ የዋሽንግተኑ ቻፕተር ተወካይ አንድ ቃል ገባ ። እንዲህም አለ ። “በመካከላችን የግንቦት 7 መሪዎቻችን ተገኝተዋል ። ግንቦት ሰባትን በተመለከተና ወቅታዊ የሃገራችንን ጉዳዮች አስመልክተው ከናንተ ጋራ ውይይት ያደርጋሉ ። ከዚህ ውይይት ጠቃሚ መረጃ እንደምታገኙ ተስፋዪ ከፍ ያለ ነው ፡ በተጨማሪም ለሚኖሯችሁ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ እንደምታገኙ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ” ። በጣም ጥሩ ነው አልን ።

ጥያቄዎቻችንን ከማቅረባችን በፊት ግን ፤ ንግግራቸውን እንስማ ብለን ፤ በተለይ አንዳርጋቸው በኢሳት ቴሌቪዥን የሰጣቸውን መግለጫዎች ያብራራል ብለን ጠበቅን ። አንዳርጋቸው ያደረጋትን አጨር ማብራሪያ ሲጀምር ፡ “የእውነቶች ሁሉ እውነት ከወያኔ በላይ የኢትዮጵያ የሃገሯ የደህንነቷና ጥቅሟ ጠላት ከወያኔ በላይ የለም ብየ ነው የምነሳው” ካለ በኋላ አንዲት ነገር ሳይቀንስ ያንኑ የሻእቢያ ጥብቅናውን ነግሮን ነው የሄደው ፤ እንዲያውም አለ አንዳርጋቸው ስለዚያች ሃገር (ኤርትራ) ብዙ ያልነገርኳችሁ ነገር አለ አለን ። ከወደ አስመራ የተሰማውም ዜና የሚያመላክተው ግን አንዳርጋቸው የሰጠው ማብራሪያ እንዳልተወደደለት ነው ። በሻእቢያዎቹ ሞገስ አገኛለሁ ብሎ ያሰበው አንዳርጋቸው አስመራ ሲገባ ፤ በሻእቢያ ስልታዊ ትምህርት ይጠብቀዋል ። የሱ ያልሆኑ ነገሮችን ሁሉ ነካክቷልና ።

ውድ አንባቢዎቼ ታስታውሱ እንደሆን ሃይለማርያም ደሳለኝ ለአልጀዚራዋ ጋዜጠኛ በዲሴምበር 2012 በሰጡት ቃለ-ምልልስ ላይ እንዲህ ብለው ነበር ። “If you ask me, ‘Do you want to go to Asmara and sit down and negotiate with Isaias Afwerki?’ Then, I will say yes’. አስመራ ሄደህ ከኢሳኢያስ አፈወርቂ ጋር ተቀምጠህ ትደራደራለህ ወይ ብለሽ ብትጠይቂኝ አዎን ነው የምልሽ ፤ ብለው ነበር ። እና ኃይለማርያም ደሳለኝ ይህን ጥያቄ ራሳቸው ጠይቀው ራሳቸው ሲመልሱ በአሳዳሪዎቻቸው ወያኔዎች ሞገስ አገኛለሁ ብለው አስበው ነበር ። እሳቸው የፈለጉት የወያኔን ሰላም ፈላጊነት በተሻለ መንገድ ለማሳየትም ነበር ። ሃሳባቸው ግን የፈለጉትን ግብ ሳይመታ ቀርቶ እንዲያውም ፤ የተሰጣቸውን መስመር በማለፋቸው “ማን ይህን በል አለህ” በሚል በወያኔ ከፍተኛ ተግሳፅ እንደደረሰባቸው ሁላችንም የሰማነው ነው ። ምን ጭራህን ትቆላለህ ይለዋል ይህን አይነቱን ሰው ያገሬ ሰው ። ሃይለማርያም ወያኔ ፊት ጭራ እንደቆሉ ሁሉ አንዳርጋቸውም ሻእቢያ ፊት ጭራውን ቆልቷል ። እንደሰማነው አስመራዎቹ አንዳርጋቸው የማይመለከተውን ሁሉ ዘባርቋል ብለው አስበዋል ።

ሻእቢያዎች እንዲህ አይነት ነገር ሲያጋጥማቸው ለምን እንዲህ አልክ ለምን እንዲህ አደረክ ብለው አይጠይቁም ፤ ለተናጋሪው ግን የአሰራር ገደብ ያደርጉለታል ። ከዚህ በፊት ይሰጡት የነበረውን ፊት ቀስ በቀስ ይነፍጉታል ። በሚሄድበት ቦታ ሁሉ የሚያገኛቸውን አገልግሎቶች ሁሉ ይቀንሱበታል ። ክፍት የነበሩት በሮች ሁሉ ገርበብ ይደረጋሉ ፤ በኋላም ላይ ከናካቴው ይዘጋሉ ። ዛሬ አስመራ አንዳርጋቸው የሚጠብቀው ይህ ነው ።

የአርሊንግቶኑ ስብሰባ ላይ ብርሃኑ ነጋም ሆነ አንዳርጋቸው መሬት ላይ ጠብ የማይል ወሬ ነው የነገሩን ። “ወሬ በዝቷል ፤ ሁሉም እኮ እኩል የሆነው ለዚህ ነው” ሲሉ ተናገረ ብርሃኑ ። ምን ማለት ይሆን ይህ አባባል ? እኔ አልገባኝም ። እኩል አይደለንም እንዴ ? በምን ይሆን የምንበላለጠው ? “በስራ የሚታየውን እናሳይና then we will talk” ትክክል ብለሃል ብርሃኑ ግን እኮ በዚህ አምስት አመት ውስጥ እኛ አልነበርንም በነጋ በጠባ ኢሳት ወይ ፓልቶክ ላይ እየወጣን ወሬ ያበዛነው ። እናንተ ናችሁ ። ከወሬ ውጪ ምን አሳያችሁን ። ወያኔ እንኳ የአባይን ግድብ 20% የሚሆነውን ሰርቻለሁ ብሎናል ። እናንተ ከያዛችሁት ፕላን ምን ያህሉን ሰራችሁ ። ፕላንስ ነበራችሁ ወይ ? ወይስ ዝም ብሎ በደመ-ነፍስ ነው ስራችሁ ሁሉ ። አንዳርጋቸውስ ምንድነው ያለው በዚህ ስብሰባ “እዛ አካባቢ ያለውን ሰራዊት ለማንም ፓርቲ አሽከር እንዳይሆን ፤ ትምህርቱ ይሄ ነው ስልጠናው ይሄ ነው” ። “ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” እንደሚባለው ፤ መጀመሪያ ሰራዊት ይኑራችሁና አሽከር ስለመሆንና አለመሆን በኋላ እንነጋገራለን ። ዛሬ ህዝባችን ውጤት ይጠብቃል ። ከእንግዲህ ውጤት ካላየ አምስት ሳንቲም ጠብ እንደማይለው በአርሊንግቶኑ ስብሰባ ላይ ህዝቡ አስይቷችኋል ። እና የምንመክረው ዘፈናችሁን ቀይሩ ነው ። “በፋሲካ ይተገዛች ባሪያ ሁሌ ፋሲካ ይመስላታል” እንዲሉ ፡ ሁሌ በኢሳት ወይም በፓልቶክ ብቅ እያላችሁ ፤ ወይም አዳራሽ ውስጥ እየሰበሰባችሁን ስለምታወሩ የምትሉትን ሁሉ የምናምን መስሏችኋል ። አሁንም እየነገራችሁን ያለው ትምህርት እየሰጣችሁ እንደሆነ ነው ። አንድ ጠብታ ተግባር ማየት እንፈልጋለን ።

አርሊግቶን የተጠራው ስብሰባ አቢይ አላማ አንዳርጋቸው በኢሳት ለሰጠው ቃለ-መጠይቅ ማብራሪያ በማስፈለጉ ነበር ፤ የሆነው ግን ይህ አይደለም ። ክህዝብ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ስላስፈራችሁ በእቅድ አንዳርጋቸው ወደአስመራ በሚበርበት እለት ስብሰባ አዘጋጃችሁ ፤ ወይም በረራ አለበት ብላችሁ ከአዳራሹ የእጅ ሻንጣ ይዞ እንዲወጣ አደረጋችሁ ። ስብሰባው ቅዳሜ ሊዘጋጅ አይችልም ነበር ?

ጥያቄ ለማቅረብ እድል ከተሰጣቸው ሰዎች አንዱ ስለማያገባችሁ ስለነኢሳኢያስ አታውሩ ብሎ ማሳሰቢያ ሰጠ ። ሌላው ጠያቂ እያሾፈና እየሳቀ “አቶ አንዳርጋቸው የጦር ሰው ስለሆኑ እንግዲህ ” ብሎ ሲናገር ከአዳራሹ የተሰማው ሳቅ የሚያመላክተው ነገር ነበረው ለሚገባው ሰው ፤ እስቲ እናሹፍ ( አሁን አየር ሃይል አላችሁ አይደል?) ።

አንዳርጋቸው በኢሳት ላቀረበው የሻእቢያና የኢሳኢያስ ፍቅር ማብራሪያ በመስጠጥና የተናገርኩት ትክክል አልነበረም ብሎ ለህዝብ በማስረዳት ፈንታ ፤ በአዳራሹ የተሰበሰበውን ሰው በነበረከት ስምኦን ውስኪና በአላሙዲን ኬክ አቅርቦት ማዝናናት ነው የመረጥከው ። አላሙዲን ለነበረከት ከእንግሊዝ አገር ኬክ አሰርቶ ቢያመጣላቸው እንኳ እኛ ምን አገባን ።

አቶ አንዳርጋቸው ፤ ስለተገረፉት ሰዎች ማለትም ስለሰብአዊ መብት መረገጥ ፤ ስለወያኔ ፍርድ ቤቶች ፍትህ መጓደል ፤ ስለወያኔ ሚዲያዎች ነፃ አለመሆን ፤ ስለዲሞክራሲ እና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች አንዳንድ ቦታ እስከ10ሺህ አንዳንዴም 4ሺህ ሰዎችን አስትምር ነበር ወያኔዎቹ ጋር እያለሁ ብለኽናል ። ጥሩ የማስተማር ችሎታ የለህም እንዴ ? ወያኔዎቹ ትምህርትህ ካልገባቸው ፤ የተቀዱበት ወንዛቸው አንድ ነውና ፤ ድምህቶችም አይገባቸውም ብትተወው ይሻልሃል ።

ስለዚህ ስብሰባ ኢሳት ያቀረበው ልዩ ዝግጅት 57ኛዋ ደቂቃ ላይ መመልከት ይቻላል ፤ በቅርቡ ኢሳኢያስ ስለተናገርው ያልካትና ብዙው ሰው ያስተዋለው አንድ ነገር ነበር ፤ አሁንም ለዚህ ስብሰባ ተብሎ የተለቀቀ ነገር የማቀው ነገር የለኝም ብሎት እንደሆነ አላለውም አላውቀም ስለ ኢሳኢያስ የተነሳ ጉዳይ አለ ፤ ብለኽናል ። ቦታና ጊዜ ተጠቅሶ የቀረበንና ኢትዮጵያ ከሁለተኛ የአለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረች አገር ናት ሲል ለኤርትራ ጋዜጠኞች የሰጠውን ቃለ ምልልስ አላምንም እያልከን እኮ ነው ። ሄደህ ከኢሳኢያስ እስክትጣራ እንጠብቅሃለን ። ለነገሩ ኢሳትም እኮ ኢሳኢያስ ስለተናገረው አንድ ነገር ትንፍሽ አላለም ።

ለዚሁ ስብሰባ ሲባል በግንቦት7 ምንጭነትና በኢሳት አጋፋሪነት የቀረበውን 4 ፓይለቶች የግንቦት 7ን ህዝባዊ ሃይል ተቀላቀሉ ዜናስ እንዴት ልታስረዳን ትችላለህ ? ለዚህ ስብሰባ የተለቀቀ ዜና አይደለምን? ! ፓይለቶቹ መቼ ወደኤርትራ እንደገቡና ከየት አገርስ እንደመጡ ቀኑና ጊዜው አልተገለፅም ። 2ቱን ከቻይና የመጡ መሆናቸውን ስትገልፅ ሌሎቹ 2ቱ ከይት እንደመጡ አልነገርከንም በቀጥታ ከኢትዮጵያ ወይስ ከኬንያ ና ከደቡብ አፍሪቃ ስደተኛ ካምፖች ።

አንዳርጋቸው ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና እናትህም አንተም ስለተወለዳችሁባት ስለመዲናችን አዲስ አበባ ያለህን ፍቅር ፤ ብሎም ስለነበርክበት የተማሪ ትግል ስህተቶች በድፍረት በመናገርህ ሳላደንቅ ያለፍኩ እንዳይመስልህ። ይህን ንግግርህን ብርሃኑ ነጋ ለታክቲክ የምንጠቀምባቸው ነገሮች አሉን ከሚላቸው ውስጥ ነው ብየ ለማመን አልፈልግም ከልብ የተናገርከው ነው ብየ እገምታለሁ ። ስለብርሃኑ ከተነሳ ደግሞ አንድ ነገር ልበል በዚሁ ስብሰባ ላይ ከተናገረው።

ብርሃኑ የግንቦት 7 መሰረታዊ እምነቶች ብለህ 3 አበይት ጉዳዮችን እንዲህ ስትል አቀረብክ ። ኢትዮጵያ ውስጥ መሰራታዊ የሆኑ የዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት ሃገር እንድትሆን ፤ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገነባ ፤ ኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ መሆኗና አንድ አገር መሆኗን መቀበል ነው ፤ አልከን ። ብርሃኑ ዛሬ በምትኖርባት አሜሪካ የዲሞክራሲ ስርአቱ ጀማሪዎች “The founding fathers” በተግባር ዲሞክራሲን ስለተጠቀሙበት ነው ዛሬ አሜሪካ እዚህ የደረሰችው ። ብርሃኑ በአምስተርዳም የኢሳት ቢሮ የፈፀምከው ተግባርና ትጠቀምባቸው የነበሩ ስድቦች እንዲሁም ተፈጥሮ በነበረው ጉዳይ የአውሮፓው አጣሪ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርት እንዴት እንደገለበጥከው ልናቀርብ እንችላለን ፤ ይህ ታዲያ ዲሞክራሲያዊ ነበር ? በሾለከው የድምፅህ ቅጂ ላይ ድርጅቶች አንዴ ይከስማሉ ሌላ ጊዜ ይፈነዳሉ ስትል የተናገርከው፤ በራሱ ዲሞክራሲያዊነት አይደለምና ታዳሚው ሊሰማ የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን ፤ ዲሞክራሲን ልምድህ ብታደርገው ለራስህም ይጠቅምሃል ። ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ጋር መስራትም ተገቢ ነው ብለን እናምናለንም ብለኻል ፤ ያው የድምፅህ ቅጂ እንዳስተማረን የአብሮ መስራት ባህርይም የለህም ።

ብርሃኑ በተጨማሪ ከዚህ ቀደሞቹ የፓለቲካ ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ ግንቦት7 ለሂደት ትኩረት ይሰጣል ብለኻል ። ከዚህ ቀደም እኮ የኤርትራን አካሄድ ወይም ሂደት ገብተው ሞክረውት እንደማያዋጣ መዝነውና ተመልክተው ትተው የወጡና አሁንም እዚያው ተዘፍቀው የቀሩ ድርጅቶች አሉ ። የናንተ ሂደት ምን አዲስ ነገር ቢኖረው ነው? በአንድ ሰው እድሜ 5 አመታት ቀላል አይደለም ። ሂደታችሁ እኮ የትም ፈቅ አላለም።

በአጠቃላይ በዚህ ስብሰባ መድረክ ላይ የነገራችሁንን ነገር እኮ ሸራተን ድረስ ሳታለፉን $20 ዶላርም መግቢያ ሳታስከፍሉን ፤ በተለመደው አይንና ጆሮችሁ በኢሳት ለትነግሩን ትችሉ ነበር ።

አንዳርጋቸው ስለትግራይ ድምህት ወጣቶች የሙዚቃ ባንድ የኢትዮጵያን ባንዲራ መልበስ ነገርከን ። ሽእቢያ ልበሱ ካላቸው ነገ ደግሞ የኤርትራን ባንዲራ ይለብሳሉ ። አንድ የሙዚቃ ባንድ የመድረክ ልብሴ ነው ያለውን ዩኒፎርም በፈለገው አይነት ይለብሳል ፤ ያን ለበሰ ማለት ደሞ ሆነ ማለት አይደለም ። የመለስ ዜናዊ አስከሬን የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሶ አልነበረም እንዴ ። በእግዚአብሄር እምነት የሌለው እቴይስቱ መለስ ፀሎተ-ፍትሃት ተደርጎለት የለም እንዴ አስከሬኑ ሲሸኝስ በኦርቶዶክስ ካህናት ታጅቦ አልነበረም እንዴ ? ምን ይደንቃል ! አገራችን እንደሆነ በዚህም በለው በዛ ትያትር ቤት ሆናለች ። ይልቅ ስለ ድምህቶች መልእክት እንነጋገር ።

እኛም ድ.ም.ህ.ቶች ይህ መልእክት ይድረሳችሁ እንላለን !

እንደሚታወቀው የትግራይ ህዝብ በደርግ ስርአት ይደርስበት ከነበረው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ አፈና ለመላቀቅ የ17 አመታት የትጥቅ ትግል አድርጎ ፤ ብሎ ሲጀምር መልእክታችሁ ፤ ወያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ሲገባ የተናገረውን አዋጆች አይነት ስሜት ይፈጥራል ። በደርግ ስርአት አፈና የደረሰው ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሁሉ እንጂ በትግራይ ህዝብ ላይ ብቻ አልነበረም ። በመቀጠልም ከ65 ሺህ በላይ ግጀግኖች ልጆቹ ሲሰው በአሰር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ አካለ ጎዶሎ ሆነዋል ፤ ይላል መልእክታችሁ ። መቼም በሞተና በተጎዳ ላይ ወቀሳ ማቅረብ በባህላችን ተገቢ ባይሆንም እናንተ ስላነሳችሁት ነው መልስ እንድንሰጥ የተገደድነው ። የአንድ ህዝብ መስዋእትነት የሚለካው በውጤቱ ነው ። በኛ በኩል እነዚህ ሰዎች ኤርትራን ከእናት ሃገሯ ለማስገንጠል ሲሉ የተዋደቁ ናቸው እንላለን ። የነዚህ ሰዎች ሞትና ጉዳት ለኢትዮጵያ ምን አተረፈላት ብሎ ራስን መጠየቅ የተገባ ነው ። በነዚህ ሰዎች ደምና አጥንት ኢትዮጵያ የባህር በሮቿን አጥታለች ፤ ህዝቧ በዘር ፤ በሃይማኖት ፤ በጎሳ ፤ በቋንቋ ተከፋፍሏል ፡ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ እናንተ ራሳችሁ እንኳ የተደራጃችሁት በዘር መሆኑ በቂ ምስክር ነው ። የነዚህ ሰዎች ሞትና ጉዳት በሙዚቃችሁ ፊልም ላይ እንደሚታየው ህዝባችንን ለአረብ አገር ባርነት ዳርጓል ። የነዚህ ሰዎች ሞትና ጉዳት የስንቱን ኢትዮጵያዊ ቤትና ኑሮ ፈትቷል መሰላችሁ ፤ ለኢትቶጵያ አንድነት የተዋደቀው ሰራዊት ከነቤተ-ስቡ ተበትኗል ። በአገራችን ኢትዮጵያ ሽርሙጥና ተስፋፍቷል ፡ ህዝባችን በቀሳፊ በሽታዎች እየማቀቀ ይገኛል ፤ የትግራይ ህዝብ ከፈለው የሚባለው መስዋእትነት ውጤት ይህ ነው ። አንድ እንሁን የሚለውን ጥሪያችሁን በመላው አለም ላለነው ኢትዮጵያውያን አስተላልፋችሁልናል ። አንድ እንዳንሆን ሌት ተቀን የሚደክመው ሻእቢያ ጉያ ተቀምጣችሁ አንድነት ይመጣል የሚል እምነት የለንም ። እግዚአብሄር ካላችሁበት እስር ቤት ያወጣችሁ ዘንድ ፀሎታችን ነው።

ይህን መልእክት አድርሱልን ብለዋል ብሎ አንዳርጋቸው ስለነገረን ፤ ለመልእክታችሁ መልስ ለመጠት ብለን ነው ።

ወድ አንባቢዪ ሆይ ! በአጠቃላይ በዚህ በሴፕቴምበር 22/2013 በአርሊንግቶን ቨርጂኒያ ሸራተን ሆቴል የተደረገው ስብሰባ በአብዛኛው የኢሳት የአንዳርጋቸውን ቃለ-መጠይቅ እንደገና ፎርሙን ቀየር አድርጎ ነው የቀረበው ። አንዳርጋቸውም ሆነ ብርሃኑ በስብሰባው ንግግራቸው ላይ ባጠቃላይ በወያኔ የወደፊት ውድቀት ላይ እየፎከሩ የማይጨበጥ ተስፋ ብቻ ነው የሰጡን ። ሁሌ ካፋቸው የማይለየው የህዝባችን ብሶትንም ሲያኝኩት ውለዋል ። እኛ የምንጠብቀው ተግባር እናንተ የምታወሩልን ቀቢፀ-ተስፋንና ብሶት ብቻ ። ይህ ስብሰባ ትንሽ ትያትር ቢጤ የተሰራበትም ነበር ። አንዳርጋቸው እዚህ ስብሰባ ላይ ሰራዊታችን ሻንጣውን ይዞ ገባ ? መኪና ውስጥ መተው አለዚያም የሆቴሉ receptionist ቶችጋ ማስቀመጥ ይችል ነበር ። ከስብሰባው አዳራሽ ሲወጣ ሻንጣውን ይዞ ነበር የወጣው ። መልእክቱ ምን ይሆን ? በአጠቃላይ በዚህ ስብሰባ አንዳርጋቸው በግንቦት 7 ስም ይህን ሰርቻለሁ ፤ ይህን አድርጌያለሁ ፤ ሰራዊታችን በዚህ አውደ-ውጊያ ይህን ግዳይ ጣለ ብሎ ለመናገር የሚለው ቢያጣ ሁለት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ምንቅስቃስ ህዝቢ ትግራይን ሙዚቃዎች ጋብዞን በመሄዱ አመስግኛለሁ ። እንዴት ነበር ስብሰባው ብለው ለጠየቁኝ ሁሉ አንዳርጋቸው ፅጌ ዘፈን ጋብዞን ሄደ ብያቼዋለሁ።

ቸር ይግጠመን!

እንኳን ለመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ ! ከአንበሳው ይብራ
[email protected]