የዓመቱ ‹በጎ ሰው›
የዳንኤል ዕይታዎች ‹የዓመቱ በጎ ሰው› የምርጫ ኮሚቴ ሰባት አባላት ነበሩት፡፡ እነዚህ አባላት ከተለያዩ ሞያዎችና አካባቢዎች የመጡ ሲሆን በ‹የዳንኤል ዕይታዎች› አማካኝነት ለአንድ ወር ያህል አንባብያን ‹በጎ ሰው› የሚሉትን እንዲጠቁሙ ዕድል ተሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በ159 ጠቋሚዎች 70 ግለሰቦችና ሰባት ተቋማት ተጠቁመዋል፡፡
እነዚህን 70 ኢትዮጵያውያንና ሰባት ተቋማትን አመዛዝነው አሥር ምርጦችን እንዲሰይሙ በተለያዩ ክልሎችና ሞያዎች ለሚገኙ እርስ በርሳቸውም ለማይተዋወቁ 9 ሰዎች ተሰጠ፡፡ በዚህም መሠረት ከጠቋሚዎችና ከመራጮች የተሻሉ ድምፆችን ያገኙ አሥራ ሰባት ሰዎች ተመረጡ፡፡
እነርሱም
- እንዳለ ጌታ ከበደ
- መዓዛ ብሩ
- ብንያም በለጠ
- ቴዎድሮስ ጸጋዬ
- ዶ/ር ቴዎድሮስ መሰለ
- ንቡረ ዕድ ገብረ ሕይወት መልሴ
- ዶ/ር በላይ አበጋዝ
- ሸገር ሬዲዮ
- ደ/ር አበበ ከበደ
- ዶ/ር በላቸው ጨከነ
- ሲ/ር ዘቢደር ዘውዴ
- ወ/ሮ አበበች ጎበና
- ቀሲስ ሰሎሞን ሙሉጌታ
- ማኅበረ ቅዱሳን
- ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት
- ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድኅን
- ወ/ሮ ሙሉ ሰሎሞን
ተመርጠዋል፡፡ የመጨረሻውን ድምጽ የሰጠው የምርጫ ኮሚቴው ሲሆን ከመራጮቹ መካከል 3/4ኛና ከዚያ በላይ ድምጽ ያገኙትን በመውሰድ አምስት ሰዎችን ‹የዓመቱ በጎ ሰው› የሚል ሽልማት እንዲቀበሉ ወስኗል፡፡ እነዚህም
ንቡረ ዕድ ገብረ ሕይወት መልሴ
የርእሰ አድባራት አዲስ ዓለም ማርያም አስተዳዳሪ ናቸው፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በትምህርት ያላደረሱት መስክ የለም፤ በሲመትም የታላቋ ደብር አለቃ ሆነዋል፡፡ ይህ እልቅናቸው እንደሌሎቹ ቤት ልሥራ፤ ዘር ልዝራ አላሰኛቸውም፡፡ ነገር ግን ሀገራዊ ጉዳይ ያሳስባቸው ነበር፡፡ እርሳቸው አረጋዊ ናቸው፤ በእርጅና ጎንበስ ብለው ድካምን የሚጋፉት፤ እርሳቸው በዕድሜ ጣርያ ላይ ያሉ ናቸው፤ ዐርፈው መቀመጥ የሚያስፈልጋቸው፤ ግን እንዲህ አላደረጉም፡፡ በዚህ የእርጅና ዕድሜያቸው በመላው ዓለም እየዞሩ፣ እየለመኑና እያባበሉ ኢትዮጵያዊ ዕውቀት የሚገኝባቸው፣ ነገር ግን እንደ ዋልያና ቀይ ቀበሮ በመጥፋት ላይ ያሉት የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲጠበቁ፣ ተሻሽለውም እንዲቀጥሉ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማሰባሰብ ተግተዋል፤ ድካም ሳያግዳቸው የሰው ፊት እያዩ ለአብነት ትምህርት ቤቶች የሚሆን ገንዘብና ቁሳቁስ ሰብስበዋል፡፡
ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመሆን በወጠኑት በዚህ አገልግሎት ዛሬ ከመጥፋት ድነው፣ ከመድከም በርትተው ታሪካዊውን፣ ሃይማኖታዊውንና ሀገራዊውን ዕውቀት የሚያካሂዱ አያሌ የአብነት ትምህርት ቤቶችን አፍርተዋል፡፡ ያሉትን ከመጠበቅም በላይ አዳዲሶች በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ እንዲከፈቱ አድርገዋል፡፡ አረጋዊው ንቡረ ዕድ ገብረ ሕይወት መልሴ!
መዓዛ ብሩ
በመረዋ ድምጽ፣ ልብን ሰርሥሮ በሚገባ፣ ቤተኛ በሚያደርግ የቃለ መጠይቅ ጥበብ እንደ መልካም ወገኛ በማጫወት የተካነች ናት፡፡ ለጋዜጠኝነት ሞያ ባላት ፍቅር ኢትዮጵያዊ መልክ ያላቸውን፣ ታሪክና ባህልን የሚያስታውሱንን ታላላቅ ሰዎቻችንን እንድናውቅ የሚያደርጉንን ፕሮግራሞች የሚያቅፍ የሬዲዮ ጣቢያ በመመሥረትና በመምራት፣ ታላላቅ ሰዎቻችንን ሞት ሳይቀድመን በፊት ቅርስ ሆነው እንዲቀሩ፣ የማይታወቁ ጀግኖቻችን ለአደባባይ በቅተው እንዲታወቁ በማድረግ፤ አንድ የተለየ ጣዕምና ሚና፣ አንድ የሚደመጥና የሚናፈቅ፣ አንድ ልዩ ቀለምና ጠባይ ያለው የሬዲዮ መሥመር ሸገር ሬዲዮን በመዘርጋት የተዋጣለት ተግባር እያከናወነች ትገኛለች፡፡
ዕወቁኝ ዕወቁኝ አትልም፣ ስለ ራሷም ማውራት አትወድም፣ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ እንዲል ግን ሥራዋ ማንነቷን ገልጦላታል፡፡ ዛሬ የሰላምታ ያህል ከብዙዎች የሚደመጠውን ‹ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር› የሚለውን ጣፋጭ ሐረግ ገና የሬዲዮ ጣቢያ ሳይኖራትና የቅዳሜ ጨዋታን በኤፍ ኤም 97.1 ላይ ከሌሎች አጋሮቿ ጋር ስታዘጋጅ ጀምራ መርሕ አድርጋ ይዛዋለች፡፡መዓዛ ብሩ!
አቶ ብንያም በለጠ
የ35 ዓመት ወጣት ነው፡፡ አያቱ በጎንደር ከተማ የታወቁ ነበሩ፡፡ ችግረኞችን በመርዳትና ሰው ለሌላቸው ሰዎች መጠጊያ በመሆን ነበር የሚታወቁት፡፡ እንዲያውም የተቸገረ ሰው ላመጣላቸው ሰው ወሮታውን በእህል ይከፍሉ እንደነበረ የከተማው ሰዎች ዛሬም ያስታውሷቸዋል፡፡ አባቱም በዚያው መንገድ ተጓዙና ሰው መርዳት ሆነ ነገር ዓለማቸው፡፡ በወቅቱ የሼል ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አባቱ አቶ በለጠ ደመወዛቸው 4000 ብር ነበር፡፡ በቤት ውስጥ ግን ልጆቻቸው ሽሮ እንኳን አጥተው ጦም የሚያድሩበት ጊዜ ነበር፡፡ ጠጥተውበት አይደለም፣ ቁማር ተጫዉተዉ ተበልተውም አልነበረም፡፡ ለችግረኞች የሚራሩ በመሆናቸው ለድኾች አከፋፍለው ስለሚጨርሱት እንጂ፡፡
መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ያፈራል ነውና፤ ይህንኑ በጎ ነገር ልጃቸውም ወረሰው፡፡ ለታክሲ የተሰጠውን ገንዘብ በእግሩና በአውቶቡስ እየተጓዘ በመቆጠብ ችግረኛ ተማሪዎችን ይረዳበት ነበር፡፡ እንዲህ እየኖረና እየተማረ አድጎ አሥራ ሁለተኛ ክፍል አራት ነጥብ አመጣ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ገብቶ ሕግ ተማረ፡፡ ከዚያም ተመርቆ ጥቂት ጊዜ ሠራና አሜሪካ ገባ፡፡ እዚያም ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪውን ሠራ፡፡
እዚያ አረጋውያንን በሚንከባከብ ድርጅት ውስጥ ሲሠራ የሀገሩን አረጋውያን ነበር በልቡ የሚያስበው፡፡ እንዲያም ብሎ እዚያ እየሠራ ገንዘብ በመላክ እዚህ የሠፈሩን ድኾች ይረዳ ነበር፡፡ እንዲህ እንዳደገው ዓለም የሚንከባከባቸውና ርግማናቸውን ሳይሆን ምርቃታቸውን የሚያተርፍ ተቋም በሀገሬ መቼ ነው የሚኖረው? እያለም ያስብ ነበር፡፡ እዚያ ማዶ ሆኖ የሚልከው ገንዘብ እዚህ በሚገባው ቦታ እየዋለና የሚፈለገውን ውጤት እያመጣ አለመሆኑን አየና ነገር ዓለሙን ሁሉ ጥሎ ሀገሩ ገባ፡፡
በቤተሰቦቹ ቤት ይህንን ክብር ያለው ግን ቆራጥነትና ትዕግሥት፣ ትጋትና ቻይነት የሚጠይቅ አገልግሎት ሲጀምረው፤ ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹና ወዳጆቹ ሁሉ ‹አበድክ › ብለውታል፡፡ እርሱ ግን አለማበዱን በተግባር ለማሳየት ተጋ፡፡ ቀስ በቀስም ተቃዋሚዎቹን ሁሉ ተባባሪ አደረጋቸውና ‹መቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ ድርጅትን› መሠረተ፡፡ ዛሬ በዚህ ድርጅት 170 አረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን ይረዳሉ፡፡ እርሱም መኖርያው ከአረጋውያኑ ጋር ነው፡፡ የበሉትን ይበላል፤ የጠጡትን ይጠጣል፡፡ አቶ ብንያም በለጠ!
ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድኅን
የአፍሪካ የምግብ ችግር ከምርት ብቻ ሳይሆን ከምርቱ ገበያ ጋር የተያያዘ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ በዚህም የተነሣ ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች ላይ ሠርተዋል፤ ተመራምረዋል፡፡ በዓለም ባንክ፣ ዋሽንግተን በሚገኘው ዓለም ዐቀፍ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ማዕከል፣ እና በተባበሩት መንግሥታትም በከፍተኛ ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ በኢኮኖሚክስ ዲግሪያቸውን ከኮርኔል ዩኒቨርሲቲ፣ ማስትሬታቸውን ከሚችጋን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፤ በአፕላይድ ኢኮኖሚክስ ደግሞ ፒ ኤች ዲያቸውን ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ወስደዋል፡፡
|
አቶ ሰሎሞን የዶ/ር እሌኒን ሽልማት ሲቀበሉ
|
ለምግብ እህል እጥረት አንዱ ችግር የገበያው ሁኔታ ነው የሚከለውን የጥናት ውጤታቸውን እውን ይዘው ከነ መፍትሔው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2004 ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ሃሳባቸውን ወደ ተቋም በመለወጥም በኢትዮጵያ የምርት ገበያ እንዲመሠረት ዋነኛዋ ሐሳብ አፍላቂና አንቀሳቃሽ ኃይል ሆነው ሠሩ፡፡ በዚህም ምርምርንና ጥናትን በጥራዞች ላይ ከማዋል ባሻገር ለሀገር ችግር መፍትሔ አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ አሳዩ፡፡ ዛሬም ናይሮቢ ላይ ከመሠረቱት ቢሮ እየተነሡ በአፍሪካ ይህንኑ ሐሳባቸውን ለማካፈልና አፍሪካን ከምግብ እጥረት ለማላቀቅ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድኅን!
እንዳለ ጌታ ከበደ
ደራሲ ነው፡፡ ሰባት ያህል መጻሕፍትን አቅርቦልናል፡፡ የተወለደው ወልቂጤ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚከታተልበት ጊዜ ‹ተስፋ› ብሎ በሰየማት አነስተኛ የመጻሕፍት መደብሩ ለከተማዋ ነዋሪዎች እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ እያከራየ የንባብ ባሕል እንዲዳብር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ እንደ ተከራዮቹ ሞያና የትምህርት ደረጃ ስለ መጻሕፍቱ አጭር ማብራርያ እየሰጠ፤አንብበው ሲመልሱም ስለ መጻሕፍቱ አስተያየት እየተቀበለ ያበረታታ ነበር፡፡
በወልቂጤ ከተማ ውጤታማነትን ለማበረታታት በራሱ ተነሣሽነት በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማቶችን ይሸልማል፡፡
የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሲሆን በዚህ የሥራ ድርሻው አዳዲስ ሐሳቦችን በማመንጨትና በመተግበር ደራስያን እንዲጠቀሙ ድርሰትም እንድታብብ እያደረገ ነው፡፡ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የአእምሮ ሥራቸውን ማሳተም ላልቻሉ ደራስያን በተዘዋዋሪ ገንዘብ ድርሰቶቻቸውን የማሳተሙን ሐሳብ አቅርቦ ከሌሎች ጋር ሆኖ እንዲተገበር አድርጓል፡፡
ከኢትዮጵያ ጡረተኞች/አዛውንቶች ጋር በመተባበር መድረኮችን አዘጋጅቶ ወጣቶችና አረጋውያን ተገናኝተው ልምድ እንዲለዋወጡ አድርጓል፤
በወር አንድ ጊዜ በብሔራዊ ቴአትር የሕጻናት ዝግጅት በሕጻናት እንቀዲርብ በማድረግ ፣ የንባብ ባህል በሕጻናት ላይ እንዲዳብር የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ እንዳለ ጌታ ከበደ!
ተስፋ ያዘለ ሃሳብ
ይህ ‹የበጎ ሰው ሽልማት› ራሱን በቻለ ሁኔታ ተቋቁሞ ወደፊትም በየዓመቱ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ሌሎች ጀግኖችን ለመፍጠር ያሉትን ማድነቅና ማክበር ያስፈልጋል፡፡


.jpg)