ወያኔ ለካራቱሪ ኩባንያ ሰጥቶት የነበረውን ሰፊ መሬት የተወሰነውን ክፍል መልሶ መውሰዱ ታወቀ

የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ካራቱሪ ለሚባለው የህንድ ኩባንያ በገፍ ከሰጠው መሬት ላይ ከ147 ሺ ሄክታር በላይ መልሶ እንደወሰደ ብሉምበርግ የተባለው ድህረ ገጽ ዘገበ። የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ይህንን መሬት መልሶ ለመውሰድ የተገደደዉ ከአለማቀፍ ማህበረሰብ በደረሰበት ጫናና በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለም የአገራችንን መሬት ለባዕዳን አሳልፎ መሰጠቱን ተቃውመው በሰፊው መንቀሳቀስ በመጀመራቸው ቢሆንም ዋናዉ ምክንያት ግን እንካችሁ ብሎ ለባዕዳን የሰጠዉ መሬት ባዕዳኑን ራሳቸዉን አስገርሞ ለትችት በማብቃቱ ነዉ፤ በተለይ የካራቱሪ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ በቅርቡ ወደ ጋምቤላ ተጉዞ ስለመሬት ቅሚያ ጥናታዊ ፊልም ለሰራው ለጋርዲያን ጋዜጠኛ ያንን የሚያክል ለም መሬት በነጻ ማግኘቱ እንዳስገረመዉ በመናገሩና ፊልሙ በመላው አለም በመሰራጨቱ በአገዛዙ ዙሪያ ቅሬታ መፍጠሩ ለመሬቱ መመለስ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የወያኔን ገመና የሚያዉቁ የፖለቲካ ተንታኞች አስረግጠዉ ይናገራሉ።

 በፊልሙ ላይ የኩባንያው ባለቤት “መሬቱን ሲሰጡን ሄደን አላየነውም ዝም ብለው ሰጡን ወሰድን” ብለዉ መናገራቸው በአንድ በኩል ህዝባዊ ቁጣዉን እንዳባባሰዉና በሌላ በኩል ደግሞ የገዢውን ፓርቲ ማንነት በግልጽ ማሳየቱ ይታወሳል። የኩባንያው ባለሀብቶች እንዲህ አይነት ንግግር ባይናገሩ ኖሮ ህንዳዊዉ ኩባንያ ካራቱሪ ጭራሽ ተጨማሪ መሬት ያገኝ እንደሆነ እንጂ ወያኔማ የኢትዮጵያ ጉዳይ የማይጨንቀዉ ጉድ መሆኑን ከብዙ የህዝብ አስተያየት መረዳት ተችሏል።

የካራቱሪው ዋና ስራ አስኪያጅ ሳይ ራማካሪሻና ካራቱሪ ለብሉምበርግ እንደገለጹት ዜናው ፈጽሞ መሰረት የሌለው ነው ከማለት ውጪ የአንድ አነስተኛ የአውሮፓ አገርን የሚያክል መሬት ያገኘው ካራቱሬ መሬቱን ስለመቀማቱ የገለጸው ነገር የለም። ለካራቱሪ የተሰጠው መሬት በአለም ላይ በርካሽነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሲሆን፣ ኩባንያው በአመት ለአንድ ሄክታር መሬት የሚከፍለዉ አንድ የአሜሪካን ዶላር ብቻ ነዉ ። የሚገርመዉ ዘረኛዉ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ አስከዛሬ የሰጠዉ መሬት አልበቃ ብሎት አሁንም ለተለያዩ አለማቀፍ ኩባንያዎች የእርሻ መሬቶችን በርካሽ ዋጋ በመቸብቸብ ላይ ነዉ።

 ከዚሁ ጋር በተያየዘ ከፍተኛ መጠን ያለው የአገሪቱ የደን ኃብት ሊተካ በማይችል ሁኔታ መውደሙ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉና፣ አርብቶ አደሮች ለከብቶቻቸው የሚሆን የግጦሽ ቦታ አጥተው መቸገራቸው በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

የግንቦት 7 ንቅናቄ ወያኔ ህዝባችንን እያፈናቀለ ለውጪ ባለሃብቶች እንደገና ዳቦ የሚያከፋፍለው መሬት በአስቸኳይ እንዲቆም ከመጠየቅ አልፎ ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም የሚያስጠብቅላት መንግሥት በምትመሰርትበት ጊዜ አሁን በዘረፋው በመተባበርር መሬታችንን እየወሰዱ ያሉ ሁሉ ምንም አይነት ህጋዊ ዋስትና እንደማይኖራቸው ልያውቁት ይገባል ሲል ማስጠንቀቁ ይታወቃል።