የዘረኛውን መለስ ዜናዊ አገዛዝ የመሬት ቅሚያ ፖሊሲ በመቃወም የሰሜን ጎንደር የደባርቅ ወረዳ ህዝብ ተቃውሞ አስነሳ በወረዳ የተነሳው ቅዋሜ እስካሁን አልበረደም
ሰሞኑን ከወደ ኢትዮጵያ የሚሰማዉ ዜና “ወያኔ መሬት ቀማ” ወይም “ወያኔ ቤት አፈረሰ” የሚል ብቻ ሆኗል፡፡ መቀሌ ዉስጥ የህዝብ ቤት ካላፈረስኩ ብሎ ከከተማዉ ነዋሪዎች ጋር ግብግብ ዉስጥ ገብቶ የከረመዉ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ፊቱን ወደ ጎንደር አዙሮ ሰሜን ጎንደር ዉስጥ በደባርቅ ወራዳ የምንቃር ንኡስ ከተማ ህዝብ ለግጦሽ የሚጠቀምበትን ሰፊ መሬት ለባለሃብቶች ለመሸጥ ሲያስማማ የአካባባዉ ህዝብ በከፍተኛ ቁጣ ተንቀሳቅሶ መሬቴን አላስነካም ብሎ የወያኔን ባለስልጣኖች አሳፍሮ ወደመጡበት መልሷቸዋል።
ጀግናዉ የደባርቅ ከተማ ህዝብ የወያኔን ተንኮል ተከታትሎ ማክሸፍ የቻለዉ የክልሉ ባለስልጣናት ለአካባቢው ህዝብ የአትሌቲክስ መንደር እንሰራለን በሚል ሽንገላ መሬቱን ለመከለልና የመሰረት ድንጋይ ለማኖር ወዳካባቢው እንደሚመጡ አስቀድሞ መረጃ ከደረሰው በኋላ ውስጥ ለውስጥ ሲመካከርና ሲዘጋጅ ከቆየ ቦኋላ እንደሆነ ታውቆአል። ህዝብ ይቃወመናል የሚል ምንም አይነት ስጋት ያልነበራቸው የክልሉ የወያኔ ሹመኞች በቦታው እንደደረሱ በነቂስ ወጥቶ በስፍራው ይጠባበቃቸው የነበረውን ህዝብ እንደለመዱት በጸጥታ ሃይል ለመበተን ጥረት ያደረጉ ቢሆንም መሬቴን አላስነካም ብሎ በብሶትና በቁጣ ገንፍሎ የወጣዉን ህዝብ መቆጣጠር ተስኗቸዉ ፊታቸዉን በሀፍረት ሸፍነዉ ወደመጡበት ለመመለስ ተገድደዋል።
“ላለፉት 20 አመታት ያታለላችሁንና ከአብራካችን የወጡ የራሳችንን ልጆች እንደመሳሪያ በመጠቀም ያዋረዳችሁን ይበቃል ከአሁን ቦኋላ በምንም አይነት መንገድ አንታለልላችሁም” ያለው የደባርቅ ነዋሪ “እስከዛሬ ተታልለን ብዙ ነገር ሰጥተናችኋል ካሁን በኋላ ግን የምንሰጣቸሁ ምንም ነገር የለም። ደግሞስ እንዴት ብትንቁን ነዉ በስፖርት ስም መሬታችንን ለውጭ ባለሀብቶች ልትሰጡብን የመጣችሁት” ሲል የደባርቅ ህዝብ ቁጣዉን በምሬት ሲገልጽ የዋለ ሲሆን፣ የህዝቡን ቁጣ መቋቋም የተሳናቸው የወያኔ መልዕክተኞች ለቴሌቪዥን ፍጆታ እንዲሆናቸዉ በዕቅድ ያልተያዘ ቦታ ላይ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዉ በሀፍረት ወደመጡበት ተመልሰዋል።
ጸጥታ እንዲያስከብር ወደ አካባቢወ ተጠርቶ የመጣው የጸጥታ ሃይል ከአንዳንድ ተቃዋሚዎች ጋር ግጭት ለመፍጠርና ድብደባ ለማካሄድ ሙከራ ከማድረጉም በላይ የታጠቀዉን መሳሪያ ወደሰማይ ሲተኩስ እንደነበር በአካባቢዉ የነበሩ የአይን ምስክሮች ተናግረዋል። ደባርቅ ዉስጥ በመሬት ጉዳይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አሁንም እንዳልበረደና ህዝቡ መሬቱ እንዳይሸጥበት በንቃት አካባቢዉን እየጠበቀ እንደሆነ ተገልጿል።