አዲስ አበባ ከተማ በትራንስፖርት እጥረት እየተጨናነቀች ነው፣ ነዋሪዎች ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ አዲስ የሃሳብ አቅጣጫ ማስቀየሪያ ስልቱ ነው አሉ

በአዲስ አበባ ከተማ ሚኒባስ ታክሲዎች በሚያስከፍሉት ታሪፍ ላይ ጭማሪ እንዲደረግና ትናንሽ ታክሲዎች ደግሞ በርቀት መለኪያ እየተጠቀሙ ክፍያ የሚጠይቁበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መታቀዱን፣ የአገዛዙ ሹመኞች መግለጻቸውን ተከትሎ፣ በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የታክሲና አውቶብስ ፌርማታዎች ነዋሪዎች እጂግ ሲጨናነቁ መታየታቸውን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ሪፖርት ገለጸ::

እንደሪፖርተራችን ዘገባ በተለይም ሰፈሮቻችው እጂግ ራቅ ያሉ ቦታዎች የሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለበርካታ ሰአታት በታክሲ እጦት ሲንገላቱ እንደነበር አቅም ያላቸው በእግር ጉዙ ወደየቤቶቻቸው መድረሳቸውን፣ አቅም የሌላቸው ደግሞ ባሉባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ቤት ለማደር እንደተገደዱ ገልጹአል።

አዲስ የተፈጠረውን የታክሲ ችግር አስመልክቶ አስተያየታቸውን እንዲሰጡት ዘጋቢያችን ያናገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ ተመሳሳይ በሆነ አገላለጽ የአሁኑ የታክሲ ችግር ነጠላ ዜማ ደግሞ አዲስና ህብረተሰቡም ስለሌላ ነገር እንዳያስብ ማጥመጃ እንደሆነ እንደሚያምኑ ገልጸዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በቅርብ ጊዜ የነጋዴውን ማህበረሰብ ከህዝቡ ጋር የማጣላት ሰፊ ዘመቻ ከፍቶ ሊሳካለት ባለመቻሉ አሁን ደግሞ ታክሲ አሽከርካሪና የታክሲ ባለሃብቶችን ከህብረተሰቡ ጋር በማናቆር በጋራ እንዳይቆሙ ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ ነው ብለዋል። አያይዘውም በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ አመጽ ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት ያየለበት ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ እያንዳንዱአን ቀዳዳ ለማድፈን ሌት ተቀን እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። በመጨረሻም ምንም አይነት አፈና ያድርግ ምንም አይነት ዘዴን ይቀይስ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ አብዮት መፈንዳቱ ፍጹም አይቀሬ እንደሆነ በርካታ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን በመግለጽ አስተያየታቸን አጠቃለዋል።